ቡድን ሀያ እና የአፍሪቃ ተስፋ | አፍሪቃ | DW | 08.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ቡድን ሀያ እና የአፍሪቃ ተስፋ

አፍሪቃ በመሠረተ ልማት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም መስኮች ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል። በጎርጎሮሳዊው 2050 የክፍለ ዓለሙ ህዝብ ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል። ሥራ አጥነት የክፍለ ዓለሙ አንዱ ችግር ነው። ከ«ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ» ውጥኖች አንዱ የሥራ እድሎችን መፍጠር ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:01

ቡድን ሀያ እና የአፍሪቃ ተስፋ

ቡድን ሃያ የሚባለው የበለጸጉ ሃገራት ስብስብ፣  ከአሁኑ በበለጠ በአፍሪቃ የውጭ ባለሀብቶችን የግል ውረታ ማበረታታት ይፈልጋል። ዓላማው ክፍለ ዓለሙን ማልማት እና ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር ነው ተብሏል። ቡድን ሃያ ስለነደፈው ስለዚህ እቅድ አፍሪቃውያን ምን ይላሉ ? የዶቼቬለው ዳንኤል ፔልስ በዚህ ላይ አትኩሮ ያዘጋጀውን ዘገባ ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች።
የቡድን ሀያ እና የአፍሪቃ ሀገራት ፣ ቡድን ሀያ ለአፍሪቃ ልማት በነደፈው እቅድ ላይ የፊታችን ሰኞ እና ማክሰኞ በርሊን ጀርመን ይነጋገራሉ። በክፍለ ዓለሙ የውጭ የግል መዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ለማበረታታት እና የሥራ እድሎችንም ለመፍጠር ያስችላል ስለተባለው ስለዚህ እቅድ አፍሪቃውያን የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ነው።  ሲዲ ቲሞኮ የኮት ዲቯር የወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ናቸው። በበርሊኑ ስብሰባ ላይ ለሀገራቸው የሥራ አጥነት ችግር መፍትሄ ፍለጋ እርዳታ ለመጠየቅ አስበዋል። እርሳቸው እንደሚሉት የሀገሪቱ ወጣቶች በአደገኛ የባህር ጉዞ ለሞት መዳረጋቸው መገታት አለበት። ከኮት ዲቯትር ሕዝብ ግማሽ ያህሉ ከድህነት ወለል በታች የሚባል ሕይወት ነው የሚገፋው። ከሕዝቡ 60 በመቶው ዕድሜው ከ24 ዓመት በታች ነው። ለወጣቶች በቂ የሥራ ዕድልም የለም።  እናም የኮት ዲቯር መንግሥት በሚቀጥለው ሳምንት ከቡድን ሃያ ጋር የሚካሄደው ስብሰባ ብዙ ለውጦችን ሊያመጣ ይችላል የሚል ተስፋ አለው። ኮት ዲቯር ቡድን ሃያ በነደፈው ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ በተባለው የልማት እቅድ ውስጥ ከታቀፉት ሃገራት አንዷ ናት። በእቅዱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ቡድን ሃያ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋሉ። ባለሀብቶችን በመፈለግም ይሳተፋሉ። አፍሪቃውያን ደግሞ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚያስችሉ ለውጦች ለማድረግ ቃል ገብተዋል። ከእቅዱ ትኩረቶች ዋነኛ በክፍለ ዓለሙ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት ነው። ናይጀሪያዊው የልማት ጉዳዮች ተመራማሪ ኮሌ ሸቲማ እንደሚሉት ይህ ለክፍለ ዓለሙ ኤኮኖሚ እድገት ወሳኝ ነው። 
«በአካባቢው ከፊታችን ከተጋረጡት ችግሮች ዋነኛው የመሠረተ ልማት ችግር ነው። ኤልክትሪክ ይሁን መንገድ፤ የባቡር ሀዲድ ወይም የውኃ አቅርቦት። እነዚህ የክፍለ ዓለሙ ዋነኛ የመሠረተ

ልማት ጉድለቶች ናቸው።  ከነዚህ ችግሮች የተወሰኑትን እንኳን ማቃለል ብንችል የክፍለ ዓለሙ ኤኮኖሚ ሊለወጥ ይችላል።»
አፍሪቃ በመሠረተ ልማት ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም መስኮች ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል። በጎርጎሮሳዊው 2050 የክፍለ ዓለሙ ሕዝብ ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል። ሥራ አጥነት የክፍለ ዓለሙ አንዱ ችግር ነው። ከ«ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ» ውጥኖች አንዱ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ነው። እቅዱ ጥሩ መሆኑን የሚናገሩት ሌላው የአፍሪቃ ልማት ባለሞያ ማርቲን ሶንኩ የታሰበለትን ግብ ማሳካቱን ይጠራጠራሉ። በርሳቸው አስተያየት ስኬቱን የሚወስነው እቅዱ የሚተገበርበት መንገድ ነው።
« የግል ባለሀብቶች ውረታዎች ሥራ ይፈጥራሉ ሲባል ምን ዓይነት ሥራዎች ነው የሚፈጥሩት ? እና ሥራውስ በምን መንገድ ነው ወደ አፍሪቃ የሚመጣው? ይህ  መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው። ይህ እቅድ ሊያካትት ይገባ የነበረው አንዱ ጉዳይ ወደ አፍሪቃ የሚመጣው የውጭው ውረታ የየሐገሩን የግል ዘርፍ ሊያነቃቃ የሚችልበት መንገድ መሆን ያለበት ይመስለናል። ይህን ግን በእቅዱ ውስጥ አናይም።» 
ሌላው በእቅዱ ላይ የቀረበው ትችት ተጨማሪ የንግድ እንቅስቃሴ ለሚያስፈልጋት ለአፍሪቃ የሚጠቅም የንግድ ፖሊሲ መዘንጋቱ ነው። እንደ ልማት ባለሞያዎቹ ሁሉ ነጋዴዎችም እቅዱ ይጎድለዋል ከሚሉት ጉዳዮች አንዱ ይህ ነው። ጋናዊው ነጋዴ ቱቱ አጋይሬ ችግሩን በምሳሌ ነው ያስረዱት።
«ያመረትኩትን ጥሬ ካካዎ ስሸጥ የአውሮጳ ኅብረት ያለ ቀረጥ ያስገባልኛል። ሆኖም ቼኮላታ አምርቼ ለአውሮጳ ኅብረት ለመሸጥ ብሞክር 30 በመቶ ቀረጥ አለ። ከጀርመን ወደ አፍሪቃ የሚመጣው ኮምፓክት ሆነ ቡድን ሃያ በዚህ ረገድ እስካሁን የሚደረገውን ለመለውጥ አልተዘጋጁም። እኔ መንቀሳቀስ እንድችል ቡድን ሃያ የተለመዱትን አሠራሮች ለመቀየር ምን ዝግጅት አድርጓል?»
ሲሉ ነጋዴው ይጠይቃሉ ። የአፍሪቃ ሃገራት እና በእቅዱ የሚሳተፉ አጋሮች በሚቀጥለው ሳምንት የሚደርሱበት ስምምነት በጉጉት እየተጠበቀ ነው። ከዚያ በኋላ ብቻ ነው«ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ »ለአፍሪቃ ኤኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ማድረግ መቻል አለመቻሉ ግልጽ ሊሆን የሚችለው።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች