ባህላዊዉ የጀርመን ድግስ በአዲስ አበባ | ባህል | DW | 23.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ባህላዊዉ የጀርመን ድግስ በአዲስ አበባ

የጎርጎረሳዉያኑ መስከረም ወር በገባ በሶስተኛዉ ቅዳሜ በጀርመን የባቫርያ ግዛት መዲና በሆነችዉ ሙኒክ ከተማ ላይ የሚጀምረዉ ባህላዊዉ የቢራ ድግስ፤ ዘንድሮ ከተለያዩ የዓለም ሀገራትና አካባቢዎች የተሰባሰቡ 6, 3 ሚሊዮን እንግዶችን አስተናግዶ የዛሬ አስር ቀን ግድም ተጠናቅዋል።

ታድያ በዚህ ለአስራ አምስት ቀናት በተካሄደዉ የጀርመናዉያኑ ታዋቂ ቢራ ድግስ ላይ 6,5 ሚሊዮን ሊትር ቢራ እንደተሸጠ፤ በርካታ የዶሮና የአሳማ ሥጋ ጥብስ በማዕድ መቅረቡን መሸጡን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ታዋቂ የዓለም ሰዎች የሚገኙበት ይህ ባህላዊ መድረክ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት እየተለመደ የጀርመናዉያኑን ባህል እያስተዋወቀ ዳስ ማስጣሉን ቀጥሎአል። አዲስ አበባ የሚገኘዉ አንጋፋዉ ሂልተን ሆቴል የጀርመኑን ባህላዊ የቢራ ድግስ ከጀርመን ባህላዊ ምግቦችና ሙዚቃ ጋር በማዋዛት ዘንድሮ ለአስራ ሰባተኛ ግዜ እንግዶችን ጋብዞ ባህሉን አስተዋዉቆአል። በዕለቱ ዝግጅታችን የአዲስ አበባዉን ባህላዊ የጀርመኞች የቢራ ድግስ ማለትም በጀርመንኛ መጠርያዉ «ኦክቶበር ፊስት»ን እናያለን
የባቫርያ ግዛት መዲና በሆነችዉ በሙኒክ ከተማ በየዓመቱ የሚደገሰዉ የጀርመናዉያኑ ባህላዊ የቢራ ድግስ ማለትም በጀርመንኛ መጠርያዉ «ኦክቶበርፊስት» ጀርመን ከመስከረም 10 እስከ መስከረም 25 ድረስ ተካሆዶአል። በጀርመን ኦክቶበር ፊስት በመባል የሚታወቀዉ እጅግ ታዋቂዉና ተወዳጁ የቢራ ድግስ ዘንድሮ ለ 181 ኛ ግዜ የተካሄደ ሲሆን ይህ ድግስ የጀመረዉ የዚያን ግዜዉ የጀርመኑ ልዑል ሉድቪግ እና ልዕልት ቴሪዘን የሰርግ ድግስ ተከትሎ ነዉ። ከዛሪ 181 ዓመት በፊት ከተሰረገዉ ድግስ በኋላ፤ ይኸዉ በየዓመቱ ከዓለም የተሰባሰቡ የጀርመን የቢራ አፍቃሪዎች ቢራቸዉን በመኮምኮም ያከብራሉ። በጀርመን ባቫርያዋ ግዛት የጀርመናዉያኑ ኦክቶበርፊስት ሲከበር 45 ዓመቱን ለማክበር በጣት የሚቆጠሩ ቀናት በቀረዉ በሂልተኑ ሆቴል ደግሞ የጀርመናዉያኑ ባህላዊ ድግስ ለ17ኛ ግዜ ተደግሶ ነበር። የጀርመናዉያኑ ባህላዊ ድግስ አዲስ አበባ ላይ እንዴት ነበር ስል የኖርዊዜጋ የሆኑት የአዲስ አበባዉ ሂልተን ሆቴል ዋና ስራ አስኪያጅ ሆከን ጋርደን ላርሰንን ስልክ ደዉዬ ጠይቂአቸዉ ነበር።


«የኦክቶበር ፊስት ድግስን ምንነት መቼም ማብራራት የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም ነገር ግን እኛ ሂልተን ሆቴል ላይ ስላዘጋጀነዉ ስለጀርመናዉያኑን የኦክቶበርፊስት ልንገርሽ። የዘንድሮ ይህንን ድግስ ያዘጋጀነዉ ለአስራ ሰባተኛ ግዜ ነዉ። የጀርመኑ ባህላዊ እና ዓመታዊ የቢራ ድግስ « ኦክቶበርፊስት» በሂልተን ሆቴል ለመጀመርያ ግዜ የተዘጋጀዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1997 ዓ,ም ነበር። ከዝያን ግዜ ወዲህ በየዓመቱ እናዘጋጃለን። በርግጥ ይህ ድግስ የዛሪ አስራሰባት ዓመት ሲጀመር እኔ በቦታዉ ላይ አልነበርኩም። ቢሆንም እጅግ ደማቅ ነበር። ዘንድሮ ለ17ኛ ግዜ በተዘጋጀዉ ድግስ ላይ የሙዚቃ ያቀረበዉ ባንድ የመጣዉ ከዝያዉ ከሙኒክ ነዉ። ይህ የሙዚቃ ባንድ ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት በየዓመቱ ሂልተን ሆቴል ላይ በምናዘጋጀዉ ድግስ ላይ በመሳተፍ አብሮን ተጉዞአል።»
ኦክቶበርፊስት በመባል የሚታወቀዉና በጀርመን ለሁለት ሳምንት የሚዘልቀዉ የጀርመኑ ባህላዊ ዓመታዊ ድግስ በየዓመቱ ከ 6 ሚሊዮን ህዝብን በማስተናገዱ በዓለም እጅግ ግዙፉ ሕዝባዊ በዓል በመሆኑም ይታወቃል። በርግጥ ከአለፈዉ ዓመት ድግስ ጋር ሲነጻጸር አነስ ያለቁጥር ህዝብ እንደተገኘበት ነዉ የተነገረዉ የአዲስ አበባዉ ደግሞ ወደ 2000 ያህል እንግዶች መገኘታቸዉን የሂልተን ሆቴል ዋና ስራ አስኪያጅ ተናግረዋል።
«በድግሱ ላይ የሚደረገዉ ነገር፤ በመጀመርያ ግቢዉ ዉስጥ እጅግ ትልቅ ዳስ ይጣላል። ምክንያቱም ድግሱን ብሎ የሚመጣዉ እንግዳ ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ በመምጣቱ ሆቴሉ ያለዉ አዳራሽ በቂ ባለመሆኑ ነዉ። ለምሳሌ ይህ ድግስ በተደረገበት በመጨረሻዉ ቀናት ላይ የመጣዉ ሕዝብ ቁጥር ከ 2000 ሽ በላይ ነበር። በባቫርያ ግዛት ሙኒክ ላይ እንደሚደረገዉ ሁሉ ዳሱ ዉስጥ በሚቀመጠዉ አግዳሚ ወንበርና ጠረቤዛ እንዲሁም የዳሱ ጣርያ በሰማያዊና ነጭ ዥንጉርጉር ቀለም ይሽቆጠቆጣል። የጀርመን ሙዚቃ ይደመጣል በአጠቃላይ የጀርመን እንደሚሆነዉ የጀርመኑ ድግስ ሁኔታ ሁሉ እዚህ እንዲታይ ይደረጋል።»
በበድግሱ ላይ በእንግሊዘኛዉ «ሶሲይጅ» የሚሉት ማለትም «ቋሊማ» እንዲሁም በጀርመናዉያኑ ባለሞያዎች የሚሰራዉ በጀርመንኛ መጠርያዉ ዛወር ክራዉት ማለትም፤ በኮምጣጤ የታጀለዉ የጥቅል ቆመን፤ እንዲሁም ሌሎች የጀርመናዉያኑ ባህላዊ ምግቦች ከጀርመን ወደ አዲስ አበባ ተልከዉ የሂልተኑን የቢራ ድግስ ገበታ እንደሚያደምቁ የሂልተን ሆቴል ዋና አስተዳዳሪ ተናግረዋል።
«ይህ የጀርመናዉያን ባህላዊ ድግስ አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ላይ ሲዘጋጅ ለ17ኛ ዓመት በመሆኑ አብዛኛዉ ሰዉ ስለባህሉ ምንነት የሚያዉቅ ይመስለኛል። በዚህ ድግሥ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የቢራ ጠማቂ ፋብሪካዎች ጋርም በቅርበት እንሰራለን። ቢራ በኢትዮጵያ የአመጋገብ ስርዓት ዉስጥ ትልቅ ቦታን እያገኘ የመጣ ስለሆነ እኛ በሂልተን ሆቴል በአዘጋጀነዉ የቢራ ሰፊ ግብዣ ላይ ቢራን ለመጎንጨት በርካታ እንግዶች መጥተዋል ማለት እችላለሁ። ስለዚህ ትልቅ እና እጅግ ጥሩ የሆነ ድግስ ነበር። በሌላ በኩል ድግሱ በጀርመን ሙኒክ ከተማ ላይ በየዓመቱ የሚታየዉን ባህላዊ ክንዉኖች ሁሉ በደንብ አስቃኝቶአል።»
በሂልተን ተገኝተዉ የጀርመናዉያኑን የቢራ ድግሥ እንዴትነት ያዩ ኢትዮጵያዉያን ደስተኞች መሆናቸዉንና እንደዉም በድግሱ ላይ የሚቀርበዉ ምግብና ሙዚቃ ሁሉ መለመዱን ያጫወቱንን የሂልተን ሆቴል ስራ አስኪጅ በድግሱ ላይ የጀርመናዉያኑም ቁጥር ጥቂት እንዳልነበር ተናግረዋል።
« በርግጥ በዚህ ድግስ እጅግ በርካታ ጀርመናዉያን ተካፋይ ነበሩ። በድግሱ ላይ የጀርመኑ አምባሳደር የኦክቶበሩን ድግስን ባደረግንባቸዉ ሶስት ተከታታይ ቀኖች ሁሉ ተገኝተዉ ነበር። በርግጥም እጅግ ጥሩን ግዜ ነበር ያሳለፉት። በዚሁ ዝግጅት ላይ ኢትዮጵያዉያን ጀርመናዉያን የኦስትርያ ዜጎች እንዲሁም ሌሎች በርካታ የዉጭ ዜጎችም ተገኝተዋል።»
ይህ የጀርመን ባህል ዉቅያኖስ አቋርጦ በአፍሪቃ ሕብረት ዋና መቀመጫ መዲና አዲስ አበባ ላይ መካሄዱ ከጀርመን ጋር ያለዉን የባህል ትስስር እና ትዉዉቅ ከኢትዮጵያ ብሎም ከአፍሪቃ ጋር እንደሚያጠናክር የተናገሩት የሂልተኑ ማኔጀር ሆከን ጋርደን ላርሰን


«ድግሱ ላይ ለመገኘት በርግጥ በቅድምያ ትኬት መግዛት ያስፈልግ ነበር። ትኬቱን ገዝቶ ወደ ድግሱ የመጣ ደግሞ ለድግሱ የተዘጋጀዉን ምግብ በነጻ መመገብ ይችላል። ቢራ ግን በሽያች መልክ ነበር የቀረበዉ። በሳምንቱ መጠናቀቅያ ላይ አርብ ዕለት የጀመረዉ የጀርመናዉያኑ ባህላዊ ድግስ «ኦክቶበርፊስት » እሁድ ነበር የተጠናቀቀዉ። የእሁድ ዕለቱ ድግስ የተመደበዉ የቤተሰብ እንዲሆን ነበር፤ በርካታ ወላጆች ከልጆቻቸዉ ጋር በመገኘት ተደስተዉ አሳልፈዋል»
ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሂልተን ሆቴል በተዘጋጀዉ የጀርመን ባህላዊ ድግስ ላይ ሶስቱንም ቀናት የተገኙት በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር እጅግ መኩራታቸዉን የገለፁልን የሂልተኑ ስራ አስኪያጅ ሆከን ጋርደን ላርሰን
« እርግጥ ነዉ ሂልተን በተዘጋጀዉ «ኦክቶበርፊስት» ላይ ሲገኙ በጀርመናዊነታቸዉ የኮሩና የዚህም ዝግጅት ተካፋይ በመሆናቸዉ ደስተኛ የሆኑ ይመስለኛል። እኔም በድግሱ ላይ አብሪአቸዉ በአንድ ጠረቤዛ ላይ በመቀመጤ ታላቅ ኩራት ይሰማኛል። እንደነገርኩሽ ለሶስት ቀን በተዘጋጀዉ ድግስ ላይ ሶስቱንም ቀን ተገኝተዉ ነበር። ጥሩ ግዜም እንዳሳለፉም እተማመናለሁ።»
ከዓመት ወደ ዓመት የጀርመናዉያኑን ባህላዊ ድግስ አይነት ለማየት ዓመት ጠብቆ ወደ ሂልተን ሆቴል ግቢ ዉስጥ በሚጣለዉ ትልቅ ድንኳን ዉስጥ ባህላዊዉን የጀርመናዉያን ድግስ አብሮ የሚደግሰዉ ሕዝብ መጨመሩን የገለፁት የሂልተኑ ማኔጀር ሆከን ጋርደን ላርሰን በመጨረሻ፤
« በአዲስ አበባዉ ሂልተን ሆቴል በየዓመቱ የሚዘጋጀዉ «ኦክቶበርፊስት» ማለትም የጀርመናዉያኑ ባህላዊ ድግስ ለከተማዋ አንድ ማዕከል ሆንዋል ማለት እችላለሁ። በዚህም በመጭዉ የጎርጎረሳዊዉ 2015 ዓ,ም በምናዘጋጀዉ በዚሁ በዓል ላይ በርካታ ሰዎችን ለማስተናገድ ከአሁኑ እየተዘጋጀን ነዉ»
በሂልተን የሪቪኑ ማኔጀር ነኝ ያሉን የሆቴሉ ሰራተኛ አቶ ሰይፈዲን ባዲ በበኩላቸዉ የጀርመናዉያኑን ድግስ እዝያዉ አዲስ አበባ ላይ በመተዋወቃቸዉ ደስተኛ መሆናቸዉን ተናግረዋል።በሂልተን የተዘጋጀዉን የጀርመናዉያን ባህላዊ ድግስ በተመለከተ ቃለ ምልልስ የሰጡንና ለዝግጅቱ መሳካት የተባበሩንን የሂልተን ሆቴል ባልደረቦች እናመሰግናለን። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።
አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic