ቡናን ወደ ዉጭ መላክ የጀመሩ አርሶ አደሮች | ኤኮኖሚ | DW | 06.02.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

ቡናን ወደ ዉጭ መላክ የጀመሩ አርሶ አደሮች

ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ከፍተኛ መጠን ያለዉ የቡና ምርት ከሚያቀርቡ ሀገሮች አንዷ ናት። የቡና አምራቶች የምርቱን ያህል በገበያ ተጠቃሚ አለመሆናቸዉ ይነገራል። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የግብይት ሰንሰለት ጠብቆ ለዓለም ገበያ ከሚቀርበዉ ቡና አምራቹ አርሶ አደር 35 በመቶ ብቻ ተጠቃሚ ነዉ። ቀሪዉን 65 በመቶ በግብይት ሰንሰለት ያሉ ይጠቀማሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:09

ቡና በማምረት እና መላክ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች

ኢትዮጵያ የአፍሪካን አጠቃላይ የቡና ምርት 40 ከመቶ ገደማ የመሸፈኗን ያህል በዚሁ መጠን ምርቱን ወደ ዓለም ገበያ ማቅረብ ብትችል እጅጉን ተጠቃሚ ትሆን እንደነበር ይነገራል። የተሻለ የውጭ ምንዛሪ በማግኘትም በኢኮኖሚዋ ላይ ልዩነት መፍጠር የሚያስችል አቅም መገንባት ትችል እንደነበርም በዓለምአቀፍ ደረጃ በቡና ምርት እና ግብይት ላይ ከሚወጡ ተከታታይ መረጃዎች መገንዘብ ይቻላል።
ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት በኢትዮጵያ ውስጥ የመመረቱን ያህል ወደ ዓለም ገበያ ቀርቦ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚደጉመው ከአጠቃላይ ምርት በአማካይ ከ40 በመቶ እምብዛም እንደማይሻገር ነው ጥናቶች የሚያመለክቱት። ለዚህ ደግሞ በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የቡና ፍላጎት መኖሩ እና የሚመረተው ቡና በጥራቱ በዓለም ገበያ ያለው ተወዳዳሪነት የምርቱን ያህል አለመሆኑም ነው የሚጠቀሰው።

Kaffebauer mit Kaffepflanze im Jemen (Maskal/Langenbahn)


በእርግጥ የቡና ምርት የጥራት ችግር ለአረቢካ ቡና መገኛ ሀገር የቆየ ተግዳሮቷ ስለመሆኑ ወደ ፊት አልራመድ ያለው ዘልማዳዊ የቡና ልማት በረዥሙ የገበያ ሰንሰለት ውስጥ አልፎ ገበያውጋ እስኪደርስ ባለው ሂደት ለጥራቱ ትኩረት ለመስጠት አስቻይ ሁኔታዎች እምብዛም በመሆናቸው ተገቢው ውጤት ሳይገኝበት ዘመናትን ተሻግሯል።
የግብይት ሰንሰለቱን ጠብቆ ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው ቡና አምራቹ አርሶአደር ከ35 -40 በመቶ የሚሆነውን ገቢ መጋራት እንደሚችል ነው ጥናቶች የሚያመክቱት። ከ60-65 በመቶ የሚሆነውን የገበያውን ዋጋ በዚሁ የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑት ነጋዴዎች ይቀራመቱታል ማለት ነው።
አሁን አሁን በጥቂት አርሶአደሮች እና የአርሶ አደር ማህበራት አማካኝነት የቡና ምርታቸውን በራሳቸው ለዓለም አቀፍ የቡና ገዢዎች ማቅረብ መጀመራቸው አዲስ የኢኮኖሚ ትሩፋት ይዞላቸው ስለመምጣቱ እነዚሁ አርሶ አደሮች ይናገራሉ። ረዥሙ የገበያ ሰንሰለት አጥሮ በቀጥታ መገናኘታቸው ደግሞ ለቡና ልማቱም ሆነ ጥራቱን ለመጠበቅ አይነተኛ አቅም ሆኖናል ይላሉ።
አቶ ሙስጠፋ አባ ሉሌሳ በጅማ ዞን ጎማ ወረዳ ሆማ ፉንጡሌ ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው። ከአባታቸው ባገኙት ጥቂት የቡና መሬት ውርስ ላይ በራሳቸው በማስፋፋት 41 ሄክታር መሬት ላይ ቡና ያለማሉ። ይህንኑ የቡና ምርታቸውን በተለመደው መንገድ ለገበያ ሲያቀርቡ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ከዓመት ዓመት ተመሳሳይ እና ወደ ፊት ፈቀቅ የሚያደርግ ሁኔታ እንዳልነበረ ይናገራሉ በገቢው ረገድ ማለት ነው።  ድንገት ግን መንግስት ከሁለት ሄክታር በላይ የቡና ልማት ያላቸው አርሶአደሮች ቡናቸውን ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ህግ ሲያወጣ የገበያውን ሰንሰለት አስቀርቶ የዓለም ገበያ ደጄ ድረስ መጣልኝ ይላሉ።
በቡና ምርቱ ተገቢውን ዋጋ ማግኘት ከተቻለ ልማቱን ለማስፋት እና ጥራቱን በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ አቅም ፈጥሮልኛል ይላሉ። ነገር ግን የገበያው ወጥ አለመሆን እና የመለዋወጥ ባህሪ አማራጭ ገበያ በማፈላለግ ሂደት አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ።
አርሶ አደሩ የጠለቀ የንግድ ዕውቀት ሳይኖራቸው ጥራቱን የጠበቀ ቡና ብቻ በማምረታቸው ገዢው ራሱ ፈልጎ እንዲመጣ ማድረግ ችለዋል። ቡናውን ሸጠው በቀጥታ ከሚያገኙት ገቢ ባሻገር የቡና ምርታቸውን ከሚያቀርቡበት ሀገር የቡና ማጠቢያ ማሽን በስጦታ እንደተበረከተላቸው ነው የሚያስረዱት።
ቡና በባህሪው ከለቀማው ጀምሮ እስከ ገበያ መዳረሻው እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ የምርት አይነት ስለመሆኑ የመስኩ ባለሞያዎች ያሳስባሉ። ከተለያዩ የቡና ማሳዎች ተሰብስቦ በአንድ ስፍራ በማከማቸት ለገበያ ማቅረብ ጥራቱን መጉዳቱ ስለማይቀር የሚገባውን ዋጋ እንዳያገኝ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽዖ ያበረክታል። አርሶ አደሩ በአንድ ማሳ የሚያመርተውን ቡና በጥንቃቄ አዘጋጅቶ ለገበያ ማቅረብ ከቻለ በዚያው ልክ በገበያው ተፈላጊ ይሆናል፤ የተሻለ ገቢ ማግነት እንደሚችልም በማሳያነት የጠቀስናቸው አርሶ አደር አስረጅ ናቸው።
በኢትዮጵያ የቡና ንግድ ሰንሰለት በህጋዊ መንገድ ለገበያ የሚቀርበው ቡና የሀገር ውስጥ የገበያ መዳረሻው የምርት ገበያ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ለምርቱ ደረጃ ያወጣለታል፤ በወጣው ደረጃ መሰረት ግብይቱ ይከናወናል። በዚህ ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑት ደግሞ የቡና ንግድ ፈቃድ ያላቸው እና በድርጅቱ ውስጥ ቦታ ያላቸው የቡና ነጋዴዎች ናቸው።
በምርት ገበያ ድርጅት የጅማ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ በየነ አለማየሁ እንደሚሉት በሂደት እየተስተካከለ የሄደው የቡና አቅራቢ እና ላኪ ህጉ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ አድርጎታል።  ህጉ ቀደም ሲል ፈቃድ ያለው የቡና ነጋዴ በትንሹ 60 ኬሻ ቡና በቀጥታ ለገበያ እንዲያቀርብ ይፈቅድለታል። በሂደት ግን ወደ 30 እና 20 ኬሻ ድረስ ዝቅ እንዲል የተደረገውን ቡና የማቅረብ ህግ ማንኛውንም ሁለት እና ከዚያ በላይ ሄክታር የቡና ማሳ ላላቸው አርሶአደሮች የተለየ ጥቅምን ይዞላቸው እንደመጣ ነው የሚያስረዱት። አርሶአደሩ በአንድ ማሳ የተመረተ አንድ ወጥ የሆነ የቡና ምርትን በቀጥታ ለዓለም ገበያ እንዲያቀርብ መንገድ ከፍቶለታል ይላሉ።
በጅማ ዞን እንዲህ በግላቸው ገበያውን ሰብረው በመግባት ጥቅማቸውን ለማስከበር ሁኔታዎች የተመቻቹላቸው አርሶ አደሮች የመኖራቸውን ያህል በአነስተኛ ማሳ ላይ ቡና የሚያመርቱ አርሶአደሮችም በመሰረቷቸው ማህበራት አማካኝነት ምርታቸውን በቀጥታ ለዓለም ገበያ ማቅረብ እና የተሻለ ጥቅም ማግኘት መጀመራቸውም እየተነገረ ነው ። በዚህኛው መንገድ ደግሞ በአነስተኛ ማሳ ላይ ጥቂት የቡና ምርት ያላቸው አርሶአደሮች በፈጠሩአቸው ማህበራት አማካኝነት ነው ወደዚህ መስመር መግባት የቻሉት። ለዚህ ደግሞ እስከ 40,000 የሚደርሱ አርሶ አደሮችን ከተለያዩ ማህበራት በአንድነት ያቀፈው አጋሮ ከተማ የሚገኘው የከታ ሙዱጋ የቡና አምራች አርሶ አደሮች ዩኒየን አንዱ ነው። ዩኒየኑ ያለፉትን ሦስት ዓመታት የቡና ምርቱን በቀጥታ ለአሜሪካ አውሮፓ እና የኤሽያ ገበያዎች ሲያቀርብ ቆይቷል። የዩኒየኑ ስራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ ንጋት እንደሚሉት ዩኒየኑ ምርቱን በቀጥታ ለአለም ገበያ ማቅረብ ከጀመረበት ያለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ በየአመቱ እመርታን እያስመዘገበ ስለመሆኑ ነው። 
ዩኒየኑ  በ2019/2020 የቡና የምርት ዘመን ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው ቡና 15 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዱንም ነው አቶ አስናቀ የነገሩን። በዚህም የአርሶ አደሩ የትርፍ ክፍያ መጠን በየዓመቱ ጭማሪ እያሳየ ስለመምጣቱም ነው የገለጹት። የተንዛዛ የገበያ ሰንሰለት ቀርቶላቸው በራሳቸው በቀጥታ ገበያው ውስጥ መግባታቸው አርሶ አደሩ በተናጥል ከሚያገኘው የትርፍ ክፍፍል ባሻገር በአካባቢያቸው በሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ መሆን የሚያስችላቸውን አቅም እየፈጠረላቸው ስለመሆኑም ይገልጻሉ። 
አርሶ አደሩ የቡና ምርቱን በቀጥታ ለዓለም ገበያ እንዲያቀርብ የሚፈቅደው ህግ ስራ ላይ መዋሉ ከቡና ልማት ወደ ሌሎች የእርሻ ስራዎች ፊታቸውን አዙረው የነበሩት አርሶ አደሮች ተመልሰው እንዲመጡ ዕድል እንደፈጠረላቸው ነው የጅማ ዞን የእርሻና ተፈጥሮ ጥበቃ ጽህፈት ቤት የሚገልጸው። ቡና በማምረት እና መላክ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱንም የቡና አምራች አርሶአደሮችን ለማሳያነት የመረጥነው የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ረጋሳ የነገሩን። 

Mischwald in Santong, Lombok (DW)


እዚህ ጀርመን በሚገኙት ሰፊ የገበያ ድርሻ ባላቸው የሬቬ እና አልዲ የገበያ ማዕከላትን ጨምሮ ጀርመኖቹ ባዮ ማርክት የሚሏቸው በተፈጥሯዊ መንገድ የተመረቱ የዕጽዋት እና የእንስሳት ተዋጽዖ መሸጫ የገበያ ማዕከላት ውስጥ በተለይ ከምስራቅ አፍሪካ የገቡ የኢትዮጵያ እና የኬኒያ ቡናዎች የተሻለዋጋ ተቆርጦላቸው አይቻለሁ። አንድ ኪሎ ተቆልቶ እና ተፈጭቶ ታሽጎ የቀረበ ቡና እስከ 19 ኦይሮ ከ96 ሳንቲም ድረስ ዋጋ ወጥቶለታል። የቡና ምርቷን በገፍ ለገበያ የምታቀርበው የብራዚል ቡና በኪሎ ግራም ከ 5 ኦይሮ ጀምሮ እስከ 12  ኦይሮ ድረስ ዋጋ ወጥቶለታል። ልዩነቱ ግልጽ ነው ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች በምድራቸው በተፈጥሮ የተገኘውን ቡና የተፈጥሮ ሚዛኑን ሳያዛቡ እና በጥራት ማምረት ከቻሉ ገበያው ላይ ተፈላጊ ስለመሆናቸው ማሳያ ነው። ነገር ግን ጥሬ ቡና አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ብቻውን ተጠቃሚነትን አያረጋግጥም ። ምክንያቱም ቡና አምርተው ወደ ገበያ ከሚያቀርቡት ይልቅ ቡናውን ዕሴት ጨምረው እና አዘጋጅተው ለገበያ የሚያቀርቡት የተሻለ ጥቅም ስለማግኘታቸው ከገበያው ዋጋ መረዳት ይቻላል። በዚህ ረገድ ኬኒያ የተሻለ አቅም እንዳላት ይነገርላታል። በኢትዮጵያ አርሶ አደሩ ከገበያው ጋር እንዲተዋወቅ ዕድል የማግኘቱን ያህል የቡና ማዘጋጃ እና ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረቡ የገበያ ሰንሰለቱን የበለጠ በማሳጠር ዳጎስ ያለ ገቢ የሚገኝበትን ዕድል ማስፋት እንደሚቻል መገንዘብ ይቻላል። 


ታምራት ዲንሳ


አዜብ ታደሰ
 

Audios and videos on the topic