«ባሩድና ብርጉድ» የሥነ-ጥበብ ትርዒት | ባህል | DW | 25.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

«ባሩድና ብርጉድ» የሥነ-ጥበብ ትርዒት

«ኤግዚቢሽኑ በሰዉ ልጅ አካልና በሚለብሰዉ ጨርቅ ሲኖርም ሲሞትም፤ የሰዉ ልጅ አካል በጨርቅ ይጠቀለላል። አንድ ሰዉ አጥቶም ይሁን አግኝቶም፤ ከብሮም iይሁን ከስሮ ፤ ተቀጥሮም ሕጻንም ሆኖ፤ ሞቶ ይሁን ተኝቶ ሁል ጊዜም ጨርቅን ይለብሳል። በዝያ ጨርቅ የተነሳም የለበሰዉም ይሁን ተመልካቹ ሰዉ ስለሰዉየዉ ማንነትና ምንነት፤ በጣም ግራ ይጋባል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:37

በአለባበሱ የሰዉን ልጅ ማንነት በርግጥ ማወቅ ይቻላል?

የሰው ልጅ በዚህ ዓለም ቆይታውና ሁዋላም በስንብቱ ሰዓት ሳይቀር ገላውን በጨርቅ ወይም በቆዳ መሸፈን ነባርና እስካለንበት ዘመን አብሮት የኖረ ባህሉ ነው። በሰው ልጅና በሚለብሰው ልብስ መካከል ያለው አስገራሚ ግንኙነት እኔንም እንደሌላው ሰው ሁሉ ያስደንቀኝ ፤ ያሳስበኝም ነበር። በተለይ ባለፉት አምስት ያህል ዓመታት ውስጥ ይሁነኝ ብዬ ከዕለት ተዕለት አጋጣሚና ከተራ ጨዋታ ባለፈ ሰውና ልብሱን ወይም አለባበሱን በሚመለከት በበርካታ ጥናቶች ውስጥ የተመዘገቡ አያሌ አስገራሚ ታሪኮችን ለመመልከት ሞክሪያለሁ። የሰው ልጅና የልብሱ ጉዳይ እስከዛሬ ከማውቀውና ከምገምተው በላይ ኃይማኖታዊ ፤ሥነ-ልቦናዊ፤ ፆታዊ፤ ሕጋዊ ታሪካዊና ሌሎችንም ብዙ ብዙ ጉዳዮችን የሚያጣቅስ ምስጢራዊ የግንኙነት መስመር መሆኑን አረጋገጥኩ ። ይላል እፍኝ አሳብ ስለ «ባሩድና ብርጉድ» ብሎ አዲስ አበባ ከተማ ላይ የሥነ -ጥበብ ትርኢቱን ለእይታ ያቀረበዉ የሥነ- ጥበብ መምህሩ ተባባሪ ፕሮፊሰር በቀለ መኮንን።

 በእለቱ ዝግጅታችን «ባሩድና ብርጉድ» የተሰኘዉን የሥነ ጥበብ ትርኢት በምናባችን የሚያስቃኙንን ባለሞያዎች አነጋግረን ቅንብር ይዘናል።   

«ባሩድና ብርጉድ» በሚል ርዕስ አዲስ አበባ እንብርት ላይ በሚገኘዉ በዘመናዊ የሥነ-ጥበብ ቤተ-መዘክር በገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከል የሚገኘዉን ትርዒት አርብ ታህሳስ 27 ቀን መርቀዉ የከፈቱት የባህል ቱሪዝም ሚኒስትር  ዶ/ር ሂሩት ወልደ ማርያም ናቸዉ። በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ቫግነርን ጨምሮ በመዲናዋ የሚገኙ የተለያዩ ዴፕሎማቶች በከተማዋ አሉ የተባሉ በርካታ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች እንደተገኙበት የተነገረዉ ይህ የሥነ-ጥበብ ኤግዚቢሽን እስከዛሬ ከታዩት በይዘቱ የተለየ እንደሆነ ነዉ የተመለከተዉ። ከትርኢቱ ስያሜ ስንነሳ «ባሩድና ብርጉድ» ማለት ምን ማለት ይሆን ? የኤግዚቢሽኑ አዘጋጅ የሥነ ጥበብ መምህሩ ተባባሪ ፕሮፊሰር በቀለ መኮንን እንዲህ ይዘረዝራል።  

«ባሩድ የጦር መሳርያ አረር እሳቱን የሚያቀጣጥለዉ ሲሆን ፤ ብርጉድ ደግሞ የእጣን ዓይነት ነዉ። የሁለቱንም ዉጤት ነዉ ለማሳየት የሞከርኩት። ሁለቱም ነገሮች ደግሞ ተመሳሳይ ናቸዉ ። ሁለቱም ይጨሳሉ። አመድ እና ዱቄት እንደማለት ነዉ።  አመድ እና ዱቄት ሲታዩ ሁለቱም ነጫጮች ናቸw፤ ነገር ግን ዱቄቱ ሕይወት ያለዉ ሲሆን አመድ ደግሞ ያበቃለት ነዉ። አንዱ የተናቀ አንዱ የሚከበር አይነት ማለት ነዉ ልክ እንደዚህ ሁሉ ብርጉድ ጢስ አለዉ፤

ባሩድም ጢስ አለዉ ሁለቱም ሲጨሱ የትኛዉ ኩነኔ የትኛዉ የፅድቅ እንደሆነ ግን አናዉቅም።  

ዓዉደ ርዕዩ  ከሰዉ ልጅ የተለያየ አልባሳት ጋር ተያያዥነት እንዳለዉ ተመልክቶአል። ኤግዚቢሽኑ ይህንን ስያሜ ለምን ተሰጠዉ ይሆን ?  ሰዓሊ በቀለ መኮንን እንዲህ ይመልሳል። 

«ኤግዚቢሽኑ በሰዉ ልጅ አካልና በሚለብሰዉ ጨርቅ ሲኖርም ሲሞትም፤ የሰዉ ልጅ አካል በጨርቅ ይጠቀለላል። አንድ ሰዉ አጥቶም ይሁን አግኝቶም፤ ከብሮም iይሁን ከስሮ ፤ ተቀጥሮም ሕጻንም ሆኖ፤ ሞቶ ይሁን ተኝቶ ሁል ጊዜም ጨርቅን ይለብሳል። በዝያ ጨርቅ የተነሳም የለበሰዉም ይሁን ተመልካቹ ሰዉ ስለሰዉየዉ ማንነትና ምንነት፤ በጣም ይወናበዳል። ለሚያየዉም የለበሰዉም ተመልካቹም ማለት ነዉ።  እንደ ጨርቁም ዓይነት ባህሪዉም ከዉስጥ ይለወጣል። ትሁት ትቢተኛ ፤በራሱ የሚተማመን ወይም የማይተማመን ሆኖ ባህሪዉ ይለዋወጣል። የምንመለከተዉም ሰዎች ስለዛ ሰዉ፤ በጨርቅ ስለተጠቀለለዉ ሰዉ ማንነት ያለን አስተሳሰብ ይለያያል። ወይ እንፈራዋለን ወይ እንሰግድለታለን፤ እንበረከክለታለን ወይ እናፈቅረዋለን፤ እንሸሸዋለን አልያም እንጠላዋለን፤ ወይም የነዚህ ነገሮች ሁሉ ድብልቅ ይሆናል። በዚህm የሰዉ ልጅ በሚጠቀለልበት ጨርቅ የተነሳ ስለዛ ሰዉ ያለዉ አስተሳሰብ የተዛባ እንደሆን በለባሹም ሆነ በተመልካቹ ዘንድ ያለዉን ነገር የሚያሳይ የሚመረምር ተመልካቹንም የሚጠይቅ አይነት ትርዒት ነዉ። ርዕሱም ለዚህ ዓይነቱ ኤግዚቢሽን በጣም የተስማማ ነዉ።»

እንደ ሰዓሊ በቀለ መኮንን የሰውን ገላ በጨርቅ ወይም በቆዳ፡ መሸፈን ከጥንታዊ ግልጋሎቱ፤ ከብርድ ከተባይና፡ ከዓይን መከላከያነት ያለፈ ተግባር እንዳለው ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ይጠቁማል።

የሰው ገላ፡ በሚሸፈነው ጨርቅ የተነሳ በለባሹም በተመልካቹም አስተሳሰብ ላይ ብርቱ ተፅዕኖ ስለመፍጠሩ ያለተጨማሪ ጥናት በመኖር ብቻ፡ እንኩዋ የምናውቀው ልምድ ነው ። የገላ መሸፈኛ ጨርቅ በቀለም ምርጫው፤ በአሰፋፉ ዘይቤ፤ በንፅህናው ፤ በዕድሜው ፤በጌጣጌጡ  በመሳሰሉት ሁሉ፤ልብሱን ያደረገዉ ሰዉ ልብ ውስጥ ድፍረትን ወይም ስጋትን፤ በራስ መተማመንን ወይም በራስ ማፈርን፤ ትህትናን ወይም ዕብሪትን ፤ ትዕግስትን ወይም ብስጭትን እንደ የባህርያቸው ለማቀጣጠል ልብስ ብርቱ ምክንያት ሊሆን አንደሚችል ብዙ ማረጋገጫዎች ተፅፈው እንደሚገኙ ሰዓሊዉ በትርኢቱ መክፈቻ ተናግሮአል። አንድ ሰዉ የለበሰዉ ልብስ በተመልካቹ ዘንድ ስለሚፈጥረው የአስተሳሰብ ተፅዕኖ ደግሞ ከሰርክ ኑሮአችን የምናውቀው ፤ ለመከበርና ለመመረጥ ወይም ለመናቅና ለመረሳት፡ ሰበብ ሲሆን መሆኑንም አመላክቶአል።  ሊቃውንት በጥናት ያረጋገጡት ደግሞ ከዚህም የራቀ እውነት አለ ። የሰው ልጅ ለገላ መሸፈኛ የለበሰው ጨርቅ በፍርድ ደጃፍ ሳይቀር ፍትህ እስኪዛባ በፈራጆች ዓይንና፡ አይምሮ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ መኖሩን ገልፆአል። ይህንን እውነት መስማት ስለ ገላ መሸፈኛ ጨርቅ ከዚህ ቀደም የነበረንን ዋዘኛ ግምት መለወጡ አይቀርም። ባጠቃላይም በየዘመኑ አየተራቀቀ የመጣው የሰው ልጅ ገላን የመሸፈን ባህል በራሱ ትልቅ የጥናትና የማሰላሰያ ርዕሰ - ጉዳይ መሆኑን የሥነጥበብ መምሕሩ ተባባሪ ፕሮፊሰር በቀለ መኮንን ገልፆአል።

የሥነ-ጥበብ ባለሞያዉን ይህን ኤግዚቢሽኑን ከማንሳታችን በፊት ቀደም ያሉ ሥራዎቹንም ልናይ ይገባል  ያሉት በትርዒቱ የተደመሙት ረዳት ፕሮፌሰር እና ሰዓሊ ብርኃኑ አሻግሬ በበኩላቸዉ ሰዓሊ በቀለ እስከዛሬ ያቀረባቸዉ ኤግዚቢሽኖች ሁለት የተለያዩ ተፃራሪ ነገሮችን በማነፃፀር ያሳየበት ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።

ሰዓሊ ያሉት እዮብ ኪታባ «ባሩድን ብርጉድ» ኤግዚብሽን ነገሮች የሚታዩበት ብቻ ሳይሆን ተመልካቹ የተለያዩ ኃሳቦችን እያሰበ የተለያዩ ጥያቄዎችን እንዲያነሳ  የሚጋብዝ ፤ ሞጋች ዓዉደ ርዕይ ነዉ፤ ብለዉታል።  

ሶቭየት ኅብረት በተከፋፈለበትና የቀዝቃዛዉ ጦርነት ለዉጥ በመጣበት በሰማንያዎቹ አጋማሽ በሞስኮ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ዲግሪዉን የያዘዉና በዘጠናዎቹ መጀመርያ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰዉ ረዳት ፕሮፊሰር በቀለ መኮንን፤ በሩስያ የዓለም ርዕዮት ሽግግር ፤ የማኅበራዊ ኑሮ ሽግግር በነበረበት ወቅት ብዙ እንዳየ ብዙ ትምህርትም እንደቀሰመ የለዉጡ ምስክርም የለዉጡ ተሳታፊም እንደነበር ተናግሮአል። ኢትዮጵያ ወጣትበርካታ የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎችን አፍርታለች ያለዉ ሰዓሊ በቀለ መኮንን እንዲያም ሆኖ ሥነ -ጥበብ እንዲጎለብት የሚደረግ ይህ ነዉ የሚባል ጥረት እንደሌለ ሳይገልፅ አላለፈም። 

«ባሩድና ብርጉድ» በሚል ርዕስ አዲስ አበባ ከሚገኘዉ ከጀርመኑ የጎተ ተቋም ትብብር ጋር በዘመናዊ የሥነ-ጥበብ ቤተ-መዘክር በገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከል ታህሳስ 27 የጀመረዉ ዓዉደ ርዕይ እስከ ጥር 23 ድረስ ለተመልካች ክፍት እንደሚሆን ተመልክቶአል ። አድማጮች ቃለ ምልልስ የሰጡንን በዶይቼ ቬለ ስም እያመሰገንን ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።       

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic