ቡድን ሃያና የኤውሮው ቀውስ | ኤኮኖሚ | DW | 29.02.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ቡድን ሃያና የኤውሮው ቀውስ

ቡድን-ሃያ በመባል የሚታወቀው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉና በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ መንግሥታት ስብስብ ተጠሪዎች ባለፈው ሰንበት ሜክሢኮ-ሢቲይ ላይ የሁለት ቀናት ጉባዔ ማካሄዳቸው አይዘነጋም።

ቡድን-ሃያ በመባል የሚታወቀው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉና በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙ መንግሥታት ስብስብ ተጠሪዎች ባለፈው ሰንበት ሜክሢኮ-ሢቲይ ላይ የሁለት ቀናት ጉባዔ ማካሄዳቸው አይዘነጋም። በፊናንስ ሚኒስትሮችና በማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪዎች ደረጃ የተካሄደው ስብሰባ በተለይም የኤውሮን የዕዳ ቀውስ ዋነኛ ማተኮሪያው ሲያደርግ በማዳኑ ተግባር የዓለምአቀፉን ምንዛሪ ተቋም ሚና ለማጠናከር አውሮፓውያን የማዳን ድርሻቸውን ከፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተነግሯል።

ስብስቡ ከሁለት ቀናት ጉባዔው በኋላ ሜክሢኮ-ሢቲይ ላይ ባወጣው የጋራ መግለጫ እንዳሳሰበው የኤውሮ ሃገራት የማዳን ተግባራቸውን በመጪዎቹ ወራት ይበልጥ ማጠናከር አለባቸው። ሜክሢኮ ለነገሩ ከመልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ አንጻር ለአውሮፓ እጅጉን የራቀች ናት።

ይሁን እንጂ ሃያ መንግሥታትን ባሰባሰበው ቡድን ጉባዔ ላይ የአሮጌይቱ ክፍለ-ዓለም ችግር ነው ከሁሉም በላይ ሲያነጋግር የሰነበተው። ለዚህም ምክንያቱ የኤውሮ የዕዳ ቀውስ በብዙዎቹ ከአውሮፓ ውጭ በሆኑ መንግሥታት ዘንድ የዓለም ኤኮኖሚን የሚያሰጋ አደጋ ሆኖ መታየቱ ነው። ይህ በተለይም በአሜሪካ መንግሥት ተደጋግሞ ሲነገር ተሰምቷል።

ከዚህ የተነሣም ባለፉት ጊዜያት ችግሩን ለመቋቋም በቂ አስተዋጽኦ አላደረጉም በሚል በአውሮፓውያንና በተለይም ኤኮኖሚዋ ጠንካራ በሆነው በጀርመን ላይ ወቀሳ ሲሰነዘር መቆየቱ ይታወቃል። ጀርመን ከምዕራባውያኑ መንግሥታት ሁሉ በፍጥነት ከዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀወስ በማገገም በጥሩ የዕድገት ሁኔታ ላይ ነው የምትገኘው። ለዚህም ነው የበለጠ ድርሻ የሚጠበቅባት። ይሁንና የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ በበኩላቸው ይሄው አመለካከት አሁን እየረገበ እንደሄደ ነው የሚናገሩት።

«እንደማስበው አሁን መላው ተሳታፊዎች በአውሮፓ ያደረግነውን ሁሉ በጥሩ ዓይን መመልከት መያዛቸውን በጥቅሉ ለመናገር ይቻላል። በያዝናቸው ማረጋጊያ ዕርምጃዎች በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆናችንን የሚጻረር የተለየ ነገር የለም»

በዕውነትም የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት በዓባል ሃገራቱ ውስጥ የበጀት ቁጥጥርን ለማጠናክርና የዕዳን መጠን ለመገደብ እንዲቻል ጥርጊያን ለመክፈት የወሰዱት ዕርምጃ፤ እንዲሁም በቀውሱ በተወጠሩት በኢጣሊያና በስፓኝ የተያዙት የለውጥ ዕርምጃዎች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዕርካታን ማስከተላቸው አልቀረም።

ለግሪክ አዲስ የዕርዳታ ፓኬት መቋጠሩም እንዲሁ በቂም ባይባል ጥሩ ዕርምጃ ሆኖ ነው የታየው። ሌላው ቀርቶ ለወትሮው የአውሮፓን ሕብረት በመተቸት የሚታወቁት የአሜሪካ የፊናንስ ሚኒስትር ቲሞቲይ ጋይትነር እንኳ አውሮፓውያን ቀውሱን ለመቋቋም ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ብዙ መጣራቸውን ነው የሚመሰክሩት።

«ዕርምጃው ባለፈው 2011 መጨረሻ በፊናንሱ ስርዓት ላይ የተፈጠረውን ከባድ ውጥረት ለማርገብ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነበር። ግን አሁን አውሮፓውያኑ ባሉበት ቆመው መቅረት አለባቸው ማለት አይደለም። ሁኔታው የተረጋጋው ዕርምጃውን አስተማማኝ ለማድረግ በዙ ይክተላል በሚል ተሥፋ ላይ በመመስረት ነው»

እንግዲህ ጋይትነር በአውሮፓውያኑ ላይ ለዘብ ያሉ ቢመስልም እነዚሁ የበጀት ችግር ላይ የወደቁ የኤውሮ ሃገራትን ለማዳን ተጨማሪ ሚሊያርዶችን እንዲያፈሱ መጠየቃቸውን አላቆሙም። አውሮፓውያን ችግራቸውን ለመቋቋም በቂ ጥረት አላደረጉም የሚለው የዋሺንግተን አቋም ምናልባት ለዝቦ እንደሆን እንጂ ጨርሶ አልተወገደም ማለት ነው።

ይህ አመለካከት በተፋጠነ ዕድገት ላይ በሚገኙት የቡድን-ሃያ ዓባል ሃገራት በቻያና፣ ብራዚል፣ ሜክሢኮና መሰል ሃገራት ዘንድም የተስፋፋ ሆኖ ነው የቆየው። ለምሳሌ የጉባዔው አስተናጋጅ አገር የሜክሢኮ ፊናንስ ሚኒስትር ሆሴ-አንቶኒዮ-ሜአዴ እንዲሁም የካናዳና የጃፓን መሰሎቻቸውም ያንኑ ነው የሚናገሩት። በወቅቱ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክም ወደዚሁ ያዘነበለ ነው።

«እኛ እንደ አውሮፓ ማዕከላዊ ባንክነታችን የገበያው ሁኔታ እየተሻሻለ ቢመጣም ማዳኛው ገንዘብ የመጨመሩን አስፈላጊነት ተናግረናል። እንግዲህ የምንመርጠው ማዳኛው ግምብ ከፍ እንዲል ነው»

ይህን የሚሉት እስከ ቅርቡ በጀርመን ፊናንስ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ሚኒስትር-ዴኤታ የነበሩት የወቅቱ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ አስተዳደር ዓባል ዮርግ አስሙሰን ናቸው። በአሕጽሮት OECD በመባል የሚታወቀው የአውሮፓ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ሃላፊ አንሄል ጉሪያ እንዲያውም መሰላሉን ከፍ አድርገው ሰቅለውታል። የአውሮፓ ሕብረት ድርሻ በርሳቸው አባባል ከሆነ ገና ብዙ ነው የሚቀረው።

ባለሥልጣኑ በጉባዔው ላይ ሲናገሩ የአውሮፓ መድህን ገንዘብ በሰፊው ከፍ እንዲል ነበር ያሳሰቡት። በርሳችው አባባል እርጋታን ለማስፈን እንዲቻል የሚያስፈልገው ገንዘብ 1,5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚጠጋ ነው። ይህ ደግሞ በአውሮፓ ሕብረትና በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ከተመደበው ሶሥት ዕጅ ይበልጣል። በወቅቱ ሁኔታ ከየት እንደሚመጣም አይታወቅም።

ለማንኛውም የምንገነባው መከላከያ ግንብ ወፍራም በሆነ መጠን ልንጠቀምበት መቻላችንም አስተማማኝ ይሆናል ነው ያሉት ጉሬያ። አስተናጋጇ አገር ሜክሢኮ ዘንድሮ የስብስቡ ሊቀ-መንበር ስትሆን በጉባዔው የተሳተፉት የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪ አጉስቲን ካርስተንስም በፊናቸው አውሮፓውያን ለምንዛሪው ተቋም የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ከፍ እንዲያደርጉ ነው ያሳሰቡት። አለበለዚያ ሌሎቹ ሃገራት ለቀውስ መከላከያው ግንብ ድርሻቸውን እንዲወጡ መጠየቅ አይቻልም።

የአሜሪካው ፊናንስ ሚኒስትር ቲሞቲይ ጋያትነር እንደሚሉትም የበጀት ቀውሱን ለማስወገድ የበለጠ ገንዘብ የማቅረቡ ተራ በወቅቱ የአውሮፓውያኑ የራሳቸው ነው። ሚኒስትሩ በተለይም በኤኮኖሚዋ ጠናካራ የሆነችው ጀርመን ለዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የምትሰጠውን ገንዘብ ከፍ እንድታደርግ እንደገና ጠይቀዋል።

እርግጥ ጥሪው የርሳቸው ብቻ አልነበረም። ጀርመን በአውሮፓ ያላትን ግንባር-ቀደም ሚና ልብ በማለት መላውን የኤውሮ-ዞን የጠቀለለ ዕቅድ እንድታቀርብ ነው የካናዳው ፊናንስ ሚኒስትር ጂም ፍላኸርቲም ያስገነዘቡት። ከዚህ በኋላ መርዳት በሚቻልበት ሁኔታ ለመወያየት ዝግጁነት መኖሩ ነው ከጃፓን በኩል ደግሞ የተገለጸው።

የጀርመን መንግሥት በበኩሉ የበለጠ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የተያዘውን ግፊት እንደማይቀበል ሲያስገነዝብ ቆይቷል። ነገር ግን አሁን ጀርመን በዚህ ረገድ የሚደረገውን ገፊት ለመቋቋም የምታደርገው ጥረት የአገሪቱ ፊናንስ ሚኒስትር ቮልፍጋንግ ሾይብለ እንደሚሉት እየለዘበ ሲሄድም እየታየ ነው።

«አውሮፓ ውስጥ የምናደርገውን ውሣኔ በፊታችን መጋቢት ወር ሂደት እንደገና መልሰን እንመረምራለን። በወቅቱ የተከሰቱትን ለውጦች አጢኖ አጠቃላዩ የማዳን ጥረት ይብቃ-አይብቃ መለየቱና ተገቢውን ዕርምጃ መውሰዱ አስፈላጊ ነው»

ይህ ደግሞ ዓለምአቀፍ ድጋፍን ለማግኘት እንዲቻል ሳይዘገይ ገቢር መሆን ይኖርበታል። አውሮፓውያኑ መንግሥታት ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF ቀውሱን ለመታገል የሚያቀርበውን ገንዘብ ከ 500 እስክ 600 ሚሊያርድ ዶላር ከፍ እንዲያደርግ ይፈልጋሉ። አብዛኞቹ ከአውሮፓ ውጭ የሆኑ የቡድን-ሃያ ዓባል መንግሥታትም በመሠረቱ ለዚሁ ዝግጁ ናቸው። ሆኖም ግን አውሮፓውያኑ የራሳቸውን ቀውስ መከላከያ ከፍ ማድረጋቸውን ቅድመ-ግዴታ ያደርጋሉ።

የጀርመን ፌደራል ባንክ ፕሬዚደንት የንስ ቫይደማን በበኩላቸው እንደሚሉት የአውሮፓን የዕዳ ቀውስ ለማስወገድ በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የሚደረግ የገንዘብ ማጠናከሪያ ዕርምጃ ጊዜ ከማግኘት አልፎ በራሱ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። እናም ይሄው ጊዜ ችግሩን ከስር መሠረቱ ለመታገል ጥቅም ላይ ሊውል ይገባዋል። በባለሙያው አነጋግር አውሮፓውያኑ መንግሥታት በዚሁ ጊዜ በተጨባጭ ጊዜውን ብሄራዊ የፊናንስ ይዞታቸውን ለማረጋጋት፣ መዋቅራዊ ለውጦችን ለማካሄድና የተሻሉ ደምቦችን ገቢር ለማድረግ ቢጠቀሙበት ገንቢ ነው።

አለበለዚያ ገንዘብ በመርጨት ብቻ ቀውሱን ለማሸነፍ አይቻልም። የምንዛሪው ተቋም ያቅርብ ከተባለው 600 ሚሊያርድ ዶላር 200 ሚሊያርዱ የሚመነጨው ከአውሮፓ ነው። እስካሁን 386 ሚሊያርድ ዶላር ከድንገተኛው ጊዜ ካዝና ውስጥ ገብቶ ይገኛል። በወቅቱ የሚታየው የምንዛሪው ተቋም ጠንካራ የገንዘብ ድርሻና መጠናከር አውሮፓን ብቻ ሣይሆን መላውን ዓለም እንደሚጠቅም ነው የሚታመነው።

ሆኖም የሜክሢኮው ፊናንስ ሚኒስትር ሆሴ-አንቶኒዮ-ሜአዴ በቡድን-ሃያው ስብሰባ ዋዜማ ባለፈው አርብ እንደገለጹት ጭብጥ አሃዝ ለመጥቀስ ገና ጊዜው አይደለም። ባለፈው ሰንበት የሜክሢኮ-ሢቲይ የቡድን-ሃያ ጉባዔም ይህን መሰሉን ውጤት የጠበቀው ማንም የለም። ምናልባት የምንዛሪው ተቋም በፊታችን ሚያዚያ ወር ዋሺንግተን ላይ በሚያካሂደው ስብሰባ ጭብጥ ውሣኔ ይገኝ ይሆናል። ይህ ለነገሩ የጀርመኑ ፊናንስ ሚኒስትር የሾይብለም ጽኑ ዕምነት ነው።

«በዛሬው ክርክር ላይ ይህንኑም ጨምሬ ነው የተናገርኩት። በመጪው የቡድን-ሃያ ስብሰባ በአውሮፓ ነክ ችግሮች ላይ በዙ ማውራት እንደማይኖርብን አምናለሁ»

ይህ ቢሆን ቡድን-ሃያ ወደ ዋና ተግባሩ መመለስና በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ማተኮር ይችላል ማለት ነው። በሌላ በኩል የኤውሮ-ዞን ሁኔታ በአማካይና በረጅም ጊዜ ምን መልክ ይዞ እንደሚቀጥል በወቅቱ በትክክል ለመናገር አይቻልም። ግሪክን ከለየለት ክስረት ለማትረፍ የተወጠነው የ 130 ሚሊያርድ ኤውሮ ሁለተኛ የዕርዳታ ፓኬት ቢቋጠርም አገሪቱ በዚህ ከችግሯ መላቀቋ ጨርሶ አይታመንም።

ይበልጡን ጭብጥ ነግር የሚመስለው አገሪቱ ገና ሌላ የረጅም ጊዜ ዕርዳታ የሚያስፈልጋት መሆኑ ነው። ሃቁ ይህ ሲሆን ግሪክ ከኤውሮ-ዞን ዓባልነቷ እንድትወጣ ቢደረግ መዘዙ ተስፋፍቶ የበጀት ችግር ያለባቸውን ፖርቱጋልን፣ ስፓኝን ወይም ኢጣሊያን ቢያንከረባብትስ? ይህ ሊያጋጥም አይችልም አይባልም። እርግጥ የአውሮፓ ሕብረት በውቅቱ አጥብቆ የሚፈራው ይህን መሰሉን ክስተት ሲሆን እንደ አማራጭ የመፈራረሱን ሂደት የሚገታ የፊናንስ ግንብ ለማቆም መጣሩም አልቀረም።

ለግሪክ ክስረቱ ቢከተል ደቡብ አውሮፓይቱን አግር ከለየለት የኤኮኖሚ ቀውስ ላይ የሚጥል ነው የሚሆነው። መንግሥት ተቀጣሪዎቹን ደሞዝ መክፈል አይችልም፤ ኩባኒያዎች ተራ በተራ በድን ይሆናሉ፤ የውሃና የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሳይቀር ሊሰናከል እንደሚችል ነው የሚጠበቀው። ይህ ደግሞ ከኤውሮ-ዞን መውጣትንም በማስከተል ችግሩን ያባብሰዋል። እንደ ዕውነቱ ከሆነ ባያስቡት የሚሻል ነገር ነው።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 29.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14BbG
 • ቀን 29.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14BbG