ቡድን ሰባት፣ የአለም ምጣኔ ሐብትና አዳጊ ሐገራት | ኤኮኖሚ | DW | 26.04.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ቡድን ሰባት፣ የአለም ምጣኔ ሐብትና አዳጊ ሐገራት

«ባለፈዉ የካቲት ከተሰበሰብን ወዲሕ የአለም ምጣኔ ሐብት በተሻለ ፍጥነት እያገገመ፣ እየተጠናከረ፣ እየሰፋም መጥቷል---»

የቡን ስምት ሚንስትሮች

የቡን ስምት ሚንስትሮች

የአለም ምጣኔ ሐብት በተሻለ ፍጥነት እንደሚያድግ ሠባቱ በኢንድስቲሪ የበለፀጉ ሐገራት አስታወቁ። በሳምንቱ ማብቂያ ዋሽንግተን-ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ተሰብስበዉ የነበሩት የሠባቱ ሐገራት የገንዘብ ሚንስትሮችና የባንክ ገዢዎች እንዳስታወቁት የዘንድሮዉ የአለም ምጣኔ-ሐብት ዕድገት ከአምናዉ የተሻለ ነዉ። የድሆቹ የአፍሪቃ ሐገራት ምጣኔ-ሐብት ግን የመሻሻል ተስፋ የለዉም።የበለፀገዉ አለምም ሆነ የአለም የገንዘብ ተቋማት የአፍሪቃን ችግር ለማቃለል ብዙ አለመጣራቸዉ የተቃዉሞ ሠልፍ ወቀሳና ትችት አስከትሏል።

ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓንና ዩናይትድ ስቴትስን የሚያስተናብረዉ ቡድን-ሰባት ሥለአለም ምጣኔ ሐብት እድገት ያደረገዉ ግምገማና ዉጤቱ-በእጅጉ ለሰባቱ፣ በጣሙን እነሱን ለሚከተሉ የአዉሮጳ፣ የእስያና የደቡብ አሜሪካ አብዛኛ ሐገራት የምሥራች ነዉ።ዋሽንግተን ዉስጥ ቅዳሜና እሁድን የመከሩት የሰባቱ ሐገራት የገንዘብ ሚንስትሮችና የየሐገሩ ብሔራዊ ባንክ ገዢዎች ትናንት በስብሰባቸዉ ማብቂያ ባወጡት የጋራ መግለጫ እንዳሉት «የአለም» ያሉት ምጣኔ ሐብት ዘንድሮ ያሳየና የሚያሳየዉ እድገት አበረታች ነዉ።

የሰባቱ ሐገራት የገንዘብ ተቋማት ባለሥልጣናት ባለፈዉ የካቲት አድርገዉት በነበረ ስብሰባቸዉ ያኔ ከዉድቀት በማገገም ላይ የነበረዉ የአለም ምጣኔ ሐብት በ 3.9 በመቶ እያደገ እንደነበር አስታዉቀዉ ነበር። «ባለፈዉ የካቲት ከተሰበሰብን ወዲሕ የአለም ምጣኔ ሐብት በተሻለ ፍጥነት እያገገመ፣ እየተጠናከረ፣ እየሰፋም መጥቷል---» ይላል የሰባቱ የአለም ሐብት ዘዋሪዎች የትናንቱ የጋራ መግለጫ።በአዉሮጳዉያኑ አምና 3.9 የነበረዉ እድገት አራተኛዉ ወሩ በተገባደደዉ ዘንድሮ ወደ 4.6 ከፍ ብሏል።ይሕ አመታዊ የምጣኔ ሐብት እድገት ከሁለት ሺሕ ወዲሕ ፈጣኑ እድገት ነዉ።

የሐይል ምንጭ ዋጋ የመናር፣ የፀጥታ ችግር እድገቱን ያዉከወል የሚል ሥጋት ባይለየዉም---የሰባቱ ሐገራት የገንዘብ ሐላፊዎች እንደሚሉት የአለም ምጣኔ-ሐብት እድገት በመጪዉም የአዉሮጳዉያን አመት (2005) በ 4.4 በመቶ ያድጋል።የዩናይትድ ስቴትሱ የግምጃ ቤት ሚንስትር ጆን ስኖዉ ከሰባቱ ሐብታም ሐገራት የገንዘብ ባለሥልጣናት ጎን ለተሰበሰቡት ለአለም ባንክና ለአለም ገንዘብ ድርጅት-(IMF በምሕፃሩ) የፖሊሲ አርቃቂዎች እንደነገሩት ያሁኑ ስብሰባ የተደረገዉ የአለም እድገትና መረጋጋት ተስፋ በደመቀበት ወቅት ነዉ።

እድገቱ የተመሰከረለት፣ የመረጋጋቱ ተስፋ-የተነገረለት አለም-ወትሮም የበፀገዉ ብቻ መሆኑ ግን የአለምን የትነት ብያኔ-ግራ፣ የእድገቱን እንዴትነት ትርጓሜም ጠባብ ማድረጉ ነዉ-እንቆቅልሹ።የድሆቹ ሐገራት በተለይ ከሰሐራ-በስደቡብ የሚገኙት የአፍሪቃ ሐገራት ሕዝብ መጪዉንም ዘመን እንደ-እስከ ዛሬዉ ምናልባትም በባሰ ሁኔታ በድሕነት፣ በበሽታ፣ በረሐብና ብጥብጥ የሚገፋ መሆኑን እራሳቸዉ የአለም መሪዎች መስክረዋል።በሁለት ሺሕ መግቢያ የተሰየመዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ድሕነት፣ በሽታ፣ ረሐብና ማይምነትን ለመቀነስ ያፀደቀዉ መርሕ በተገያዘለት ጊዜ ግብ ሊመታ ቀርቶ ገቢራዊነቱም ጨርሶ የተረሳ ይመስላል።


የድሖቹ ሐገራት ተወካዮች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የድሆች ተከራካሪዎች ለአፍሪቃ ድሕነት መባባስ፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዉሳኔም መጣስ ተጠያቂዉ የበለፀጉት ሐገራትና እኒሕ ሐገራት የሚመሯቸዉ የአለም ባንክና የአለም ገንዘብ ድርጅት የሚከተሉት መርሕ ነዉ።

ለድሆች ይበልጥ መደሕየት ዋና ተጠያቂ የሚደረገዉ የአለም ባንክ ራሱ-በቅርቡ እንዳመነዉ አፍሪቃና ደቡብ አሜሪካ ዉስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በረሐብና በበሽታ እንዲሰቃይ ተፈርዶበታል።ወይም በባንኩ ቋንቋ-ተትቷል።ባንኩ ከIMF ጋር የተመረተበትን ስልሳኛ-አመት ሲያከብር እንዳለዉ ከ1981 እስከ 2001 በነበረዉ ሃያ ዘመን በፍፁም ድሕነት የሚኖረዉን የአለም ሕዝብ ቁጥር በግማሽ ያሕል መቀነስ መቻሉን እንደ ግዙፎቹ የገንዘብ ድርጅቶች-በጎ ሥራ፣ እንደ በለፀገዉ አለም ቸሮታ መቁጠሩ አልቀረም።

ባለፈዉ ቅዳሜ እዚያዉ ዋሽንግተን ዉስጥ የተሰለፈዉ ከሁለት እስከ ሁለት ሺሕ የተገመተ ሕዝብ የሁለቱን የገንዘብ ተቋማትና ተቋማቱን የሚመሩትን የቡድን ሰባት አባል ሐገራትን መርሕ አዉግዛል።ሠልፉን ካደራጁት አንዱ ኦክስፋም የተባለዉ ግብረሰናይ ድርጅት ባልደረባ ካሮሊነ ግሪን እንዳሉት የበለጉት ሐገራት-የገንዝብ ሐላፊዎችም፣ የአለም ገንዘብ ድርጅቶች ተጠሪዎችም ስብሰባ ለድሐዉ አለም ምንም የተከረዉ ነገር የለም።