ቡሩንዲ እና የተመድ ቡድን ወቀሳ | አፍሪቃ | DW | 09.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ቡሩንዲ እና የተመድ ቡድን ወቀሳ

የተመድ የቡሩንዲ መንግሥት ላይ ከባድ የመብት ጥሰት ወንጀል ፈጽሟል ሲል ከባድ ወቀሳ በመሰነዘር፣ ጉዳዩ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ ሀሳብ አቅርቧል። ቡሩንዲ ግን ወቀሳውን በአንፃሯ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ነው ስትል ውድቅ አድርጋዋለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:16
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:16 ደቂቃ

ቡሩንዲ የተመድን ወቀሳ ውድቅ አደረገች።

የተመድ የቡሩንዲ መንግሥት አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅሟል ሲል ወነጀለ። የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን እንደሚወዳደሩ ካስታወቁ ከሚያዝያ 2015 ዓም በኋላ በሀገሪቱ በተካሄደው ተቃውሞ ወቅት ከፀጥታ ኃይላት ጋር በተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭት ከ500 እስከ 2000 የሚሆን ሰው መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ነበር የተመ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት መስከረም፣ 2016 ዓም የቡሩንዲን ጉዳይ የሚመረምር ሶስት አባላት ያሉት አንድ መርማሪ ቡድን የሰየመው። 

ኮሚሽኑ ተቃውሞ የወጡ ለተገደሉበት ተግባር  የሀገሪቱን መንግሥት  ተጠያቂ  አድርጓል። ይሁንና፣ ሶስቱ የተመድ መርማሪዎች የቡሩንዲ መንግሥት የመግቢያ ቪዛ ስለከለከላቸው ወደዚችው ሀገር በመጓዝ ምርመራቸውን ለማካሄድ አልቻሉም። ስለዚህ  በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ላደረጉት የምርመራ ውጤት መረጃቸውን ያሰባሰቡት ወደ ቡሩንዲ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ከ500 የሚበልጡ የቡሩንዲ ስደተኞችን በማነጋገር ነው። ውዝግቡ ከሁለት ዓመት በፊት ከተነሳ ወዲህ ወደ 400,000 የቡሩንዲ ዜጎች ከሀገራቸው ሸሽተዋል። በተመድ ግምት መሰረት፣ እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም ቁጥራቸው ወደ ግማሽ ሚልዮን ይደርሳል። መርማሪዎቹ ባወጡት የምርመራ ውጤት ብዙዎቹ  የቡሩንዲ መንግሥት የኃይል ርምጃ  ሰለባ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቃውሞ ለማሰማት አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች፣ የመንግሥት ተቃዋሚዎች፣ ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟጋቾች  የቁም ስቅል ማየታቸውን እና የፖሊስ የዘፈቀደ እስራት እና እገታ ሰለባ መሆናቸውን የተመድ መርማሪ ኮሚሽንን የመሩት ፋታህ ኡጉዌርጉዝ አስታውቀዋል።

 

«ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሱት ርምጃዎች የተፈጸሙት በቡሩንዲ የስለላ ድርጅቶች፣ በብሔራዊ ፖሊስ፣ በፀጥታ ኃይላት እና በጦር ኃይሉ ወኪሎች ነው። ይሁንና፣ በተወሰኑ የመብት ጥሰቶች ኢምቦኔራኩሬ በመባል የሚታወቁት የገዢው ሲኤንዲዲ-ኤፍዲዲ የወጣቶች ሊጋ ሚሊሺያዎችም  በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳታፊዎች ነበሩ።»

ብዙዎቹ ስደተኞች በቡሩንዲ ጥሰት ፈጻሚዎቹን ለፍርድ የሚያቀርብ ነፃ አካል እንደሌለ ቃላቸውን ለመርማሪዎቹ በሰጡበት ጊዜ ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ የተመድ ዘገባን ያወጡት መርማሪዎች ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ እና ተከታዮቻቸው የፀጥታ ኃይላት ለፈጸሙት ጥሰት መቀመጫውን በዘ ሄግ ኔዘርላንድስ ባደረገው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት፣ አይሲሲ በኃላፊነት እንዲጠየቁ ሀሳብ አቅርበዋል። ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የቡሩንዲን ጉዳይ ለመመለከት ከወሰነ ባፋጣኝ ርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፣ ምክንያቱም፣ ቡሩንዲ ባለፈው ጥቅምት፣ 2016 ዓም ከአይሲሲ እንደምትወጣ በማስታወቋ ይኸው ውሳኔዋ ከሚቀጥለው ጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል። ይህ ዕለት ካለፈ አይሲሲ በቡሩንዲ ላይ ክስ ሊመሰርት የሚችለው በተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ትዕዛዝ ብቻ ነው።

የመርማሪው ቡድን ያቀረበውን ወቀሳ ግን የቡሩንዲ መንግሥት ወቀሳውን ዓለም አቀፉ ማህበ,ረሰብ በሀገሩ ላይ ሆን ብሎ ያቀረበው ከመሆኑም በላይ ኮሚሽኑ ወገንተኛ እና ያዘረበው የምርመራ ውጤትም ፖለቲካዊ ምክንያት ያለው ነው በሚል አጣጥሎታል።
በዚህም የተነሳ፣ የቡሩንዲ መንግሥት የራሱን መርማሪ ኮሚሽን ለማቋቋም መወሰኑን የሀገሪቱ ሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተመልካች ሚንስትር ማርቲን ኒቫይባንዲ ገልጸዋል።

«አሁን የተመድ መርማሪ ኮሚሽን ያወጣውን ዘገባ የሚጻረር ጽሑፍ እናዘጋጃለን። ወንጀል የፈጸሙ ካለቅጣት እንዳይታለፉ መንግሥት ብዙ ጥረት ማድረጉን እናሳየለን። በህጉ መሰረት መቀጣት ይኖርባቸዋል።  ወደ ቡሩንዲ በመምጣት ምርመራ ማካሄድ ግን  የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል መዳኛ ፍርድ ቤት፣ አይሲሲ ተግባር አይደለም።  መፍትሔው የቡሩንዲን የፍትሕ አውታር መርዳት ብቻ ነው። »     

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic