ባድመ፣ ግዙፍ ተቋማት ለሽያጭ፣ ሹም ሽርና ሌሎችም | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 08.06.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ባድመ፣ ግዙፍ ተቋማት ለሽያጭ፣ ሹም ሽርና ሌሎችም

ሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን ትንፋሽ ያሳጣ ይመስላል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱ፣ ግዙፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ ለአክሲዮን ሽያጭ ዝግጁ እንደኾኑ መነገሩ፣ በደህኅንነቱ እና መከላከያው የአመራር ለውጥ መደረጉ ብሎም የአልጀርሱ ስምምነትን በተመለከተ የተሰጠው ውሳኔ ያለ ፋታ አነጋግሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:49
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
07:49 ደቂቃ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን ፋታ ያሳጣው ሳምንት

በሳምንቱ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ፓርቲ ኢሕአዴግ መንግስት የሚቆጣጠራቸዉን ግዙፍ አገልግሎት ሰጪ ሠጪ እና አምራች ቋማትን በከፊል ለባለሐብት ለመሸጥ ማቀዱን ገልጧል።የኢትዮ-ኤርትራን የድንበር ጦር ለማስቆም የተደረገዉን ስምምነት እና አወዛጋቢዋን የባድመ ከተማንና አካባቢዋን ለኤርትራ የሚሰጠዉን የድንበር ኮሚሽን ዉሳኔን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ወስኗልም። 

ከሰባ ሺህ በላይ ሰው እንደ ቅጠል ረግፎበታል። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎችን ለአካል ጉዳት ዳርጓል። ማዶ ለማዶ የሚተያዩ ዘመዳሞችን ለዓመታት ነጥሏል።  የባድሜ እና አካባቢዋ ውዝግብ።  ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጦር አማዞ ደም እንደ ዥረት አንዠቅዥቋል። በጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አኅመድ የሚመራው መንግሥት  የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታ ለመተግበር መስማማቱን የገለጠበት ውሳኔ የአካባቢው ሰላም ወሳኝ ነው ሲሉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  የተናገሩ ጥቂት አይደሉም። ቁጣቸውን የገለጡ ግን በርካቶች ናቸው። የሀገሪቱን ግዙፍ የልማት ድርጅቶች በከፊል አለያም ሙሉ በሙሉ ለግሉ ዘርፍ ክፍት ሊደረጉ ታስቧል  የሚለው ውሳኔ መሰማቱም ተጨማሪ ቁጣ አጭሯል።  የደህንነት ኃላፊ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሽረትም ሌላ መነጋገሪያ ኾኗል። 

ሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን ትንፋሽ ያሳጣ ይመስላል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱ፣ ግዙፍ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ ለአክሲዮን ሽያጭ ዝግጁ እንደኾኑ መነገሩ፣ በደህኅንነቱ እና መከላከያው የአመራር ለውጥ መደረጉ ብሎም የአልጀርሱ ስምምነትን በተመለከተ የተሰጠው ውሳኔ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን ያለ ፋታ አነጋግሯል። 

ሠላምም ጦርነትም ሳይኖር  ወታደሮችን አፋጦ ለዓመታት ሥጋት አዝሎ የቆየው የባድሜ እና አካባቢዋ ጉዳይን በተመለከተ ኢሕአዴግ የአልጀርሱን ስምምነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እተገብራለሁ  ማለቱ ብዙዎችን አስደምሟል። አስራት አብርሃም በፌስቡክ ገጹ ባቀረበው ጽሑፍ የባድሜ ጉዳይ ጠፍቶ ከቆየበት ፌስቡክ እንደመለሰው ይገልጣል። «ሕወሓት በሥልጣን ለመቆየት ካለው ጥማት የተነሳ አሳልፎ የማይሰጠው ነገር ያለ አይመስልም» ሲልም ኢህአዴግ የአልጀርሱ ውሳኔን በተመለከተ የያዘውን አቋም ተቃውሟል።

Grenzkonflikt Eritrea Äthiopien Soldat Eritrea (AP)

 

የምሥራች አጥናፉ፦ «ዛሬ አይደለም እኮ ስምምነት ፊርማው የተፈፀመው። አልጀርስ ላይ ነው ያለቀው» ብላለች።  «ምንም ፋይዳ በሌለው ጦርነት ባድሜ ላይ ስንቱ የኢትዮጵያ ወጣት ውድ ሕይወቱን ገብሮ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ሐዘኑ ገና ከውስጣችን እያለ እንደተራ ነገር ባድሜን ለኤርትራ በማስረከብ የወገኔ ደም ከንቱ ሁኖ ቀረ: ሁለት ሞት ማለት ይሄ ነው» ያለው ደግሞ ገዛኸኝ መለስ ነው፤ በፌስቡክ። 
ቴዎድሮስ ምክረ ግን «ጦርነት አይበቃንም??» ሲል በአጭሩ ጽፏል። «የተቀበለው እኮ ዛሬ አይደለም! ሲፈረም ነበር መቃወም» ያለው ደግሞ ሠይፈ ኤም ኤች ነው። ዘመን በተስፋ የተባለ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ «ህዝብን ያላማከረ ውሳኔ ውድቅ ነው» ሲል ውሳኔውን ተቃውሟል። 

ውሳኔውን «ፍፁም ፍትሀዊ ያልሆነና ህዝቡን ያስቆጣ መላው የትግራይ ህዝብን ፍላጎት በተለይም በድንበር አከባቢ የሚኖር ህዝብ ሀሳብና ፍላጎት ግምት ውስጥ ያላስገባ ምናልባትም ሌላ መዘዝ ይዞ ሊመጣ የሚችል ውሳኔ ነው» ሲል የገለጠው ደግሞ ብርሃነ ኩማኒት የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው። ያም በመኾኑ ሲል ይቀጥላል ብርሃነ፦ «ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የአልጀርስ ስምምነትን በተመለከተ የወሰነውን ውሳኔ መልሶ ማየት አለበት። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ አስቸጋሪ ግዜ ከጎናችን እንደሚቆም እናምናለን» ሲል አክሏል።

በትዊተር ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ሚካኤል ኦፒየልካ የተባሉ ግለሰብ በጀርመንኛ ቋንቋ ቀጣዩን አስፍረዋል። «ጦርነት ሕዝቡን አንዳችም የጠቀመው ነገር የለም። ይልቁንስ ስግብግብ የኾኑ መሪዎችን ነው የጠቀመው። መሪዎች ተጠያቂ የኾኑ ጊዜ አፍሪቃ ሐብታም ልትኾን ትችላለች።» ብሏል።

Karte Infografik Umstrittene Gebiete Äthiopien Eritrea DEU


ጦማሪ ዘላለም ክብረት በአልጀርሱ ስምምነት ወቅት የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አቶ ሥዩም መስፍን የአልጀርሱን ውሳኔ በተመለከተ በእንግሊዝኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ የሚታዩበትን የቪዲዮ ምስል አያይዟል። የያኔው ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር የተናገሩትንም ቃል በቃል በእንግሊዝኛ ጽፎ አቅርቦታል። እንዲህ ይላል፦ «ኤርትራ በተሳሳተ ይገባኛል ጥያቄ ወራ የሰፈረችባቸው ባድሜ እና አካባቢዋ አኹን በኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ ተወስኗል» ይላል መልእክቱ። 

ጎበና ስትሪት በሚል ስም የትዊተር ተጠቃሚ የኤርትራው የማስታወቂያ ሚንሥትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል ባድመን በተመለከተ የኢትዮጵያ ውሳኔን እንዴት እንደሚያዩት ረቡዕ እለት በአንድ የትዊተር ተጠቃሚ በትግርኛ ተጠይቀው የሰጡትን መልስ አያይዟል። ሚንሥትሩ ግልጽ ባልኾነ መልኩ «ከ16 ዓመት በፊት ነው የተቀበልነው» ብለዋል ሲልም ትርጉሙን አስፍሯል። 

የኤርትራ መንግሥት ዝምታን በተመለከተ ሔርሞን ትዊተር ላይ እንዲህ የሚል መልእክት ጽፋለች። «አንዳንድ ጊዜ ምንም አለማለት ምርጥ መልስ ነው። የኤርትራ መንግሥት።» 

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መንግሥት በብቸኝነት የተቆጣጠራቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ድርሻ "ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል" ለመሸጥ ማቀዱም ሌላው የመነጋገሪያ ርእስ ነበር።  ውሳኔው ተወዳዳሪ አልባ ጥቂት ፈርጣማ ሐብታሞችን ፈጥሮ የድሆችን መከራ ያራዝማል ሲሉ ርምጃውን የተቃወሙ በርካቶች ናቸው።  የለም ወደ ሊበራሊዝም እና ኒዮ ሊበራሊዝም መግባታችን ለድህነታችን ፈጣን መፍትትኄ ነው ሲሉ የሞገቱም አሉ። 

«አብዮታዊ ድሞክራሲ ይብቃ....ወደ neo-liberalism በመንግስት ስር ሆነው ምንም የመጣ ነገር የለም ..ይሸጥ...በየትኛውም መንገድ አዲስ አስተሳሰብ የድሮውን አሁን መቀየር አለበት!.ለውጥ ለውጥ ምንም ይሁን የድሮው ሰልችቶኛል ይሞከር» ሲል በፌስቡክ አስተያየቱን ያሰፈረው በኃይሉ አስማረ ነው። 
በኃይሉ ባቲ ደግሞ፦ «ባደጉት አገሮች እኮ አየር መንገድና የባቡር ትራንፖርት የመንግሥት ናቸው እንደውም a national career ይሉታል መንግሥት በነዚህ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል» ሲል ተቃውሞውን ገልጧል። 

«ገዥው ማን ይሆን? ቁም ነገሩ እዚህ ላይ ነው» ሲል የጠየቀው ደግሞ ኢትዮጵያን ፍሪደም በሚል ፌስቡክ የሚጠቀም ግለሰብ ነው። «ይኽ ለዶክተሩ ትልቅ ውርደት ነው በጣም እየቸኮለ ነው ቢረጋጋ» የኃይሌ ዓለም አጭር አስተያየት ነው።

ሰው ለሰው በሚል የፌስቡክ ስም ተጠቃሚ የቀረበ መልእክት እንዲህ ይነበባል። «ሐሳቡ ግልጽ ነው ግን ገዢዎቹ እነማን ናቸው? መጀመርያ የተዘረፈው የህዝብ ገንዘብ ይመለስ ከዚህ ውጪ የትላንት ዘራፊዎች የዛሬ ባለ አክሲዎኖች ሁነው ከች ብለው የተለመደ ስራቸውን ሊሸነሽኑ አስበዋል ማለት ነው» ይላል። 

ሐሙስ ዕለት ይፋ የኾነው የደኅንነት ኃላፊ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሽርም ሌላው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ ነው። ትዊተር ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ፦ «በኢትዮጵያ ፖለቲካ እጅግ ከሚፈሩ ሰዎች አንዱ ጌታቸው ተሰናብቷል» ያለው አያሌው ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ «እውነተኛ ሥልጣን» እንደሚያገኙ እና «ተጽዕኖ መፍጠር» እንደሚችሉ እምነት መጣል መጀመሩን ጽፏል። 

ቢዮ በበኩሉ ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የበሩት ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ጀነራል ሳሞራን መተካታቸውን የሚገጥለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፍጹም አረጋ የትዊተር መልእክትን በማያያዝ ቀጣዩን ጽፏል።   «ይኽ ታሪካዊ ስህተት ነው፤ መቼም የማይተካ» ብሏል። ሹም ሽረቱ ከተነገረበት ሐሙስ እለት ጀምሮ በርካቶች ተቃውሞ እና ድጋፋቸውን በመግለጥ ላይ ይገኛሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic