ቡድን ሃያ መንግሥታትና የዕዳው ቀውስ | ኤኮኖሚ | DW | 26.10.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ቡድን ሃያ መንግሥታትና የዕዳው ቀውስ

በቡድን-ሃያ ስብስብ ውስጥ ተጠቃለው የሚገኙት በተፋጠነ ዕድገት በመራመድ ላይ ያሉ ሃገራት የዓለም ኤኮኖሚ መንኮራኩር ከሆኑ ረዘም ያለ ጊዜ አልፏል።

default

ቻይናን፣ ብራዚልን ወይም ሕንድን የመሳሰሉት መንግሥታት ባለፉት ዓመታት ያሳዩት የኤኮኖሚ ዕድገት እጅግ የሚደነቅ ነው። ይሁን እንጂ ዓለምአቀፉ የዕዳና የፊናንስ ቀውስ በእነሱም ላይ ቢሆን ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። እነዚሁ ተራማጅ ሃገራት በአውሮፓው የዕዳ ችግር የተነሣ መላው ዓለም ከኤኮኖሚ ቀውስ ላይ እንዳይወድቅ በወቅቱ ብርቱ ስጋት አድሮባቸው ነው የሚገኙት። በመሆኑም ከሣምንት በኋላ ፈረንሣይ-ካን ላይ በሚካሄደው የቡድን-ሃያ የመሪዎች ጉባዔ ዋዜማ የዕዳውን ቀውስ በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም በአይ.ኤም.ኤፍ. በኩል ገንዘብ በማቅረብ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ሃሣብ ሰንዝረዋል።

የምንዛሪው ተቋም ገንዘቡን ከፍ በማድረግ ወደፊት ቀውሶችን በስኬት ለመቋቋም እንደሚችል ነው በነዚህ መንግሥታት የሚታመነው። ሆኖም ይህ ሃሣብ በተለይ በአሜሪካ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። አውሮፓውያኑም ቢሆኑ በወቅቱ በጥርጣሬ ዓይን ነው የሚመለከቱት። የአውሮፓውያኑ የገንዘብ ሽግግር ግብር ሃሣብ በአንጻሩ በተፋጠነ ዕድገት ላይ ባሉት ሃገራት ብዙ ደጋፊዎችን አግኝቷል። ግን ይህንንም አሜሪካ አልተቀበለችውም። እንግዲህ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸጉትንና በተፋጠነ ዕርምጃ ላይ በሚገኙት ሃገራት መካከል አንድነትም ልዩነትም በየመልኩ ጎልቶ በመታየት ላይ ነው።

በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት የሚራመዱት ሃገራት በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ያላቸው ሚና በተለይም ባለፈው አሠርተ-ዓመት ያለማቋረጥ እየጨመረ ነው የመጣው። በአሕጽሮት ብሪክስ በመባል የሚታወቁት ብራዚል፣ ሩሢያ፣ ሕንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪቃ በአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታቸው ሲመዘኑ ዛሬ በዓለም ላይ በኤኮኖሚ ቀደምት ከሆኑት 12 ሃገራት መካከል የሚደለደሉ ናቸው። አምሥቱ መንግሥታት በጋራ የዓለም ኤኮኖሚን 25 በመቶ ድርሻም ይይዛሉ። ከዚህ አንጻር እንግዲህ ቻይናን፣ ብራዚልንና ሕንድን የመሳሰሉት ሃገራት አውሮፓውያን መንግሥታት ለዕዳ ቀውሳቸው መፍትሄ እንዲያሰፍኑ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መጠን መወትወታቸው ጨርሶ አያስደንቅም። ምክንያቱም በቀውሱ ሳቢያ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ ቢከተል የእነሱም ዕድገት ብርቱ አደጋ ላይ ነው የሚወድቀው።

“እነዚህ ተራማጆቹ አገሮች በቀውሱ ሊጠመዱ የመቻላቸው አደጋ ገና ከአሁኑ ትልቅ ነው። ይህ ደግሞ የአክሢዮን ገበዮችን፣ ምንዛሪዎችንና ዋጋን ይመለከታል። ሂደቱ በያንዳንዱ አገር ካለው የዕድገት ሂደትና መሠረታዊ ዳታዎች ነጻ መሆኑም ሊታወቅ ይገባዋል”

ይህን የሚሉት በዶቼ ባንክ የነዚሁ የአዳጊዎቹ ገበዮች ምርምር ዘርፍ ሃላፊ ማሪያ ላንዜኒ ናቸው። በዚሁ ሁኔታ የተነሣ ነው በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሃገራት በቡድን-ሃያ የካን የመሪዎች ጉባዔ ዋዜማ ዓለምአቀፉን የምንዛሪ ተቋም የመፍትሄ መንገድ አድርገው ያቀረቡት። እንደነርሱ ሃሣብ የምንዛሪው ተቋም ተጠናክሮ የኤውሮ ዞን መንግሥታት የዕዳ ቀውሳቸው ለመከላከል በሚያደርጉት ትግል አጋዥ ሊሆን ይችላል። የሚታሰበው የምንዛሪው ተቋም ወደፊት ችግር ላይ የወደቁትን የአውሮፓ አገሮች ዕዳ እየገዛ ለተራማጁ መንግሥታት እንዲያስተላልፍ ነው።
እናም መንግሥታቱ የቀውስ ሃገራትን ዕዳ በቀጥታ ሳይገዙ በዚህ መንገድ አውሮፓን ለማገዝ ይቻላሉ ነው የሚባለው። በሌላ አነጋገር ጥቅሙ በተፋጠነ ዕድገት የሚራመዱት ሃገራት በዚህ ዘዴ ከክስረት አደጋ የሚያመልጡ መሆናቸው ነው። ይሁን እንጂ በጀርመን የሣይንስና የፖለቲካ ጥናት ተቋም የዓለምአቀፍ ፊናንስ አዋቂ የሆኑት ሄሪበርት ዲተር በበኩላቸው ሃሣቡን ተግባራዊ አድርገው አይመለከቱትም።

“ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ገንዘብ በማቅረብ ሊያግዝ ይችላል። ተቋሙ ለግሪክ የሚደረግ የዕዳ ምሕረትን አብሮ መሸከሙ ግን በተለይ በአሜሪካ ተቀባይነት አያገኝም፤ እንዲያው የትም የማያደርስ ዕርምጃ ነው”

እንደሚባለው በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ሃገራት በዚህ ዕርምጃ ከሁሉም በላይ የሚያልሙት በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ውስጥ የራሷቸውን ተጽዕኖ ይበልጥ ለማሳደግ ነው። የዶቼ ባንኳን ባለሙያ ማሪያ ላንዜኒን የመሳሰሉ የፊናንስ ገበያ አዋቂዎች ታዲያ የምንዛሪው ተቋም ይልቁንም የገንዘብ እጥረት በሚገጥምበት ጊዜ መሸጋገሪያ ድጋፍ በመስጠት ለመፍትሄው የተሻለ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል ባይ ናቸው።

“በዓለምአቀፉ መስፈርት መሠረት የምንዛሪው ተቋም የብድር አሰጣጥ ሁኔታዎችን በማቃለል የተቸገሩ ሃገራት ያለብዙ ቅድመ-ግዴታ ብድር እንዲያገኙ ማድረግ ይችላል። ይህ ከዚህ ቀደም እ.ጎ.አ. በ 2009 ዓ.ም. ለሜክሢኮ፣ ለፖላንድና ለኮሉምቢያ የተደረገ ነገር ነው። እና ለወደፊትም የመፍትሄ መንገድ ሊሆን ይችላል”

ከብሪክስ ሃገራት መካከል እስካሁን የኤውሮ-ቀውስ መድህን በመሆን ዕርዳታ ላቅርብ ያለችው በተለይም ቻይና ናት። አገሪቱ በ 3,2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን የዓለም የገነዘብ ክምችት የምትቆጠጠር ሲሆን ከዚሁ የተወሰነውን የመንግሥታትን ዕዳ ለመግዛት በተግባር ልታውለው ዝግጁ ናት። እርግጥ በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም፣ ወይም በአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ዋስትና ከተሰጣት! ይሁንና ይህን መሰሉ የገንዘብ አቅርቦት የጀርመን የሣይንስና የፖለቲካ ምርምር ተቋም ባልደረባ ሄሪበርት ዲተር እንደሚሉት አውሮፓም እንደ አሜሪካ ጥገኝነት ላይ እንድትወድቅ የሚያደርግ ስውር አደጋን ያቀፈ ነው።

“አሜሪካውያን ይህን ጨዋታ ሲጫወቱ ብዙ ዓመታት አሳልፈዋል። እናም ዛሬ በቻይና መዋዕለ-ነዋይ ላይ ጥገኞች ናቸው። አሜሪካ ትልቁ ዕዳ ያለባት በቻይና ዘንድ ነው። ታዲያ አውሮፓውያንም ይህን መሻታቸውን ሲበዛ እጠራጠራለሁ”

ቻይናን ካነሣን በአውሮፓና በአሜሪካ የዕዳ ቀውስ ከተከሰተ ወዲህ የፖለቲካው ሃይል ሚዛን በፍጥነት ለሩቅ ምሥራቋ አገርና ለተቀሩት መሰሎቿ የሚያመች ሆኖ ነው አዘንብሏል። የቻይናና የብራዚል የፊናንስ ሚኒስትሮች በቅርቡ የቡድን-ሃያ ስብሰባ በዕዳ ቀውስ ላይ የወደቁትን አገሮች ለመርዳት ዝግጁ ነን ማለታቸው እርግጥ ለአውሮፓውያኑ ገና እየተለመደ መሄድ የሚኖርበት ነገር ነው። የጀርመን የውጭ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ባልደረባ ኤበርሃርድ ዛንድሽናይደር እንደሚናገሩት ሂደቱን ቀድሞ ማንስ አሰበው!

“ዛሬ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት አገሮች ከሃያና ከሰላሣ ዓመታት በፊት ከታላላቆቹ መንግሥታት ጋር እኩል እናወራለን ብለው ሊያልሙ እንኳ ባልደፈሩ ነበር። ሆኖም አሁን ዓለምአቀፉን የምንዛሪ ተቋም የመሰለ አካል በራሳቸው ቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት ጀምረዋል። በነገራችን ላይ አውሮፓውያኑና አሜሪካውያን በበኩላቸው የምንዛሪውን ተቋም ከዕጃቸው የሚያወጣ እንደሌለ አጥብቀው ሲያምኑ ነው የኖሩት”

ዛሬ አውሮፓውያን ማንገራገር ቢይዙም ቻይናን የመሳሰሉት ተራማጅ ሃገራት ለክስረት የተጋለጡትን መንግሥታት ለማዳን ከበስተጀርባ ከአሁኑ የፊናንስ ፓኬት መቋጠር መያዛቸው ነው የሚነገረው። አውሮፓ በራሷ አቅም ችግሩን ትወጣዋለች የሚል ዕምነት የላቸውም። እርግጥ ቻይና በተደጋጋሚ ለመርዳት ዝግጁ መሆኗን ብትገልጽም በሌላ በኩል ጥንቃቄን መምረጧም አልቀረም። አገሪቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የዓለም ግዙፍ የውጭ ምንዛሪ በዕጇ ቢሆንም እስካሁን ለኤውሮው ማዳኛ 300 ሚሊዮን ኤውሮ ብቻ ነው በስራ ያዋለችው። እርግጥ አውሮፓውያን የራሳቸውን የቤት ስራ ራሳቸው ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል። ሆኖም የቻይና ዕርዳታ የግድ ማስፈለጉ ደግሞ የሚቀር አይመስልም። ለነገሩ ቻይናም ራሷን ጭምር ለሚጠቅመው ለዓለም ኤኮኖሚ እርጋታ ስትል ችግሩን ለመፍታት ያላት ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ነው።

ለጊዜው ግን አውሮፓውያን በጉዳዩ የቻይና ሚና መጉላቱን የሚፈልጉት ነገር አይሆንም። ስለዚህም ውጣ ውረዱ ምናልባትም ለጥቂት ጊዜ በዚሁ ይቀጥላል። ግን ሌላ ምን መንገድ አለ? በጀርመን ፌደራላዊ ም/ቤት ቡንደስታግ የአረንጓዴው ፓርቲ ቡድን የፊናንስ ገበያ አዋቂ ጌርሃርድ ሺክ በበኩላቸው መለስ ብለው እንደሚያስታውሱት ከሆነ ቡድን-ሃያ መንግሥታት ገና በ 2008 ዓ.ም. የሌሕማን ብራዘርስ ባንክ እንደከሰረ የፊናንስ ገበዮችን ሂደት ለመቆጣጠር ጥሩ መርህ አስፍኖ ነበር። ግን ዛሬ በተግባር ጥቂት ዕርምጃ ብቻ እንደተደረገ ነው የምንታዘበው። ለምሳሌ የፊናንስ ሽግግር ግብርን በዓለምአቀፍ ደረጃ ለማስፈን የነበረው ዕቅድ በተለይም በአሜሪካና በብሪታኒያ ተጽዕኖ ወደፊት ፈቀቅ አላለም።

“በዚህ ረገድ ስኬት ማግኘቱ አንድ ዕርምጃ በሆነ ነበር። ሌላው በጣም ጠቃሚ ነጥብ ደግሞ እርጋታን የሚያዛቡትን ለምሳሌ ሄድጅ-ፎንድስ፤ በትርፍ ማጋበስ ላይ ያተኮሩ ስውር ባንኮችን መቆጠጠር መቻል ነው። ዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ በዚህ በግብር ጉዳይ ቀድሞ በ 2008 ቀርቦ የነበረውን ሃሣብ ወደፊት ለማራመድ አዲስ ጥረት ማድረግ አለበት”

ያም ሆነ ይህ ማሪያ ላንዜኒን የመሳሰሉት የፊናንስ ገበያ አዋቂዎች የሚያሳስቡት በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ቻይናን የመሳሰሉት ሃገራት ለዕዳው ቀውስ ፈጣን መፍትሄ እንዲገኝ በኢንዱስትሪ ልማት ለበለጸገው ዓለም የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች ለሁለቱም ወገን የሚጠቅሙ ናቸው።

“የመግዛት አቅምን በተመለከተ ዛሬ ተራማጆቹ ሃገራት ከዓለም ኤኮኖሚ ግማሹን ድርሻ ይይዛሉ። በዚህ የተነሣም እዚያ ቀውስ እንዳይደርስ ማድረጉ ለኤውሮ ዞንና ለአሜሪካም የሚበጅ ነው የሚሆነው”

የቡድን-ሃያ መንግሥታት መሪዎች በቅርቡ በፈረንሣይ ሲሰበሰቡ ልዩነቱን በማጥበብ ችግሩን ፍትን በሆነ መንገድ በጋራ ለመቋቋም የሚያስችል አንድነት ማስፈናቸው እጅግ ጠቃሚ ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ


Audios and videos on the topic