ቡድን-ሃያ በአሥረኛ ዓመቱ | ኤኮኖሚ | DW | 16.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ቡድን-ሃያ በአሥረኛ ዓመቱ

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትና በተፋጠነ ዕድገት እየተራመዱ የመጡት ሃገራት ስብስብ ቡድን-ሃያ ከተቋቋመ ዛሬ አሥር ዓመት ሆነው።

የፒትስበርጉ የመሪዎች ጉባዔ

የፒትስበርጉ የመሪዎች ጉባዔ

በታሕሣስ ወር 1999 ዓ.ም.፤ ማለት በሚሌኒየሙ ዋዜማ የምሥረታው ጉባዔ የተካሄደው በዚህ በጀርመን በርሊን ውስጥ ነበር። ተቋሙ ሁለት ዓመት ቀደም ሲል ከተከሰተው የእሢያ የፊናንስ ቀውስ በኋላ ሲመሰረት ዓለምአቀፉን የፊናንስ መዋቅር መልሶ የማጠናከር ዓላማ ይዞ ነበር የተነሣው። ታዲያ ስብስቡ በሂደቱ ምድራችንን ያዳረሰውን ዓለምአቀፍ የፊናንስ ቀውስ ለመግታት ባይችልም በሌላ በኩል በችግሩ የተነሣ ይበልጥ ክብደት እያገኘ መሄዱ አልቀረም። በተለይ አዳጊዎቹ አገሮች የቀውሱ ተጠቃሚ መሆናቸው በቡድን-ሃያ የአንድ አሠርተ-ዓመት ታሪክ ውስጥ የተለየ ቦታ የሚይዝ ነው። የበለጸጉት መንግሥታት በአንድ በኩል የዓለምን ኤኮኖሚ ለብቻቸው መዘወር ከማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውና በሌላ በኩልም የተራማጆቹ አገሮች ሚና መጨመር በወቅቱ ጎልቶ የሚታይ ሃቅ ሆኗል።

ቡድን-ሃያ የዛሬ አሥር ዓመት ሲመሰረት በተለይ በውስጡ የተጠቃለሉት በኤኮኖሚ በፍጥነት እያደጉ የሚሄዱ አገሮች ሚና በአሁኑ ወቅት መጠን ይጨምራል ብለው ያሰቡ ካሉ ብዙዎች አልነበሩም። የወቅቱ ዓለምአቀፍ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ የእነዚህን አገሮች ተሰሚነት ወይም ደግሞ በመፍትሄ ፍለጋው ያላቸውን ድርሻ ይበልጥ ከፍ ነው ያደረገው። ቡድን-ሃያ መጀመሪያ በርሊን ላይ ሲሰበሰብ የበለጸጉት መንግሥታት ለታዳጊዎቹ በጎ የመቀራረብ መንፈስ ያሳዩበት መድረክ እንጂ ከዚያ ብዙም ያለፈ አልነበረም። ቢሆንም ወደፊት ጠቃሚ በሆኑ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚና የፊናንስ ፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ አብሮ የመምከር ተሥፋ ተሰጥቷቸው ከጉባዔው ይሰናበታሉ። እርግጥ ሃሣቡ የተጸነሰው ከበርሊኑ የምሥረታ ስብሰባ ግማሽ ዓመት ያህል ቀደም ሲል ኮሎኝ ከተማ ውስጥ በተካሄደው የዓለም ኤኮኖሚ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ነበር። በዚሁ መሠረት ዋና ዋናዎቹ የበለጸጉ መንግሥታትና አዳጊ ሃገራት የፊናንስ ሚኒስትሮችና የማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪዎች በየጊዜው የጋራ ስብሰባ እያደረጉ እንዲመካከሩ ይወሰናል። እንዲያም ሲል ነበር የዛሬ አሥር ዓመት የበርሊኑ የቡድን-ሃያ ምሥረታ ጉባዔ የተካሄደው። የጀርመን የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት ሃላፊ ዲርክ ሜስነር የጊዜውን ሁኔታ መለስ ብለው ከሚያስታውሱት የቅርብ ታዛቢዎች አንዱ ናቸው።

“አዎን፤ ከአሥር ዓመት በፊት ያ ስብሰባ በፍጥነት የሚያድጉትን አገሮችና የበለጸጉትን መንግሥታት በአንድ ላይ ለማምጣት ቢቀር የመጀመሪያው ዕርምጃ ነበር። እስከዚያው የነበረን የዓለም ኤኮኖሚና ዓለምአቀፍ ስርዓቱም በአብዛኛው በቡድን-ስምንት አገሮች የተዋቀረ እንደነበር ይታወቃል። ቀድሞ ራመድ ያሉትና ታዳጊዎቹ አገሮች ከበለጸጉት ክበብ ሲነጻጸር በሚገባ የተደራጁ አልነበሩም። የረባ ተጽዕኖ ሊኖራቸውም አልቻለም። እና የቡድን-ሃያ ምሥረታ የተራመዱትን አገሮች የኤኮኖሚና የፖለቲካ ሚዛን በዓለምአቀፉ መድረክ ላይ ለማጠናከር የተደረገ ዕርምጃ መሆኑ ነው። ይህም በሚገባ ተሳክቷል”

ቡድን-ሃያ 19 አገሮች በፊናንስ ሚኒስትሮችና በማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪዎች የሚወከሉበት አካል ነው። ከዓባል ሃገራቱ ቀደምቱ የበለጸጉት የቡድን-ሰባት መንግሥታት ዩ.ኤስ.አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ብሪታኒያ፣ ኢጣሊያና ጃፓን ናቸው። የተቀሩት ደግሞ ከነዚሁ በቡድን-ስምንት ስብስብ የተሳሰረችው ሩሢያ፤ እንዲሁም ብራዚል፣ አርጄንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዚያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሜክሢኮ፣ ሳውዲት አረቢያ፣ ቱርክና ደቡብ አፍሪቃ ይሆናሉ። የአውሮፓ ሕብረት በሸንጎ ፕሬዚደንቱ ወኪልነት ራሱን የቻለ ሃያኛ የቡድኑ አባል ነው። ከዚሁ በተጨማሪ የዓለም ባንክና የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የ IMF ወኪሎችም በቡድን-ሃያ ስብሰባዎች የሚሳተፉ ናቸው። ዝርዝሩ እንደሚያሳየው እንግዲህ ስብስቡ በኤኮኖሚ ድርሻው በዓለም ላይ ሃያል ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትንና ራመድ ያሉትን አገሮች የጠቀለለው ቡድን-ሃያ ከዓለም ማሕበራዊ ምርት 90 በመቶውንና ከዓለምአቀፉ ንግድም 80 በመቶውን ድርሻ ይይዛል። ከዚሁ ሌላም ሁለት-ሶሥተኛውን የዓለም ሕዝብ በመጠቅለል ታላቅ ሃይል ነው።

“አዎን፤ ዋነኛው ጥንካሬ ያለው ቡድን-ሃያ ባለፉት አሥር ዓመታት ሂደት በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ታላቅ ለውጥ እንዲንጸባረቅ በማድረጉ ላይ ነው። ከ 15, 16 ወይም 17 ዓመታት በፊት የሶሻሊዝም ውድቀት በሚታይበት ጊዜ ለምሳሌ ቻይና በምጣኔ-ሐብት ሚናዋ የቤልጂግን ያህል እንኳ ክብደት የሌላት ገና አነስተኛ አገር ነበረች። እንደሚታወቀው ዛሬ የቻይና የዓለም ንግድ ድርሻ፣ ከውስጥ የሚመነጭና የሚገባው የመዋዕለ ነዋይ መጠንም በጣሙን ግዙፍ ነው። ሕንድም ከዓለም ኤኮኖሚ ወደ መተሳሰሩና መሳተፉ ሂደት ዘግየት ብላ ትግባ እንጂ አሁን ጠቃሚ ሃይል ለመሆን በቅታለች። ይህ የሃይል አሰላለፍ ለውጥ ደግሞ በቡድን-ሃያ ውስጥ ይንጸባረቃል። በጣም ጠቃሚ ነገር ነው”

ቡድን-ሃያ እርግጥ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈው ታላቅ ትኩረትን ሳይስብ ነው። በሚኒስትሮች ደረጃ የሚካሄዱት የሃሣብ መለዋወጫ ስብሰባዎቹ አጠቃላይ በሆኑ የዓለም ኤኮኖሚ ጥያቄዎች ላይ ሲያተኩሩ ሰፊው የዓለም ሕብረተሰብ ብዙም ልብ ያላቸው አልነበሩም። ሆኖም ቡድኑ የተመሰረተበትን ዘጠነኛ ዓመት ሊያከብር ጥቂት ሲቀረው ሁኔታው ከሥር መሠረቱ ይለወጣል። የጀርመኑ የልማት ፖሊሲ ኢንስቲቲዩት ተጠሪ ዲርክ ሜስነር እንደሚሉት በአሜሪካው የመዋዕለ-ነዋይ ባንክ በሌህማን ብራዘርስ ተንኮታኩቶ መውደቅ፣ በዓለም አቀፉ የፊናንስ ገበያና የኤኮኖሚ ቀውስ፤ እንዲያም ሲል ይሄው በዓለም ላይ ባስከተለው የቀጠለ ተጽዕኖ የተነሣ አሁን ዝናው የመጠቀ ነው።

“ቡድን-ሃያ አሁን በፊናንሱ ቀውስ ሳቢያ ሌላ ከፍተኛ ግምትን አግኝቷል። በመሠረቱ ስብስቡ ቡድን-ስምንትን ሲተካ በዚህም በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ወሣኙ መንኮራኩር አካል እየሆነ ነው። ይህ ደግሞ አንድ ጠቃሚ ታሪካዊ ዕርምጃ፤ እንበል ዓለምአቀፍ ዓብዮት ነው። እስካለፈው ዓመት ድረስ የጠቅላላው የዓለም ኤኮኖሚ ሂደት ዘዋሪ ማዕከል ቡድን-ስምንት ሆኖ ነበር የሚታየው። የበለጸጉት መንግሥታት ራሳቸው የሚያምኑትም ይህንኑ ነበር። ግን ዋናው ሃይል አሁን የበለጸጉትና የአዳጊዎቹ አገሮች ቅይጥ የሆነው ቡድን-ሃያ ሲሆን ይህም ዕውነተኛ ዓለምአቀፍ ዓብዮት ነው”

የሚያስደንቀው ቡድን-ሃያ በራሱ ክስረት ታላቅ ትርጉም ሊያገኝ መቻሉ ነው። ለነገሩ ከፊናንሱ ቀውስ ውስጥ የተገባው የቡድኑ ዓባል ሃገራት ዓለምአቀፉን የፊናንስ ገበዮች በአንድ መቆጣጠሪያ ስርዓት ለማረጋጋት የነበራችውን ውጥን ለማሳካት ባለመቻላቸው ነበር። አሁን ግን ይህንና ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮችን ከግቡ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።

“አሁን ትልቁ አጀንዳ መስተካከልና መስፋፋት ይኖርበታል። ምክንያቱም የፊናንሱ ቀውስ ከፈነዳ ወዲህ የምንታዘበው ቡድን-ስምንት እንደ አንድ ወሣኝ አካል በሌላ መተካቱን ነው። የቡድን-ስምንት ሚና አሁን ወደፊት ከዋነኞቹ አዳጊ አገሮች ጋር በዓለም ኤኮኖሚና የፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ ንግግር የሚደረግባቸውን ስብሰባዎች ማዘጋጀት ነው። እንግዲህ ቀድሞ የቡድን-ሃያ ማተኮሪያ የነበሩት የፊናንስ ገበያ ጥያቄዎች የአጀንዳው አንድ ክፍል ይሆናሉ። መላው ዓለምአቀፍ የፖሊሲ ጥያቄዎች፤ የአካባቢ አየር ይዞታ፣ ድህነት፣ ፈለሣ ወይም ስደት፤ በጥቅሉ በቡድን-ሃያ አጀንዳ ላይ የሚቀርቡ ናቸው”

ቡድን-ሃያ ከተመሰረተ ከአሥር ዓመት በኋላ ራሱ ቡድን-ስምንት እስካሁን ሆኖ የማያውቀውን ያህል ሃያል ለመሆን በቅቷል። ቡድን-ስምንት በጠቅላላው ዓለም፤ ቻይናን፣ ሕንድንና ብራዚልን በመሳሰሉት የተራመዱ አገሮች በሚመራው በታዳጊው ዓለም አንጻር የቆመ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታትና የሩሢያ ትንሽ ክበብ ነበር። አሁን አዳጊዎቹ አገሮች የቡድን-ሃያ የሃይል ተጋሪዎች ናቸው። እርግጥ ሁኔታው የዚሁ ስብስብ አካል ባልሆኑት አገሮች በኩል አንዳች ተጽዕኖ ማድረግ ያለመቻልን ስሜት ማሳደሩም አልቀረም። እናም ቡድን-ሃያ ሕያው ከሆነ ወዲህ ቡድን-172 የሚል ሃሣብ መጸነሱም የአጋጣሚ አይሆንም። እነዚህ የኋለኞቹ በቡድን-ሃያ ውስጥ ያልተካተቱት የመላው ወይም የቀሪው ዓለም መንግሥታት ናቸው።

ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ሂደት በጥቅል ሲታይ በ 21ኛው ምዕተ-ዓመት መግቢያ ላይ ብቅ ያሉት አዳዲስ ተዋንያን በመጪዎቹ ጥቂት አሠርተ-ዓመታት ውስጥ የዓለምን የፖለቲካ ሚዛን በሰፊው ለመለወጥ አቅም ያላቸው ነው የሚመስለው። ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑት በተለይ ብሪክ በሚል አሕጽሮት የሚታወቁት አራት መንግሥታት ብራዚል፣ ሩሢያ፣ ሕንድና ቻይና ናቸው። ዛሬ ዓለምአቀፉን የፊናንስ ችግር ለመቋቋም የሚካሄድ የመሪዎች ጉባዔ ካለነዚህ አገሮች የሚታሰብ አይደለም። አራቱ አገሮች 15 በመቶው የዓለም ኤኮኖሚ አቅም ሲኖራቸው በዓለም ንግድ ላይም 13 ከመቶ ድርሻ አላቸው። የአራቱ ክበብ በ 2,8 ቢሊዮን ዶላር ከአርባ በመቶ የሚበልጠው የዓለም ምንዛሪ ክምችት ባለቤትም ነው። ይሄው ልዕልና በዓለምአቀፉ የውሣኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የብሪክ አገሮች ሚና እጅግ እንዲያድግ ለማድረጉ አንድና ሁለት የለውም።

አንዳንድ ባለሙያዎች እንሚተነብዩት ይሄው የሚዛን ለውጥ ቢቀር በሚቀጥሉት ስድሥትና ሰባት ዓመታት ውስጥ ቀጣይነት የሚኖረው ነው። የብሪክ መንግሥታት እንዲያውም በሃያ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ቀደምቱን የበለጸጉ መንግሥታት ከኋላቸው ያስቀራሉ የሚሉም አልጠፉም። ዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ስርዓት በጥቂቶች መሆኑ ቀርቶ በብዙዎች መዘወሩ ለነገሩ ጥቅም እንጂ ጉዳት አይኖረውም። አንድ የማይታለፍ ሃቅ ቢኖር በነባሩ ስርዓት መቀጠል የማይቻል ነገር መሆኑ ነው። ቡድን-ሃያ በአሥር ዓመት ሕልውናው ቡድን-ስምንትን በመተካት ለለውጥ አመቺ መንገድን ቀዷል። የሚቀረው ዓለምአቀፍ ቀውሶች እንዳይደገሙ ሁነኛ ዘዴን ማስፈን፤ ፍትሃዊ ንግድን በማስፈን የታዳጊ አገሮችን ልማት ማዳበርና ድህነትን መቀነስ ነው።

DW

MM / HM