ባድመ-ሠላም ወይስ ጦርነት | የጋዜጦች አምድ | DW | 02.12.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ባድመ-ሠላም ወይስ ጦርነት

የኢትዮጵያ የአቋም ለዉጥ ለዉጪዎቹ እንደገባ ሁሉ ለተቃዋሚዎች በተለይ ለሕዝቡ ቢገባ ጥሩ ነበር።ለዉጡ ተፋላሚ ሐይላትን፤ የሁለቱን ሕዝቦች የሚያረካ ሠላም ካሰፈነ ቢያንስ ለአፍሪቃ ቀንድ ኮናሪ እንዳሉት ታላቅ ቀን በሆነም ነበር።አልሆነም።


ነጋሽ መሐመድ

እንደገና-እንበልላት።ከሚኖር፣ ከተወለደ፣ ባለፍ አገደም ከረገጣት በስተቀር የሚያዉቃት አልነበረም።ቆላ ነች።ደረቅ።ያጣች-የነጣች።ደሐ።የጥቂት ሺሕዎች ትንሽ ሐገር።ማን በምኗ እንዴት ይወቃት? ባድመ።ግንቦት-አምስት 1990 የኤርትራ ጦር ሲርመሰመስባት-የልማት-ብልፅግና ሳይሆን የእልቂት-ፍጅት ቋትነት፣ የሠላም-መረጋጋት ሳይሆን የመዛዛቻ፣ የትርምሥ መጋሚያነት ሥሟ ገዘፈ።

የሩቅ-የቅርቡ ታዛቢ እንደተመቸዉ እያሰለሰ-ባለጉዳዩ መአልት-ወሌት የትንሺቱን-ግዛት ግዙፍ ሥም እንደጠራ-ሥድስት አመት ተመንፈቅ ቆጠረ።ባለፈዉ ሳምንት-ሐሙስ ከአዲስ አበባ የተሰማዉ፣ ትንሽ ሥሟን ያገነነዉ መጥፎ ሁነት የማብቂያ-መባሺያዉ አንፃራዊ ምልክት መሆን አለመሆኑ አይታወቅም።እንደገና ባድመ ለማለት ምክንያት መሆኑ ግን አያጠያይቅም።

የዩናይትድ ስቴትሱ የሠላም ጥናት ተቋም ባልደረባ ጆን ፕሬንደርጋስት የዛሬ ሰወስት አመት ግድም እንደፃፉት ግንቦት አምስት 1990 ባድመ ላይ የፈነዳዉ ዘግናኝ ጦርነት ይፈነዳል ብሎ ማንም አልጠበቀም ነበር።

ጦርነቱ በዚያ ስፋትና ፍጥነት መጋሙ ደግሞ የሩቅ-የቅርቡን ታዛቢ፣ የሁለቱን ሐገሮች ሕዝብ አይደለም የጦርነቱን ዘዋሪ-የሁለቱን መንግሥታት ሳይቀር ማስገረሙ ሐቅ ነዉ።የአዲስ አበባና የአሥመራ መሪዎችም፣ አንዱ ሌላዉን በተጠያቂነት ዉንጀላ ያድምቁት እንጂ የመገረማቸዉን ሐቅ ደብቀዉት አያዉቁም።

ማንም ያልጠረጠረዉ ጦርነት መጫሩን ማንም እንዳረጋገጠ የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሱዛን ራይስ እና የሩዋንዳ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ፖዉል ካጋሚ ለሽምግልና ፈጥነዉ መንቀሳቀሳቸዉ የጦርነቱን አስገራሚ ሥፋትና ፍጥነትና ዘግናኝ ዉጤትም ለመግታት ነበር።ከመፍትሔዉ ይልቅ መወነጃጀሉን፣ ከሸምጋዮች ጥረት ከማድነቅ ይልቅ ይብስ ሐሳባቸዉን እነሱነታቸዉንም ማጣጠሉን ሁለቱ መንግሥታት በተለይ የአስመራ መሪዎች በመምረጣቸዉ ጦርነቱን የመግታቱ የመጀመሪያዉ ሙከራ በሙከራ ቀረ።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባንድ ወቅት «የሠላሳ አራት አመትዋ ወይዘሮ ማድረግ ያለበኝን ልትነግረኝ ትሞክራለች» በማለት ያሾፉባቸዉ ሱዛን ራይስ በቀድሞዉ የፀጥታ አማካሪ አንቶኒ ሌክ ተተክተዉ ከአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ጋር የራይስንና የካጋሚን ሀሳብን አዳብረዉ በ1991 ያቀረቡትን የሠላም ሀሳብም ኢትዮጵያ ሥትቀበለዉ ኤርትራ ዉድቅ አደረገችዉ።

የተፈረዉ አልቀረም።

ባድመና አካባቢዋ ትነድ ገባች።አስገራሚዉ ሠፊ፣ ፈጣን ግን ዘግናኝ ጦርነት በትንሽ ግምንት ሰባ ሺሕ ሕይወት ፈጀ።የመቶ ሺዎችን አካል አጎደለ።ሰባ አምስት ከመቶ የሚጠጋዉ የኤርትራዊ፣ የኤርትራን አጠቃላይ ሕዝብ በቁጥር የሚያጥፈዉ ኢትዮጵያዊም ለዕለት ጉርሱ የዉጪ ርዳታ ተመፅዋች ነዉ።በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የሁለቱ ሐገር ሕዝብ በኤች አይ ቪ-ኤድስ፣ በሳንባ ነቀርሳ፣ በወባና በሌሎች ተዛማች በሽቶች ከመለቅ የሚድንበት መታከሚያ-መድሐኒትም የለዉም።ንፁሕ የመጠጥ ዉሐ አያገኝም።ወጣቱ ሥራ የለዉም።ያለዉም እራሱን ከነቤተሰቡ መቀለብ የሚችል ገቢ አያገኝም።ከአለም ድሆች ከመጨረሻዉ ጠገግ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ሐገሮች ወትሮም ያጣ-የገጠጠዉን አዋሳኝ ድንበራቸዉን በጥይት-ቦምብ አረር አጋዩት።አወደሙት።

ከየሕዝቡ ጉሮሮ እየተነጠቀ ለጦር መሳሪያ መግዢያና ለጦር ሐይል የሚወጣዉ ገንዘብ በቀን እስከ አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሶ ነበር።ጦርነቱ ያፈነቃለ፣ ያሰደደ፣ ካንዱ ወደሌላዉ ያስጋዘዉ ሕዝብ- ቤት፣ ሐብት፣ ንብረት፣ ሥራዉን በማጣቱ የደረሰበትን «የማይደማ» ቁስል ሥቃይ እንደሱ ያልቆሰለ በርግጥ በትክክል አያዉቀዉም።

ዘግናኙ ጦርነት ከፈነዳ በሕዋላ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና የመን የኤርትራ ብሔራዊ ሐይላት ሕብረት የተባለዉን የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ ሐይል ይደግፋሉ።ኢትዮጵያ ለብቻዋ ሌሎች ቡድናትን ትረዳለች ነዉ-የሚባል።ኤርትራ ባንፃሩ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ድርጅትንና ሌሎች የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ሐይላትን ትረዳለች።ኢትዮጵያ ትቃወመዉ የነበረዉን የቀድሞዉን የሶማሊያ የሽግግር ብሔራዊ መንግስት ኤርትራ ግብፅና ጅቡቲን ተከትላ ትደግፍ ነበር።ሱዳን የኤርትራ እስላማዊ ጅሐድ አባላትን ታደራጃለች።ኤርትራ የቤጃ ኮንግረስና የሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ የተባሉትን የምሥራቅና ምዕራብ (ዳርፉር) ሱዳን አማፂያንን ትረዳለች።የሱዳን ዴሞክራሲያዊ ሐይላት ቅንጅት የተበለዉን ስብስብ ኤርትራ ታደራጃለች።ዩጋንዳ የቅንጅቱን ዋነኛ አባል የሱዳን ሕዝብ ነፃ አዉጪ ጦርን ትረዳለች።ሱዳን ሎርድ ሪዚስታንስ አርሚ የተባለዉን የዩጋንዳ አማፂ ሐይል ትደግፋለች።

ጥልፍልፉ ያስገርማል።ያሳዝናልም።

አዉዳሚዉ ጦርነት ማንም ሳይጠብቀዉ መጫሩ እንዳስገረመ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥት «ሉዓላዊ ግዛቴ» ሲለዉ የነበረዉን ግዛት በሐይል ማስመለሱን ባወጀ ማግሥት ለዚያዉ ግዛት ባለቤትነት የፍርድ ቤት እሰጥ-አገባ ለመግጠም መስማማቱ ለብዙዉ ኢትዮጵያዊ ዱብ ዕዳ ነበር።የፍርድ ቤቱ ሙግት ካልቀረ ጦርነቱ በዚያ ስፋትና ፍጥነት ለዚያ ዘግናኝ ዉጤት የመቀጠሉ አስፈላጊነት ለተሸከመዉ መብራራት ነበረበት።

አልጀርስ-አልጄሪያ ላይ በተፈረመዉ ዉል መሠረት የተሰየመዉ የድንበር ኮሚሽን ብይን ሚያዚያ 1994 እንደተሰማ የዉሳኔዉ እንዴትነት ሳይጠና ሕዝብ ለድል ብስራት አደባባይ የተጠራበት ምክንያት እንደ ጦርነቱ፣ እንደ ስምምነቱ ምክንያት ሁሉ እስከዛሬም ግራ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፉት ሁለት አመታት ተኩል ሲያጣጥለዉ የነበረዉን ዉሳኔ ባለፈዉ ሐሙስ «በመርሕ ደረጃ» ከሚል ቅፅል ጋር መቀበሉ ደግሞ ቢያንስ ለአብዛኛዉ ባለጉዳይ ድንገቴ ነዉ።አደናጋሪም።

ለጦርነቱ፣ ለፍርድ ቤት ሙግቱ፣ ለሙግቱ ዉጤት ድሉ፣ ለበቀደሙ የአቋም ለዉጥም፣ በቂ ምናልባት አሳማኝ ምክንያት የለም ብሎ መደምደም «የዋሕ» ያሰኝ ይሆናል።የየርምጃ-ዉሳኔዉን ምክንያት ለሚመሩት ሕዝብ ይሕ ቢቀር ባንድ ወይም በሌላ በኩል ሕዝብን እንወክላለን ለሚሉ ሐይላት፣ ጉዳዩን የማስተንተን አቅም እዉቀቱ ላላቸዉ ወገኖች አለማቅረብን ግን በቀላል የሚወገድ ቅራኔን ከማስፋት፣ ጥርጣሬን ከማጉላት በላይ የተከረዉ ነገር የለም።

ለሠላም ፣ልማት፣ ብልፅግና የሚከፈል ቤዛ መኖሩን ሥለሠላም፣ ልማትና ብልፅግና ፋይዳ የሚያዉቅ ሁሉ ያዉቀዋል።ከጦርነት ዑደት፣ ከድሕነት እሽክርክሪት፣ ከረሐብ-በሽታ አዙሪት ወጥቶ የማያዉቀዉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ለሠላም ልማቱ ጊዜዉ የሚጠይቀዉን ዋጋ ለመክፈል እንደማያመነታ መሪዎቹ፣ ፖለቲከኞቹ፣ ሙሁራኑ አያዉቁትም ማለት ታላቅ ሥሕተት ነዉ።

ጠቅላይ ሚንስትር መለሥ ዜናዉ ባለፈዉ ሐሙስ ለምክር ቤት እንደራሴዎች እንደነገሩት መንግሥታቸዉ የድንበር ኮሚሽኑ ዉሳኔ ኢፍትሐዊ መሆኑን እያወቀ የተቀበለዉ ለሠላምና ልማት ሲል ነዉ።የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ግን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የአቋም ለዉጡን ምክንያቱንም አልተቀበሉትም።አንዳድ ፖለቲከኞችና በርካታ ኢትዮጵያዉያን ደግሞ እቅዱን ሉዓላዊነትን ለማስከበር የተከፈለዉን መስዋዕትነት ገደል እንደከተተ እርምጃ ነዉ ያዩት።እቅዱም አልተብራራ።

የተቃዉሞዉ ምክንያት የሠላም ጥላቻ ነዉ ብሎ ማሰብ ጅልነት ነዉ።ለመቃወም ሲባል መቃወምም ሊሆን አይችልም።የእቅዱን ምክንያት-እንዴትነቱንም መንግሥት ቢያስረዳ ቢያስተች ፣ቢያስተነትንም ተቃዉሞዉን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ይቻላል ማለትም ሞኝነት ነዉ።በምንም መንገድ ግን ለሚመሩት ሕዝብ፣ የሚሰሩትን በተለይ ሥሱ ጉዳዮችን አስረድቶ የዉይይት፣ክርክር፣ ትችት ዉጤትን የመሸሸን፣ የአብዛኛ ሕዝብን እምነት አለመቀበልን ያሕል ሞኝነት ሊሆን አይችልም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሐሙስ ያወጀዉ እቅድ የብሪታንያና የጀርመን መንግሥታት እንዳሉት ለተዳፈነዉ የሠላም ሒደት ነብስ የሚዘራ ነዉ።የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ መርሕ የበላይ ሐቪየር ሶላና እንሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዉሳኔ ድንበር የማካለሉን ስራ፣ በዉጤቱም የታጎለዉን የሠላም ሒደት ለመቀጠል ተስፋ የሚያጭር ነዉ።

ላለፉት ሁለት አመታት ተኩል የድንበር ኮሚሽንኑን ዉሳኔ ገቢር ከማድረግ በመለስ ሌላ አማራጭን በሙሉ ስትገፋ የቆየችዉ ኤርትራ ግን የኢትዮጵያን የአቋም ለዉጥ እንደዲፕሎማሲዉ ወግ መሸንገሉን እንኳን አልፈቀደችዉም።የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አልፋ ኡመር ኮናሪ ከጦርነቱ ምክንያት ይልቅ መዘዙ ያሳሰባቸዉ ነዉ የመሠሉት።«በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሌላ ጦርነት ቢነሳ ለአፍሪቃ ታላቅ ድቀት ይሆን ነበር---» አሉ ኮናሪ በቃል አቀባያቸዉ በኩል።ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽንኑ ዉሳኔ «በመርሕ ደረጃ» መቀበልዋን ያወጀችበትን ቀን ደግሞ ኮናሬ «ለአፍሪቃ ታላቅ ዕለት» ብለዉታል።

የኢትዮጵያ የአቋም ለዉጥ ለዉጪዎቹ እንደገባ ሁሉ ለተቃዋሚዎች በተለይ ለሕዝቡ ቢገባ ጥሩ ነበር።ለዉጡ ተፋላሚ ሐይላትን፤ የሁለቱን ሕዝቦች የሚያረካ ሠላም ካሰፈነ ቢያንስ ለአፍሪቃ ቀንድ ኮናሪ እንዳሉት ታላቅ ቀን በሆነም ነበር።አልሆነም።ዕቅዱ አልተብራራም።ኤርትራም «የሕዝብ ግንኙነት ማስተዋዋቂያ-ጊዜ መግዢያ በማለት ነዉ ያጣጣለችዉ።»

እና ባድመ ላይ ሠላም የለም።ጦርነትም ቆሟል።