ባዮ-ኤነርጂ፤ የምግብ መወደድና የረሃብ መዘዙ | ኤኮኖሚ | DW | 14.11.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ባዮ-ኤነርጂ፤ የምግብ መወደድና የረሃብ መዘዙ

የሰውልጅ ለኑሮ የሚያስፈልገውን በቂ ምግብ የማግንት መሠረታዊ መብት አለው። የዚህ ሰብዓዊ መብት ክቡርነት ለአያሌ ዓመታት ሲነገርለት የቆየ ነው። ይሁን እንጂ ዛሬም በዓለም ላይ ለዚህ መብት ያልበቃው ረሃብተኛ ሕዝብ 900 ሚሊዮን ገደማ ይጠጋል።

ታዲያ ይህን ያህል ሰፊ ሕዝብ መቀለብ ባልተቻለበት በዛሬው ጊዜ እህልና ሌሎች ተክሎችን ለባዮ-ኤነርጂ ምርት የመጠቀሙ ሂደት የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባዔ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ እንዳመለከተው ሁኔታውን እያባባሰው ነው፤ ለምግብ ዋጋ መናርም ምክንያት መሆን ይዟል። የድርጅቱ “የምግብ መብት” ተከራካሪ ዣን ሢግለር ባለፈው ሣምንት በድርጅቱ ጠቅላይ ጉባዔ ላይ ለተሳተፉ ልዑካን ባሰሙት ንግግር የእርሻ መሬትን ባዮ-ኤነርጂን ለማግኘት የሚቃጠል እህል ማምረቻ አድርጎ የመለወጡን ሂደት በስብዕና ላይ ወንጀል መፈጸም ነው ብለውታል።

በእርግጥም ይህ ድንገት የተከሰተ ለውጥ ረሃብን ይበልጥ በማስፋፋት የጥፋት ምክንያት እንዳይሆን እንደ ሢግለር የሚሰጉት ዛሬ ጥቂቶች አይደሉም። ሁኔታው ለምግብ ዋጋ መናር፣ ለውሃና ለመሬት እጥረትም ምክንያት ነው የሆነው። ባለሥልጣኑ ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላይ ጉባዔ ባቀረቡት 23 ገጾችን ያቀፈ ዘገባ የድርጅቱ 192 ዓባል ሃገራት ምግብን ወደዚሁ ኤነርጂ የመለወጡን ማንኛውንም ጥረት የሚገታ የአምሥት ዓመት የጊዜ ገደብ እንዲያሰፍኑ ነው ጥሪ ያደረጉት። ይህ ሂደት ጉዳዩ በምግብ ማግኘት መብት፣ ከዚያም ባሻገር በሌሎች ማሕበራዊ፣ የተፈጥሮ ይዞታና በሰብዓዊ መብት ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ መጠን ለመገምገም፤ በአጠቃላይ ሁኔታው ረሃብን አለማስከተሉን ለማረጋገጥ ፋታ ይሰጣል ባይ ናቸው።

ለነገሩ በዓለም ላይ የብዙዎች አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት መፋጠን የኤነርጂ ፍጆቱንም በፍጥነት ከፍ እያደረገው መምጣቱ የተሰወረ አይደለም። የነዳጅ ዘይት ዋጋም ዛሬ ከዚህ ቀደም በማይታወቅ መጠን ወደ ላይ እየተተኮሰ በመሄድ ላይ ነው። ይህም ታዲያ የአማራጭ ኤነርጂን ፍላጎት ማጠናከሩ አልቀረም። ይሁን እንጂ ባዮ-ኤነርጂን ለማምረት የሚያስችሉ ሌሎች ምንጮች አልታጡም። አሉ። ለምሳሌ ምግብነት ከሌላቸው ወይም ለምግብ ፍጆት ከማይውሉ ተክሎች፣ ከእንክርዳዱና ከእርሻ ቆሻሾች ሊመረት ይችላል።
በዓለም ላይ ያለማቋረጥ በማደግ ላይ ከሚገኘው ረሃብ አንጻር እንግዲህ የእርሻ ምርትን የሚሻማው ኤነርጂ ተገቢው አማራጭ ሊሆን አይችልም። በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት በረሃብ የሚሰቃየው የዓለም ሕዝብ ቁጥር ባለፉት አሥር ዓመታት ያለማቋረጥ እያደገ ሲመጣ ዛሬ 900 ሚሊዮን ገደማ ተጠግቷል። መንግሥታት እ.ጎ.አ. በ 1996 ዓ.ም. የመጀመሪያ የዓለም የምግብ ዓቢይ ስብሰባ፤ ከዚያም እንደገና በኒውዮርኩ የሚሌኒዬም ጉባዔ ረሃብን ለመቀነስ የገቡት ቃል የረባ ዕርምጃ አላሣየም። ይህ ደግሞ በቀላሉ የሚዋጥ ነገር አይደለም።

መላው የሰውልጅ ከረሃብ ተላቆ በክብር መኖር መቻል አለበት፤ በቂ ምግብ ማግኘት ሰብዓዊ መብት ነው የሚለውን የዓለም ሕብረተሰብን የራሱን መርሆ የሚጻረር ነው። መብቱ ገቢር አለመሆኑ በተለይ በአፍሪቃ ላይ በማያሻማ ሁኔታ ይከሰታል። ሮማ ላይ ተቀማጭ የሆነው የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት FAO እንደሚለው በምድራችን ዙሪያ ዛሬ 34 አገሮች በምግብ እጥረት ቀውስ ተወጥረው ይገኛሉ። ከነዚሁ ብዙሃኑም ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች ናቸው። የችግሩን አስከፊነት ይበልጥ አጉልቶ የሚያሣየው ደግሞ ለምሳሌ የድሃ-ድሃ የተባሉ የ 14 አገሮች ሁኔታ ነው።

እነዚሁ በእርስበርስ ግጭቶች የተጠመዱ ወይም ተጠምደው የነበሩ፤ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎን፣ ቡሩንዲን፣ ላይቤሪያንና ሢየራሌዎንን የመሳሰሉትን አገሮች ይጠቀልላሉ፤ ከ 35 በመቶ በላይ የሚሆን ሕዝባቸው ሌላው ቀርቶ ድርቅ በሌለበት ጊዜ እንኳ ሳይቋረጥ የዕለት-ከዕለት ረሃብተኛ ነው። እርግጥ በምግብ ዋስትና ላይ አደጋ ደቅነው የሚገኙት ምክንያቶች ብዙዎች ናቸው። የፋኦ ጠቅላይ አስተዳዳሪ ዣክ ዲዮፍ እንደሚሉት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጡ ከባዮ-ኤነርጂ ፍላጎት መጨመር ባሻገር በአካባቢ አየር ለውጥ፣ በምርታማነት ማነስና በገበያ እጦት ጭምር ነው አስቸጋሪ የሆነው።

ዲዮፍ የሁኔታውን አሳሳቢነት ሲናገሩ የምግብ ዋጋ መናር ባለበት ከቀጠለ በሜክሢኮ፣ በየመንና በቦርኪና ፋሶ እንደታየው የምግብ ዓመጽ ቢነሣ አልደነቅም ነው ያሉት። በዕውነትም የእህል አዝመራ በሕዝብ ፈንታ አውቶሞቢሎችን ለመቀለብ ግልጋሎት ላይ ከዋለ ወሰን ሣይለይ የገበያ እጥረትን፤ እንዲያም ሲል የዋጋ ንረትን የከፋ ማድረጉና ሕብረተሰባዊ ነውጽን መቀስቀሱ የሚቀር አይመስልም። በሜክሢኮ የ 2006 የቶርቶልያ ተቃውሞ መንስዔ ለምሳሌ በቆሎን በመሰለው የሕዝቡ መሠረታዊ ቀለብ ላይ የተከተለው የዋጋ መናር ለብዙዎች የሚገፋ አለመሆን ነበር። እንግዲህ ምሳሌ አልጠፋም። ምን ክብደት አግኝታል ነው ጥያቄው።

ያም ሆነ ይህ ቢቀር የአሜሪካ ልምድ እንደሚያሣየው የባዮ-ኤነርጂ ምርት ወደፊትም በእርሻው ምድርና የምርት ምንጮች ላይ ተጽዕኖው ጸንቶ የሚቀጥል ነው የሚመስለው። የአገሪቱ መንግሥት ለዚሁ የኤነርጂ ምርት በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ድጎማ ከማድረጉም በላይ በሚቀጥለው የእርሻ ሕግ እንዲያውም በጀቱን እንደሚጨምር ነው የሚታመነው። ይህ ደግሞ ከአሜሪካ የምግብ ዕርዳታ የሚያገኙትን አገሮች ሁኔታ ይብስ የከበደ ያደርገዋል። ዋሺንግተን ይህን ዕርዳታዋን በገንዘብ ሣይሆን በቀጥታ በምርት የምታቀርብ በመሆኑ በአገሪቱ የባዮ-ኤነርጂ ምርት መጨመሩ የወደፊት አስተዋጽኦዋን የሚቀንስ ነው የሚሆነው።

ተዛማጅ ዘገባዎች