ቡሩንዲ እና የምርጫ ውዝግብ | አፍሪቃ | DW | 25.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ቡሩንዲ እና የምርጫ ውዝግብ

የቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ የፊታችን ሰኔ 26፣ 2015 ዓም ለሚደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ ዕጩ ሆነው ለመቅረብ የያዙት ዕቅዳቸው በሀገሪቱ ትልቅ ተቃውሞ ገጠመው። በዚሁ በቀጠለው ተቃውሞ የፀጥታ ኃይላት በርካቶችን ካሰሩ በኋላ፣ በ65ቱ ላይ ኃይል የታከለበት ዓመፅ ቀስቅሳችኋል በሚል ክስ መሥርተውባቸዋል።

በቅርቡ አጠቃላይ ምርጫ የምታደርገው የማዕከላይ አፍሪቃዊቷ ሀገር ቡሩንዲ ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ ጊዜ ዕጩ ሆነው እንደሚቀርቡ ዛሬው ዕለት ይፋ እንደሚያደርጉ በምሕፃሩ «ሲ ኤን ዲ ዲ - ኤፍ ዲ ዲ » ተብሎ የሚታወቀው ገዚው የዴሞክራሲ ተከላካይ ምክር ቤት እና ግንባር ፓርቲያቸው አስታወቀ። በቡሩንዲ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የፊታችን ሰኔ 26፣ 2015 ዓም ይካሄዳል። የመንግሥቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ርምጃው የመፈንቅለ መንግሥት ያህል እንደሚቆጠር በማመልከት ተቃውሞአቸውን እንደሚቀጥሉ ዝተዋል።

ከ15 ዓመት በፊት የቡሩንዲ የርስበርስ ጦርነት ማብቃቱን ባረጋገጠው እና በአሩሻ፣ ታንዛኒያ በተፈረመው ውል እና ከ10 ዓመት በፊት በፀደቀው የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት፣ አንድ ሁለት የአምስት ዓመት የአገልግሎት ዘመኑን የፈፀመ ፕሬዚዳንት ለተጨማሪ ዘመራር ዘመን በሥልጣን ሊቆይ አይችልም።

"ይሁንና፣ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ለመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የተመረጡት በምክር ቤታዊ ምርጫ መሆኑን ያመለከቱት የፕሬዚደንቱ ደጋፊዎች በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረውን ፕሬዚደንቱ ሁለት ጊዜ በቀጥታ በሕዝብ መመረጥ ይችላሉ የሚለውን አንቀጽ በመጥቀስ የፕሬዚደንቱ ዕቅድ ትክክለኛነትን አስረድተዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የአብያተ ክርስትያን መሪዎች እና በሀገሪቱ የሚገኙ ዲፕሎማቶች፣ የፕሬዚደንቱ እቅድ ንዑሷን ሀገር እንደገና እከፋ ሁከት ውስጥ ሊጥላት ይችላል በሚል ስጋት፣ ንኩሩንዚዛ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠውን ሁለት የሥልጣን ዘመን ገደብን እንዲያከብሩ ጠይቀዋል። ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ ዕቅዱን በመቃወም አደባባይ በሚወጡ እና በፀጥታ አስከባሪዎች መካከል በተካሄደ ግጭት መንግሥት በርካቶችን ማሰሩን ቀጥሎዋል።

ይሁንና፣ ምንም እንኳን የእስራቱ ርምጃ ቢጠናከርም፣ ግፊታቸውን እንደሚያጠናክሩ ነው በንኩሩንዚዛ ዕቅድ አንፃር ስድስት ፓርቲዎች ያቋቋሙት ኮሚቴ ቃል አቀባይ አንፃር ሾቪኖ ሙርዌንጌዞ ያስታወቁት። ይህ የመንግሥቱ ርምጃ አስሮዋል።

« 500፣ 1,000 ወይም 5,000 ሰዎች የሚያስሩበት ርምጃቸው ያን ያህል አያስጨንቀንም። ይህ ትግላችንን ከመቀጠል አያከላክለንም። »

ቁርጠኝነታቸውን ያረጋገጡት ሾቪኖ ተቃውሞአቸውን የሚያበቁት ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ የመወዳደር ዕቅዳቸውን ሲሰርዙ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

« የጀመርነውን ትግል በፍፁም አናቋርጥም። ፕሬዚደንቱ የማይወዳደሩበትን ውጤት እስኪያስገኝልን ድረስ እንቀጥላለን። ምክንያቱም፣ እንደሚመስለኝ፣ የቡሩንዲ ፕሬዚደንት በሀገሪቱ ዓቢይ ሁከት ሊቀሰቅስ እና የዘር ማጥፋት ፖለቲካ ወንጀል ሊያስከትል የሚችል ሁኔታ ውስጥ ሊያስገቡን ነው የሚፈልጉት። »

የቡሩንዲ ፓርቲዎች ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ ዕጩዎቻቸውን እንዲያስመዘግቡ አአአ ከፊታችን ሚያዝያ 30፣ 2015 ዓም ጀምረው የአንድ ሳምንት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል። የፕሬዚደንቱ በዕጩነት መቅረብ አለመቅረቡ በግልጽ እስካልታወቀ ድረስ ተቃውሞው ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በነገራችን ላይ ዕቅዱ በራሳቸው በፕሬዚደንቱ ፓርቲ ውስጥ ሳይቀር ክፍፍል መፍጠሩ አልቀረም።

የፕሬዚደንቱን ዕቅድ በመቃወማቸው ከገዢው ፓርቲ ቃል አቀባይነት ሥልጣናቸው የተባረሩት እና የተቃዋሚዎችን ኮሚቴ የተቀላቀሉት ኦኔሲማ ንዱዊማና አንዳንድ የጦር ኃይል አባላት የሚሊሺያ ቡድን ያቋቋሙበትን ድርጊት በጥብቅ ኮንነዋል።

« አንዳንድ ከፍተኛ የጦሩ እና የፖሊስ አባላት የተቆጣጠሩዋቸውን ሚሊሺያዎች የጦር መሳሪያ ማስታጠቅ የተያዘበትን ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን። የፕሬዚደንቱን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ ሲባል የሚፈፀመውን ሽብርተኝነት፣ በተቃዋሚዎች፣ የመብት ተሟጋቾች እና ጋዜጠኞች ላይ የሚደረገውን የግድያ ዛቻ፣ የዘፈቀደ እስራት እና ክትትልንም እናወግዛለን። »

በቡሩንዲ የስድስቱ ፓርቲዎች ኮሚቴ የቀጠለው ተቃውሞ ዓመፅ ለማነሳሳት የታለመ ንቅናቄ በመሆኑ እንደሚያስቀጣ የቡሩንዲ ፕሬዚደንታዊ ጽሕፈት ቤት የኮምዩኒኬሽን ክፍል ከፍተኛ ባለሥልጣን ዊዲንያሚት ኩዌይኮ አስታውቀዋል።

« ስለዚህ ንቅናቄው በሕጋዊ መንገድ ሊመታ ይገባል። በዚሁ ረገድ የቡሩንዲ ሕግ ግልጽ ነው። ዜጎች ሕገ ወጥ ተግባር ከፈፀሙ ፣ የፍትሑ አውታር በነዚሁ ዜጎች አንፃር ክትትልየሚያደርግበት አሰራር የተለመደ ነው። »

በወቅቱ በተካረረው ውጥረት የተነሳ 8,000 ሰው ሀገሩን ለቆ መሰደዱን የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት፣ « ዩኤንኤችሲአር » አስታውቋል። እንደ « ዩኤንኤችሲአር » መግለጫ ብዙዎቹ ወደ ጎረቤት ርዋንዳ፣ ጥቂቶች ደግሞ ወደ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ነው የሸሹት። ወደ ርዋንዳ ከተሰደዱት መካከል አንዷ ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት፣ ለስደት የዳረጉዋቸው በሀገሬው አጠራር «ኢምቦኔራኩሬ» የተባሉት የገዢው «ሲ ኤን ዲ ዲ - ኤፍ ዲ ዲ » የወጣት ክንፍ ቡድን ነው። ወጣቶቹ የ«ሲ ኤን ዲ ዲ - ኤፍ ዲ ዲ » አባል ባልሆኑት ወይም የፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛን ዕጩነት ይቃወማሉ ብለው በጠረጠሩዋቸው ላይ የኃይል ተግባ ር እንደሚፈፅሙ ነው ስደተኛዋ የገለጹት።

« የሸሸሁት የወጣት ወንጀለኛ ቡድኖች አባላት ስላዋከቡን ነው። ያሉት ወጣት መንግሥቱ እየለቀቀ በመውጣት ላይ ነው። ጉድጓዶች እየቆፈሩ ሰዉን እዚያ ውስጥ ለስገባት ማሰባቸውን አንድ ውስጥ አዋቂ በነገረን ጊዜ ነበር ሸሽተን ወደዚህ የመጣነው።»

ንኩሩንዚዛ በዕጩነት የሚቀርቡበት ሁኔታ በቡሩንዲ የቀጠለውን ጭቆና እና በሰበቡ የሚታየውን ውጥረት ወደለየለት ግጭት ሊቀይረው እንደሚችል ከጥቂት ጊዜ በፊት ቡሩንዲን የጎበኙት የተመድ የሰብዓዊ መብት ተጠሪ ዛይድ ራድ አል ሁሴን በስጋት ገልጸዋል።

« ሰዎች ምን እሆናለሁ ብለው ሳይፈሩ መወያየት እና ሀሳባቸውን በነፃ መግለጽ ከቻሉ ለነዚህ ውዝግቦች መፍትሔ ሊገኝላቸው እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ። ይሁንና፣ በሀገር ውስጥ የሚታየው የማዋከብ ፣ የማስፈራራት እና የግፊት ርምጃ እየከፋ የሄደበትን ሁኔታ ለማብረድ ነው መሞከር ያለብን። »

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic