ባንክና ቴሌኮም ለውጭ ባለወረቶች ክፍት አይሆኑም | ኤኮኖሚ | DW | 25.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ባንክና ቴሌኮም ለውጭ ባለወረቶች ክፍት አይሆኑም

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ የሚከታተሉ ምን አይነት ለውጥ እንደሚመጣ ሲጠብቁ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ ነጋዴዎች የግሉ ዘርፍ በገበያው ውስጥ ያለው ሚና እንዲጠናከር ይሻሉ።በአንፃሩ የኢትዮጵያ መንግሥት በብቸኝነት የተቆጣጠራቸው የሥራ ዘርፎች ለውጭ ባለወረቶች ይከፈቱ እንደሁ ብለው የጠበቁም አልጠፉም

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:21

መንግሥት በኤኮኖሚው ውስጥ ያለው ሚና አይቀየርም

የኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ሚያዝያ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶ ነበሩ። ፕሬዝዳንቱ ከፖላንዱ አቻቸው አንድሬ ዱዳ ጋር በጥምረት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አገራቸው በማምረቻው ዘርፍ ለሚሰማሩ የውጭ ባለወረቶች በሯ ክፍት መሆኑን ተናግረዋል። ጨርቃ ጨርቅ፤ የቆዳ ውጤቶች፤ መድሐኒቶች ማምረት፣ የምግብ ማቀነባበሪያ ማቋቋም ያቀዱ ወደ ኢትዮጵያ ብቅ እንዲሉ ግብዣም አቅርበዋል።

ከጋዜጠኞች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ግን ለውጭ ባለወረቶች ተዘግተው የቆዩትን የፋይናንስ እና የቴሌኮም አገልግሎት ዘርፎች ይመለከታል። ፕሬዝዳንቱ ሙላቱ በሰጡት ምላሽ ታዲያ አገሪቱ ባለፉት ዓመታት በእነዚህ ዘርፎች በተከተለችው ፖሊሲ የተለወጠ ነገር አለመኖሩን የሚጠቁም ነበር።  «ኢትዮጵያ ክፍት አይደለችም ይሕን ጥያቄ ያነሳዉ ጋዜጠኛ ሥለኢትዮጵያ የመዋዕለ ንዋይ መርሕ ብዙ የሚያዉቅ ይመስለኛል።ለጊዜዉ ኢትዮጵያ በቴሌኮሙኒኬሽን እና በገንዘብ መስክ የግል ባለሐብቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ አይደለችም።በገንዘብ መስክ የግል ባለሐብቶች መካፈል ይችላሉ።ግን የሐገር ዉስጥ ባለሐብቶች ብቻ ናቸዉ።የዉጪዎች አይደሉም።ለሐገር ዉስጥ  ባለሐብቶች ብቻ የተፈቀደ ነዉ» ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በአፅንዖት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን የሥራ ዘርፎች ለውጭ ባለወረቶች ለመፍቀድ ዝግጁ አለመሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል። ከተከታታይ ተቃውሞዎች በኋላ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሔደው በአቶ አብይ አሕመድ መተካታቸው ግን በመንግሥቱ ዘንድ የአቋም ለውጥ ሊኖር ይችላል የሚል ግምት ሳያሳድር አልቀረም። አይ.ኤች.ኤስ ማርኪት በተባለው ኩባንያ የኤኮኖሚ እና የአገሮች የሥጋት ትንታኔ ባለሙያው ክሪስቶፈር ሰኪሊንግ ያን ተስፋ አሳድረው ከነበሩ መካከል አንዱ ናቸው። "ኤሌክትሪክ የማመንጨትን የመሳሰሉ እና በመንግሥት እጅ ብቻ የሚገኙ የሥራ ዘርፎች ለውጭ ባለወረቶች ክፍት መሆን ጀምረዋል። በተጨማሪም የመሠረተ-ልማት ግንባታው እንደቀጠለ ነው። እንደ ቴሌኮምዩንኬሽን እና የባንክ አገልግሎት የመሳሰሉትም ክፍት ይሆናሉ ብለን እየጠበቅን እንገኛለን" ይላሉ ባለሙያው። 

የክሪስቶፈር ሰኪሊንግ ግምት አልያዘም። ነገር ግን የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅትን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና እንደ ክሪስቶፈር ሰኪሊንግ ያሉ የምጣኔ ሐብት ተንታኞች ኢትዮጵያ ሁለቱን ዘርፎች በተለይ ለውጭ ባለወረቶች ትከፍት ዘንድ መወትወት ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል። ወደ አዲስ አበባ ብቅ ብለው የነበሩት የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ የኢትዮጵያ መንግሥት በብቸኝነት የተቆጣጠራቸውን የሥራ ዘርፎች ለባለወረቶች እንዲፈቅድ ጠይቀው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ጋር «በቅርብ ጊዜ መንግሥት በኤኮኖሚው ውስጥ ያለው ሚና እንዲለወጥ» ሊጠበቅ እንደማይገባ መናገራቸውን የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም ያስታውሳሉ። የኤኮኖሚ ባለሙያው እንደሚሉት መንግሥት የቴሌኮም እና የፋይናንስ ዘርፎች ያላቸውን ሚና እና ተመሳሳይ አገልግሎት የሚያቀርቡ የኢትዮጵያ ተቋማት የመወዳደር አቅምን በማገናዘብ ዘርፉን ለውጭ ባለወረቶች ክፍት ከማድረግ መታቀቡን ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም አገሪቱ ለዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ባቀረበችው ማመልከቻ ላይ ጭምር ተፅዕኖ አሳድሯል። ቢኬፒ የተሰኘው የእድገት ጥናት እና አማካሪ ተቋም መስራች የሆኑት ዶክተር ዴርክ ቢይነን ከዚህ ቀደም ለዶይቼ ቬለ ሲናገሩ ኢትዮጵያ ሁለቱን የሥራ ዘርፎች ለውጭ ባለወረቶች ትክፈት የሚል ጠንካራ ሙግት መኖሩን ጠቁመው ነበር።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic