ባህልና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም | ባህል | DW | 30.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ባህልና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም

ሰሞኑን ፌስቡክ 13 ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አስቧል። ፌስቡክ እና ትዊተርን የመሳሰሉ ሌሎች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አገልግሎታቸዉን በማስፋት በመረጃ ፍሰት ዓለምን ጠባብ፤ የመረጃ ልዉዉጡንም ፈጣን አድርገዉታል። ሆኖም በተለይ እንደ ኢትዮጵያዊ ላሉ ሃገሮች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዛኝ ሆኖ ታይቶአል፤ የሚሉ አሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:27

«የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀማችንን ማጤን ይጠበቅብናል»

 

ስለፌስቡክ አጠቃቀም ሲነሳ በቱኒዝያ ያቀጣጠለዉ ሕዝባዊ አብዮት እንዳለ ሆኖ፤ በፌስቡክ ትዉዉቅ፤ በፌስቡክ ንትርክ በፌስቡክ የእንኳን አደረሳችሁ መልክት፤ መለዋወጡን ጨምሮ ፌስቡክ ለቅሶና ሃዘን መድረሻ፤ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት መቀባበያ መድረክም ሆኖ ይታያል። የዛኑ ያህል የቤት አመል የሚታይበት መድረክም ነዉ ያሉን አሉ። ሌላዉ ደግሞ ፌስቡክን መጠቀም አለመቻላችን ብንጠቀምም በጣም ብዙ ገንዘብ በመክፈላችን፤  አሁን አሁን እኛጋ ፌስቡክን «የፍስክ»  ነዉ የምንለዉ ሲሉም አጫዉተዉናል። የሆነዉ ሆኖ ለዛሬ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም በሰዉ ለሰዉ ግንኙነትና ባህላዊ ትስስር እና መስተጋብር ላይ የሚያሳድረዉን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተግዳሮትን አብረን እናያለን። 

ሰሞኑን ይፋ በሆነ መረጃ የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሪድራ ሞዲ በፌስ ቡክ ገፃቸዉ ላይ 40 ሚሊዮን ተከታዮችን በመያዝ ከፍተኛ ቁጥር ያስመዘገቡ የሃገር መሪ መሆናቸዉ ተነግሮላቸዋል። ከሞዲ በለመጠቅ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶላልድ ትራምፕ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ መረብ በርካታ ተከታዮች ያልዋቸዉ መሪ ሆነዉ ተመዝግበዋል። በመቀጠል የቀድሞዉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም ብዙ ተከታዮች እንዳላቸዉ ተገልጿል። ከአፍሪቃ ሃገራት የግብፁ ፕሬዚዳንት ኧብደል ፈታህ ኧልሲሲ ወደ ሰባት ሚሊዮን ተከታዮች አሏቿዉ።

ፌስቡክ ፤ ትዊተር የመሳሰሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ጥቅምና ጉዳት በተለይ ከባህላዊ ትስስር አንጻር እንዴት ይገልፁታል? ብለን በፌስ ቡክ ድረ-ገፃችን ላስቀመጥነዉ ጥያቄ ማሩ ግዛቸዉ የተባሉ የዶቼ ቬለ የፌስቡክ ተከታይ ባስቀመጡልን አስተያየት በተለይ እንደ ኢትዮጵያዊ ላሉሃገሮች የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዛኝ  ሆኖ አግኝቸዋለሁ ሲሉ ገልፀዋል። «የኢትዮጵያ ሕዝብ ለየት ያለ ያኗኗር ዘዴ ያለው ነው። በሃይማኖት፣ በባህል፣ በውግ፣ በሥነ-ምግባር በአጠቃላይ በሕግ ሳይሆን በልምድ የሚኖር ህዝብ ነው። ለዚህም ነው፤ እነዚህ ዘመኑ ያመጣቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው በዝቶብናል፤ ያልኩት። በማንኛውም መስክ መስማማት ተስኖናል። ለጋራ ችግሮቻችን በጋራ መፍትሄ ማምጣት አልቻልንም። በእርግጥ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት አንጻር የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚን ቁጥር ስናይ ምንም ተጽዕኖ አይፈጥርም ልንል እንችላለን።  ሆኖም ግን ባንዲት ትንሽ ብልቃጥ የተቀመመች መርዝ የአንድን ሀገር ሕዝብ ልታጠፋ እንደምትችል ማውቅ የግድ ይላል። እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ደግሞ አሁን ላለንበት የእርስ በርስ እንዲሁም፣ የዘርና የሃይማኖት ጥላቻ፤ የባህል መጥፋት፤ ነዳጅ ሆነው እያገለገሉ ነው። ሌላው ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የተለያየ ሃይማኖት እንዲኖር ማለትም እናት እና አባት ኦርቶዶክስ ሲሆኑ አንዱ ልጅ ጲንጤ አንደኛው ደግሞ ጆቫ ሌላኛው ደግሞ ሙስሌም ይሆናል። በፖለቲካው ዓለምም ካየነው አንዱ የቤተሰብ አባል ወያኔ ፤ አንደኛው ደግሞ ኢህአፓ ሌላው ደግሞ ኦነግ ይሆናል። ለዚሁ ሁሉ ብዥታ እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከፍተኛ አስተዋጾ አድርገዋል፤ ገና ብዙ ያደርጋሉ። በእርግጥ በሰለጠነው ዓለም ጥቅማቸው 95 % ጉዳታቸው 5% ነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። የእለት እለት እንቅስቅሲያቸው ከነዚሁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር የተሳሰረ ነው። ማለትም ትራንስፖርት ለመያዝ፣ የበረራ ቀጠሮ ለማድረግ ፣ የህክምና ቀጥሮ ለመያዝ ፣ ግብር ለመክፈል፣ የባንክ ሂሳባቸውን ለማውቅ፣ መኪና የሚያሽከረክሩም ከሆነ የተሻለውን እና የትራፊክ መጭናነቅ የሌለበትን መንገድ ለመምረጥ ባጠቃላይ ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ከሚፈልጉበት ግብ ለመድረስ ይጠቅሙባቸዋል። ቢሆንም ግን ዘመኑ ያመጣው ክስተት ስለሆነ ከነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር አብሮ ለመኖር የሞራልና የሕሊና ዝግጅት ለማድረግ ፍላጉቱ ሊኖረን ይገባል። ለመልካም ነገር ለመጠቀም ከፍተኛ የሆነ ያመለካከት ለውጥና የግንዛቤ አብዮት ያስፈልገናል» ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዉናል።

በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ወደ ዓለማችን ከተስፋፉ ወዲህ በተለይ ወጣቱ ብዙዉን ትርፍ ጊዜ የሚያዉለዉ በማኅበራዊ መገናኛ ላይ በመሆኑ በተለይ እኛ በታሪክ ከቤተሰብ ወደ ልጅ የምናሳልፈዉን የወግ ባህላችን እንዳያዉቅ እየዳረገዉ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።

የፌስቡክና የትዊተር ማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ የሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዉ ያሬድ ሹመቴ እንደሚሉት ደግሞ የሚያቋቸዉ ሰዎች አብዛኞች ነዋሪዎች የማኅበራዊ ተጠቃሚ ቢሆኑም፤ ለግልጋሎቱም የሚከፈለዉ ዋጋ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ብሎም ግን የአጠቃቀሙን ሥርዓት ባህል ማዳበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሳሚር ዴቪድ የተባሉ የዶይቼ ቬለ ተከታታይ የስድብ እና የጥላቻ ኮመንቶች በኅብረተሰቡ ተቻችሎ ተዋህዶ የመኖር ባህል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣል ስለዚህ በልዩነቶች የመከባበር ልምድ ላይ መገናኝ ብዙሃን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሥራት አለባቸዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል። በዓለማችን ከፍተኛ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ሕንድ ከዝያ ዩኤስ አሜሪካ ብራዚል መሆናቸዉን የተናገሩት የሥነ-ግጥም ቤተሰቦችን በፌስቡክ በማሰባሰባቸዉ የሚታወቁት አቶ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ፤ በኢትዮጵያን የማኅበራዊ መገናኛ አጠቃቀም በባህላችን ላይ ጥቅምም ጉዳትም ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።

በጎርጎረሳዉያኑ 2015 ዓ.ም በወጣ አንድ የጥናት መረጃ በዓለማችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የብዙኃን መገናኛ ሱሰኞች መሆናቸዉም ተመልክቶአል። ይህን ተከትሎ በማኅበራዊ መገናኛዎች ቤተሰብ የሚለዉ ትርጉም በጣም የተለጠጠ መሆኑን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዳሉት ተናግረዋል።  

የዲያቆን ዳንኤል ሃሳብን የሚጋሩት የፊልም ሥራ አዋቂዉ ያሬድ ሹመቴም የፌስቡክ አጠቃቀም ዉስን መሆኑ ትክክል አለመሆኑን ገልፀዋል። ሲሳይ አየለ የተባሉ የዶቼ ቬለ ፌስ ቡክ ተከታታይ ሲሻል ሚዲያ ማለት ትውልድ ሊማርበትም ሊከስርበትም የሚችልበት መንገድ አለው፤ ያን አላምጦ መጉረስ የባለቤቱ ፈንታ ነው፤ ያደጉት ሃገራት በሶሽል ሚዲያ አድገዋለም ከስረዋልም ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

መሃመድ አዲል የተባሉ የዶይቼ ቬለ የፊስ ቡክ ተከታታይ የመገናኛ ብዙኃን ተበራከቱ የጋዜጠኝነት ክቡር ስራን ያለ ትምህርት እና ብቃት እንዲሁም ኃላፊነተት ብዙ ሰዎች የጋዜጠኝነት ሞያን ተቀላቀሉ። በመሆኑም የውሸት ዘገባ፣ ከባህል ዉጭ ፀያፍ ነገርን ይፋ ማውጣት፣ያልተጠበቁ ነገሮችን ማየት የተሰወሩ ነገሮችን በገሀድ ማየት የተለመደ ነገር ሆነ ፡ በመሆኑም ጥቅምና ጉዳት ጎን ለጎን መጓዝ ጀመሩ ። በአጠቃላይ የመገናኛ ብዙኃን በእሬት እና በማር የተለወሰ የእለት ተዕለት ምግብ ያህል ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል ።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic