ባግዳድ፤ በመቶዎች የሚገመቱ ያዚዲዎች ተገደሉ | ዓለም | DW | 10.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ባግዳድ፤ በመቶዎች የሚገመቱ ያዚዲዎች ተገደሉ

የኢራቅ የሰብዓዊ መብቶች ሚኒስትር በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል 500 የሚሆኑ ያዚዲዎች በእስላማዊ መንግሥት ሚሊሺያዎች መገደላቸዉን አስታወቁ።

ሞሐመድ ሺያ አል ሱዳኒ እንደሚሉት ሲንጃር ላይ ከታጣቂዎቹ ጥቃት ካመለጡ ያዚዲዎች ዘግናኝ መረጃዎችም ደርሰዋቸዋል። በተጠቀሰችዉ ከተማ የሚኖሩትን ያዚዲዎች እስልምናን እንዲቀበሉ ያስገደዱት የሱኒ ታጣቂዎች በእጃቸዉ ከገቡት ሰለባዎች ገሚሱን ሴቶችና ሕፃናት ጭምር ከነነፍሳቸዉ ቀብረዋቸዋል። ወደ300 የሚገመቱ ሴቶችን ደግሞ ለባርነት አግዘዋቸዋል። እስላማዊ ተዋጊዎቹ ቁጥራቸዉ አናሳ የሆነዉ ያዚዲዎችን ሰይጣን አምላኪዎች በሚል ሃይማኖታቸዉን እንዲቀበሉ እያስገደዱ ነዉ። »

በሌላ በኩል በኩርድ ኃይሎች አጀብ 20 ሺ የሚሆኑ ኢራቃዉያን የሲንጃር ተራራን ለቀዉ በሶርያ በኩል ወደኩርዲስታን በሰላም መግባታቸዉ ተገልጿል። ርምጃዉ እንዲሳካ የረዳዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጀቶች ታጣቂዎቹ ላይ ያደረሱት የተሳካ ድብደባ እንደሆነም ተዘግቧል። ዋሽንግተን የጦር አዉሮፕላኖቿ ሰሜን ኢራቅ ዉስጥ የታጣቂዎቹን ይዞታ በድጋሚ መደብደባቸዉን አመልክታለች። ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ከአየር የተሰነዘረዉ ድብደባ የዘር ማጥፋት እንዳይፈጸም አስፈላጊ ነበር ነዉ ያሉት።

«አሸባሪዎቹ የተደላደለ ቋሚ ማረፊያ እንዳያገኙ የኢራቅ መንግሥትና የኩርድ ኃይሎች እነዚህን አሸባሪዎች እየተዋጉ ባሉበት ሁኔታ ምክርና ወታደራዊ ድጋፍ መስጠታችንን እንቀጥላለን። ኢራቅ ዉስጥ እየተባባሰ የመጣዉን ሰብዓዊ ቀዉስ ለመግታትም ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጋ መሥራታችንን እንቀጥላለል። ትኩረታችን በተራራዉ ላይ የሚገኙት ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ላይ የዘር ማጥፋት እንዳይፈጸም መከላከል ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም ለቁጥር አዳጋች የሆኑ ኢራቃዉያን በርካታ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ቤታቸዉን ለቀዉ ለመሸሽ እየተገደዱ ነዉ።
ከታጣቂዎቹ ለማምለጥ ወደሲንጃር ተራራ የሸሹት ወገኖች ለበረሃዉ ሙቀት እና ዉሃ ጥም ተጋልጠዋል። ሕፃናትና አዛዉንት ደግሞ በዚሁ ምክንያት ሕይወታቸዉን እያጡ ነዉ። ባግዳድን የጎበኙት የፈረንሳይ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎሮ ፋቢዮ ሀገራቸዉ በርካታ ቶን ርዳታ እንደምታቀርብ ቃል ገብተዋል። ጉብኝታቸዉ በሰሜን ኢራቅ በጦርና በረሃብ አደጋ ዉስጥ ለሚገኙት ወገኖች የሚቀርበዉ ርዳታ ለማጠናከር መሆኑ የተገለጸዉ የፈረንሳዩ ባለስልጣን የባግዳድ መሪዎች በታጣቂዎቹ ላይ ተብባብረዉ እንዲዘምቱም ጠይቀዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ልደት አበበ