ባህላዊዉ የቡሄ በአል | ባህል | DW | 26.08.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ባህላዊዉ የቡሄ በአል

መጣና መጣና ደጅ ልንጠና መጣና በአመቱ እንዴት ሰነበቱ ክፈቱልን በሩን የጌታዪን !

default

ጤና ይስጥልኝ አድማጮች እንደምን ዋላችሁ ምነዉ ከረፈደ ሆያሆዪ ማለታችሁ ሳትሉ አልቀራችሁም፣ እኛም ሆያ ሆዪ ልንል ሄደን እናንተም አክብሩ ብለን የበአሉን አከባበር መነሻ ለማወቅ ባለሞያ ስናፈላልግ ዘግየት አልን፣ ብቻ አሁንም ለቡሄ የተጋገረዉ ሙልሙል አላለቀም፣ ጉዝጓዙም ገና እርጥብ ነዉ፣ እንኳን አደረሳችሁ፣ በአገራችን ቡሄን ተከትሎ፣ የፍልሰታ፣ በአል በደማቅ ተከብሮአል፣ በተለይ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጽያ ክፍል አሸንዳ ወይም ሻደይ የሚል የሚል መጠርያ ያለዉ በአል በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ እንደሆነም ይነገርለታል። በዛሪዉ ዝግጅታችን በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የቡሄን በአል አከባበር እና ትርጉሙን እንዲሁም የፍልሰታ ማለት የአሸንዳን በአል አከባበርን በሰፊዉ እንቃኛለን ለጥንቅሩ አዜብ ታደሰ ነኝ መልካም ቆይታ
ቡሄ በሉ ልጆች ሁሉ ቡሄ መጣ ያመላጣ ቅቤ ቀቡት ጸጉር ያዉጣ ቡሄ መጣ ተኳኩሎ ሳይወጣብን እንጨፍር ቶሎ ብለን በተለይ በልጅነት ግዜያችን ያልጨፈርን በሙልሙል ዳቦ ያልተደሰትን የለንም።
መጣና መጣና ደጅ ልንጥና መጣና ባመቱ እንዴት ሰነበቱ፣ ክፈት በለዉ በሩን የጌታዪን ክፈት በለዉ ተነሳ ያንን አንበሳ፣ መጣሁኝ በዝና ተዉ ስጠኝ ምዘዝና እየተባለ የሚጨፈርበት የቡሄ በአል ትርጉሙ ምን ይሆን በዚህ ርእስ ዙርያ ጥናት ያካሄዱት በአዲስ አበባ ዪንቨርስቲ የቋንቋ ክፍል ባልደረባ እና መምህር መስፍን መሰለ ማብራርያ ይሰጡናል። በወሎ አካባቢ የቡሄ አከባበር እንዴት ይሆን በአዲስ አበባ ዪንቨርስቲ የቋንቋ ምሁር የሆኑት አቶ መሃመድ አሊም የሚሉን ይኖራል።

የኔማ እመቤት፣ እሜት እሜት ሎሚ ተረከዝ ትርንጎ ባት የኔ እማ እመቤት የፈተለችዉ የሸረሪት ድር አስመሰለችዉ ሸማኔ ጠፍት ማርያም ሰራችዉ ለዝያች ለማርያም እዘኑላት አመት ከመንፈቅ ወሰደባት እያሉ ልጆች ወይዛዝርትን በሞያቸዉ ያወድሳሉ።

የኔማ ጌታ የገደለበት ስፍራዉ ጎድጉዶ ዉሃ ሞላበት እንኳን ሰዉና ወፍ አይዞርበት ያሞራ ባልቴት ዉሃ ትቅዳበት። የኔማ ጌታ የሰጠኝ ካራ ከዚህ ብመዘዉ ጎንደር አበራ፣ የኔማ ጌታ የሰጠኝ ስንዴ ገና ሳልበላዉ አበጠ ክንዴ። እያሉ ልጆች አባወራን እያወድሱ ጅራፍ እያጮሁ ይጨፍራሉ በቡሄ በአል የጅራፍ ማጮህ ባህል ትርጉም ይኖረዉ ይሆን መምህር መስፍን መሰለ ማብራርያ ይሰጡናል።

ተዉ ስጠኝና ልሂድልህ እንዳሮጌ ጅብ አልጩህብህ ኸረ በቃ በቃ ጉሮሮአችን ነቃ ኸረ በስላሴ ልትወጣ ነፍሴ ብትሰጠኝ ስጥኝ ባትሰጠኝ እንዳሻህ ከነገሌ ሁሉ አነሰ ወይ ጋሻህ እየተባለ የሚጨፈርበት የቡሄ በአል ሃይማኖታዊ መሰረት እንዳለዉ ይነገራል። ወይ የኔ ጌታ የሰጠኝ ሙክት እግንባሩ ላይ አለዉ ምልክት፣ መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት፣ የኔማ እመቤት መጣንልሽ የቤት ባልትና ልናይልሽ። የኔማ እመቤት ብትሰራ ዶሮ ሽታዉ ይጣራል ገመገም ዞሮ የኔማ እመቤት የጋገረችዉ የንብ እንጀራ አስመሰለችዉ። እያሉ ልጆች እማወራን እያወደሱ ይጨፍራሉ። ሆያ ሆዪ፣ ሆያ ሆዪ ወይ የኔ ጌታ ዋርካ ነህ ዋርካ ቢጠለሉብህ የማታስነካ እየተባለ የሚጨፈርበት የቡሄ ጨዋታ ወደ ከተማዉ አካባቢ በአንዳንድ ቦታ መልኩን መቀየሩ ሊያሳስበን እንደሚገባ መምህር መስፍን መሰለ ይጠቀማሉ። ያድምጡት

አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ