ቡሩንዲ እና የምርጫ ውዝግብ | አፍሪቃ | DW | 06.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ቡሩንዲ እና የምርጫ ውዝግብ

የቡሩንዲ ፖሊስ ፕሬዝደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን ለመወዳደር ማቀዳቸዉን በመቃወም በመዲናይቱ ቡጁምቡራ የቀጠለውን የአደባባይ ሰልፍ በማስጠንቀቂያ ተኩስ እና በሚያስለቅስ ጢስ በተነ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:24

ቡሩንዲ እና የምርጫ ውዝግብ

የጥይት እሩምታም አልፎ አልፎ በሚሰማባት የመዲናይቱ ዋና ዋና መንገዶች በብዛት የተሠማራው ፖሊስ በመንግሥቱ ተቃዋሚዎች አንፃር ክትትሉን እና የኃይሉን ርምጃ አጠናክሮዋል። 40 ሰዎች የተገደሉበት ካለፈው ሚያዝያ ወዲህ በቀጠለው ተቃውሞ የተነሳ ወደ ትናንት እአአ ሰኔ አምስት፣ 2015 ዓም ተላልፈው የነበሩት ምክር ቤታዊ እና የከተሞች አስተዳደር ምርጫዎች አሁን እንደገና ወደሌላ ጊዜ ተላልፈዋል። ለፊታችን ሰኔ 26፣ 2015 ዓም ታቅዶ የነበረው ፕሬዚደንታዊ ምርጫም በአንድ ወር ሊገፋ እንደሚችል ነው የተሰማው። የቡሩንዲ አስመራጭ ኮሚሽን የምክር ቤታዊ እና የከተሞች አስተዳደር፣ እንዲሁም፣ የፕሬዚደንታዊው ምርጫዎችን ዕለት በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ አስታውቀዋል። ንኩሩንዚዛ እአአ ከ2005 ዓም ወዲህ ሀገሪቱን በመምራት ላይ ናቸው። በቡሩንዲ ህገ መንግሥት መሠረት ግን አንድ ፕሬዚደንት ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ ሀገሪቱን መምራት አይፈቀድለትም። የተቃዋሚ ቡድኖች ምርጫውን የማስተላለፉን ውሳኔ ማሞገሳቸውን የትልቁ የቡሩንዲ የተቃውሞ ፓርቲ «ብሔራዊ የነፃነት ኃይላት» ቃል አቀባይ ኤሜ ማጌራ ገልጸዋል።

« ምርጫው ወደሌላ ጊዜ መገፋቱ በመሠረቱ ጥሩ ዜና ነው፣ ይሁንና፣ ለችግሩ መፍትሔ እስካልተገኘ ድረስ የምርጫው መተላለፍ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም። ውሳኔው ለገዢው ፓርቲ CNDD-FDD ጊዜ ለመስጠት ካልሆነ በስተቀር እኛ ፕሬዚደንቱ ለ3ኛ ጊዜ በተወዳዳሪነት መቅረብ የለባቸውም በሚል ላቀረብነው ጥያቄ መልስ የማይሰጥ በመሆኑ ጥቅም የለውም። »

ይሁንና፣ ይህን መሰሉ የፖሊስ የኃይል ርምጃ በተስፋፋበት ሁኔታ ነፃ እና ትክክለኛ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል በማስታወቅ ፓርቲያቸው ከምርጫው እንደሚርቅ ኤሜ ማጌራ ዛቻ አሰምተው እንደነበር ይታወሳል።

« እኛ በመሠረቱ ከምርጫው መራቅ አንፈልግም። ይሁንና፣ ሂደቶች አሁን ባሉበት ሁኔታ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። የምርጫ ዘመቻ ማካሄድ እስካልቻልን፣ የማስፈራሪያ ዛቻ እስከቀረበብን፣ አባሎቻችን እስከተገደሉብን እና ፕሬዚደንቱ ለ3ኛ ጊዜ በተወዳዳሪነት የመቅረብ ዕቅዳቸውን እስካልሰረዙ ድረስ ምርጫው ትክክለኛ ይሆናል ብለን አናስብም፣ በመሆኑም፣ የተቃውሞው ወገን በዚህ ዓይነቱ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ አይደለም። »

በቡሩንዲ ቀውስ ላይ ባለፈው እሁድ ልዩ ስብሰባ ያካሄዱት የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት መሪዎች የቡሩንዲ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ቢያንስ እስከ ሀምሌ 2015 ዓም አጋማሽ እንዲራዘም ሀሳብ ካቀረቡ በኋላ ገዚው ፓርቲ እና አስመራጩ ኮሚሽን እአአ ለሰኔ 26፣ 2015 ዓም የታቀደውን ምርጫ ዕለት ለመቀየር ዝግጁነታቸውን አሳይተዋል፣ ይሁንና፣ እስካሁን በዚሁ አኳያ ዝርዝር መግለጫ አላወጡም። የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ ለቡሩንዲ ቀውስ መንሥዔ በሆነው ፣ ማለትም፣ ንኩሩንዚዛ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ሲሉ ለ3ኛ ጊዜ የመወዳደር አከራካሪ ዕቅድ ላይ አንዳችም አስተያየት ሳይሰጥ ያለፈበትን ሁኔታ የቡሩንዲ ተቃውሞ ቡድኖች፣ ዋነኛውን ጥያቄአቸውን ችላ ብሎ አልፎታል በማለት በጥብቅ ነቅፈዋል። የምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ አባል ሀገራት መሪዎች የምርጫዉ ጊዜ እንዲራዘም እንጂ ንኩሩንዚዛ ለ3ኛ ጊዜ እንዳይወዳደሩ አልጠየቁም፣ መጠየቅ ግን ነበረባቸው።

ካካባቢው ሀገራት ጎን፣ ዩኤስ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና የመብት ተሟጋቾች ምርጫው እንዲተላለፍ ጥሪ ቤልጅየም እና ስዊትዘርላንድ ለምርጫው ማካሄጃ ሊሰጡት የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ሰርዘዋል፣ የአውሮጳ ህብረትም ምርጫውን የሚታዘብ ቡድን ወደ ቡሩንዲ ላለመላክ ወስኗል።

በኤሜ ማጌሬ አንፃር በምህፃሩ «ኤፍ ኤን ኤል» በመባል የሚታወቀው የቀድሞ የሁቱ ሚሊሺያዎች ቡድን መሪ አጋቶን ርዋሳ ወደሌላ ጊዜ በተላለፉት ምክር ቤታዊ እና የከተሞች አስተዳደር ምርጫዎች መሳተፍን ይደግፋሉ፣ ሁኔታዎች ያን ያህል አመቺ ባይሆኑም። እንደ ርዋሳ አስተያየት፣ በቡሩንዲ መንግሥት ሕጋዊ እውቅና ያገኝ ዘንድ ምርጫ አስፈላጊ ነው፣ ግን፣ የቀውሱ ዋነኛ መንሥዔ እስካልተወገደ ደረስ ምርጫው በየጊዜው የሚገፋበት ሁኔታ ሀገሪቱን አደገኛ ቀውስ ውስጥ ይጥላታል።

የቡሩንዲ መንግሥት ሀገሪቱን ፀጥታ እና መረጋጋት ስጋት ውስጥ የሚጥለው የተቃዋሚ ቡድኖች የቀጠሉት ያደባባይ ሰልፍ ነው ባይ ነው። ተቃዋሚዎች በሀገሪቱ ለሁለተኛ ጊዜ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ናቸው በሚልም የፖሊስ ሥምሪትን ማጠናከሩን ነው መንግሥት ባለሥልጣናት ያስታወቁት፣ የትልቁ የቡሩንዲ የተቃውሞ ፓርቲ «ብሔራዊ የነፃነት ኃይላት» ቃል አቀባይ ኤሜ ማጌራ ግን መሠረተ ቢስ ሲሉ አጣጥለውታል።

« ይህ የፕሬዚደንቱን ለ3ኛ ጊዜ መወዳደርን የሚቃወሙትን ሁሉ ለማፈን መንግሥት ያስፋፋው ጭምጭምታ ነው ብዬ አስባለሁ። ለችግሩ መፍትሔ በመሻት ፈንታ የሰውን ነፃነት መግፈፍ ነው የተያዘው። እና ንኩሩንዚዛ ወደፊትም ሕዝባቸውን መጨቆን እና መግደል መቀጠል ይችሉ ዘንድ የሚጠቀሙበት ዘዴ አድርጌ ነው የምመለከተው። »

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic