ቡሩንዲ፤ ተቃዋሚዎችና የብሔራዊ አንድነቱ መንግሥት | አፍሪቃ | DW | 01.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ቡሩንዲ፤ ተቃዋሚዎችና የብሔራዊ አንድነቱ መንግሥት

በቡሩንዲ ምክር ቤታዊ እና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተሸነፉት የሃገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አጋቶን ርዋሳ ፕሩዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ በሚመሩት መንግሥት ውስጥ ለመሳተፍ ወሰኑ፣ ርዋሳ እና የቡሩንዲ መንግሥት አብረው ለመስራት የደረሱት ስምምነት፣ ብዙዎች ተስፋ እንዳደረጉት፣ ቡሩንዲን ከምትገኝበት ደም ያፋሰሰ ቀውስ ያላቅቃት ይሆን? የብዙዎች ጥያቄ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:34
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:34 ደቂቃ

ትኩረት በአፍሪቃ

ከምክር ቤታዊ እና ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በኋላ አሁን ቡሩንዲ ውስጥ አዳጋቹ የፖለቲካ ሂደት ተጀምሮዋል። በአወዛጋቢው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ድጋሚ መንበረ ሥልጣኑን በያዙት ፒየር ንኩሩንዚዛ አመራር የወደፊቱ የቡሩንዲ ዕጣ ፈንታ የተረጋጋ እንዲሆን ብዙዎች ተስፋ ቢያደርጉም፣ ተንታኞች ተጠራጥረውታል።

የፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ የ«ሲ ኤን ዲ ዲ - ኤፍ ዲ ዲ» ፓርቲ በምክር ቤታዊው ምርጫ ከ122 መንበሮች 86 አግንቶዋል። ይሁንና፣ ምንም እንኳን የብዙኃኑን ድምፅ ቢያገኝም፣ ሃገሪቱን ለብቻው ሊመራ አይችልም። የ300,000 ሰዎች ሕይወት ያጠፋውን የቡሩንዲን የርስበርስ ጦርነት ያበቃው እአአ በ2005 ዓም በአሩሻ ታንዛንያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ የቡሩንዲ ፕሬዚደንት እና ምክትል ፕሬዚደንት የተለያዩ ፓርቲዎች አባላት መሆን አለባቸው።

ይህ የቡሩንዲ ተቃውሞ ፓርቲዎች ላልደገፉት የሃገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ትልቅ ፈታኝ ሁኔታ ፈጥሮዋል። እንደሚታወቀው፣ ተቃዋሚዎች ንኩሩንዚዛ የሃገሪቱን ሕገ መንግሥት በመጣስ ለሶስተኛ ሥልጣነ ዘመን እንደሚወዳደሩ ያስታወቁበትን ድርጊት በመቃወም ከምክር ቤታዊው እና ከፕሬዚደንታዊው ምርጫዎች ርቀዋል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ያካባቢ ታዛቢዎች ፕሬዚደንታዊውን ምርጫ ዓለም አቀፍ መለኪያዎችን ያላሟላ ነፃ እና ትክክለኛ ያልነበረ በሚል ወቀሳ ሰንዝረዋል። አጋቶን ርዋሳ እና ሻርል ንዲትየ የመሩት አሚዜሮ ዪ አባሩንዲ የተባለውን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ህብረት አባላት መንግሥት በምርጫ ዘመቻ ወቅት ዕጩዎቻቸውን ለማስፈራራት የኃይል ተግባር ተጠቅሞዋል፣ ሀሳብን በነፃ መግለጽ እንዳይቻልም የግል መገናኛ ብዙኃንን የዘጋበትን ርምጃ በመቃወም ከአጠቃላዩ ምርጫ ርቀዋል። ይሁንና፣ የአሚዜሮ ዪ አባሩንዲ ህብረት ዕጩዎች በምክር ቤታዊው ምርጫ ሳይሳተፉ ቢቀሩም፣ በምክር ቤቱ ውስጥ 21 መንበሮችን አግኝተዋል። በተመሳሳይ ሁኔታም በምህፃሩ «ኤፍ ኤን ኤል» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የተቃዋሚው የነፃነት ብሔራዊ ኃይላት ፓርቲ መሪ አጋቶን ርዋሳ በፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላለመሳተፍ ከምርጫው ጥቂት ቀደም ሲል ቢወስኑም፣ ርዋሳ 18,9 ከመቶ የመራጩን ድምፅ አግኝተዋል። ለዚህም የቡሩንዲ አስመራጭ ኮሚሽን የሰጠው ምክንያት የተቃዋሚ ዕጩዎችን ስም ከምርጫው እንዲሰርዝ ከተቃዋሚዎች ዘንድ ይፋ ማመልከቻ ባለመቅረቡ፣ ለህትመት የተሰጡትን የምርጫ ወረቀቶች ማስቆም አልተቻለም ነው።

አዲሱ የቡሩንዲ ምክር ቤት ባለፈው ማክሰኞ የመጀመሪያውን ጉባዔውን በከፈተበት ወቅት አጋቶን ርዋሳ እና 20 የ«ኤፍ ኤን ኤል» ፓርቲያቸው አባላት ተገኝተው ነበር፣ ከሁለት ቀናት በኋላም ምክር ቤቱ ርዋሳን ምክትል አፈ ጉባዔ አድርጎ መርጦዋል።

« ሥልጣኑን የተቀበልነው የቡሩንዲ ሕዝብ ለውጥ በመፈለጉ ነው። እና ሕዝቡ ያሳየውን ፍላጎት ልናከብር እና ተግባራዊ ልናደርግ ይገባል ባይ ነኝ። የሕዝብን ስሜት የማያዳምጥ መንግሥት ስኬታማ ሊሆን አይችልም። ትልቁ ስራ የቡሩንዲ ሕዝብ ሊደርስበት የሚፈልገውን ለይቶ ማወቅ ነው። »።

በዚህም አጋቶን ርዋሳ ከንኩሩንዚዛ የ«ሲ ኤን ዲ ዲ - ኤፍ ዲ ዲ» ፓርቲ ጋር የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመሥረት ባለፈው ሳምንት ያቀረቡትን እና ከመንግሥቱ በኩል ተቀባይነት ያገኘውን ሀሳባቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አሳይቶዋል።

« የምርጫው ውጤት መንግሥት ለራሱ እንደሚመቸው አድርጎ ያወጣው ቢሆንም፣ ይህ መብታችንን እና የመንቀሳቀስ ነፃነታችንን በማስከበሩ ጥረታችን ላይ፣ ማለትም እንደ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ልንጫወተው የሚገባንን እና በሃገራችን ታሪክ ውስጥ ካሁን ቀደም የታየውን ሚናችንን ማገድ አይኖርበትም። »

ይኸው የአጋቶን ርዋሳ አቋም ከሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ ትችት ገጥሞታል። በምህፃሩ «ዩፕሮና» የሚባለው የብሔራዊ መሻሻል ህብረት ፓርቲ መሪ እና ዋነኛው የርዋሳ ተጓዳኝ የ ሻርል ንዲትዬ ቃል አቀባይ እንዳስታወቁት፣ ርዋሳ በዚሁ ርምጃቸው የፓርቲያቸውን ፖለቲካዊ ውድቀት አረጋግጠዋል። ይህ

አሚዜሮ ዪ አባሩንዲ በተባለው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ህብረት ውስጥ በተጠቃለሉት የቡሩንዲ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚታየው ክፍፍል በሀምበርግ ከተማ የሚገኘው በምህፃሩ «ጊጋ» የተባለው የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም የቡሩንዲ ተመራማሪ ዩሊያ ግራውፎግልን እምብዛም አላስገረመም። ምክንያቱም፣ ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ ዘመነ ሥልጣን እንዳይወዳደሩ የማከላከሉ ጥረታቸው ነበርና ፓርቲዎችን ያስማማ ብቸኛው ጉዳይ። ርዋሳ ከመንግሥት ጋር ባንድነት ለመስራት መስማማታቸው ከዉስጥ ሆነው በፖለቲካውን ሂደት ላይ መወሰን እንዲችሉ መሆኑን ነው ያመለከቱት። ዩሊያ ግራውፎግልም ከዚሁ ጋር የሚቀራረብ አስተያየት ነው የሰጡት።

« ተቃዋሚው ወገን አሁን በመንግሥት ምሥረታው ሂደት ውስጥ በተካተተበት ድርጊት ምናልባት እአአ ከ2010 ዓም ምርጫ ትምህርት ቀስሞ ሊሆን ይችላል። ተቃዋሚዎች ያኔ ታዛቢዎች ነፃ እና ትክክለኛ ነበር ካሉትምርጫው ርቀው ነበር። በዚሁ ርምጃቸው የተነሳም ለቀጠሉት አምስት ዓመታት ከሃገሪቱ ፖለቲካዊ ሂደት ራሳቸውን ኣeንዲገለሉ አድርገዋል። »

በሚቀጥለው አንድ ዓመት ውስጥ በቡሩንዲ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚካሄድበትን እና አምስት ዓመት የሚዘልቀውን የሀገሪቱን ፕሬዚደንት የሥልጣን ዘመን የሚያጥርበትን ሀሳብ ርዋሳ ለብሔራዊ አንድነቱ መንግሥት ምሥረታ እንደ ቅድመ ግዴታ አቅርበዋል። ይሁንና፣ ንኩሩንዚዛ ባለፉት ዓመታት ለቡሩንዲ መረጋጋት ትልቅ ድርሻ ማበርከታቸውን በማስታወቅ ሀሳቡን ውድቅ አድርገውታል። ይሁንና፣ የፕሬዚደንቱ ገፅታ ካለፉት ወራት ቀውስ ወዲህ መበላሸቱን ነው ዩሊያ ግራውፎግል ያስታወቁት።።

« ንኩሩንዚዛ ባለፉት 10 ዓመታት በሃገሪቱ ሰላም እና መረጋጋትን ያረጋገጡ ፕሬዚደንት አድርገው ለማቅረብ ነው የሚሞክሩት። እርግጥ፣ አሁንም ባንዳንድ የገጠሩ አካባቢ ሰፊ ድጋፍ አላቸው። ይሁንና፣ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚቆይና በሳቸው መሪነት የሚተዳደር የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ቡሩንዲ አያረጋጋም። ዕጩነታቸውን በመቃወም ባለፉት ወራት የተካሄደው ግዙፍ ተቃውሞ በተለይ ባንዳንድ አካባቢዎች በቀላሉ የማይጠፋ ዘላቂ ውጥረት ፈጥሮዋል። »

ይህ በዚህ እንዳለ፣ በውጭ ሃገራት የሚገኙ ብዙ የቡሩንዲ ተቃዋሚ ቡድኖች» አጋቶን ርዋሳን እና የ«ኤፍ ኤል ኤን» ፓርቲያቸውን በማግለል፣ ለስብሰባ በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ተሰምቶዋል። በስብሰባው ከሚካፈሉት መካከል አንዱ የሆነው ያርበኞች ምክክር ፓርቲ ፓሬዚደንት አኒሴ ኒዮንኩሩ ቡድኖቹ ንኩሩንዚዛ ጋር መደራደር እንደማይፈልጉ በማስታወቅ፣ በሥልጣን የሚቆዩበት ድርጊት ቡሩንዲን እንደገና ወደርስበርስ ጦርነቱ ሊያመራት ይችላል በሚል መስጋታቸውን ገልጸዋል።

« የኃይል ርምጃ በሚወስደው የንኩሩንዚዛ አገዛዝ አንፃር ለመታገል የጦር መሳሪያ ለማንሳት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ይህ አይሆንም ብዬ ለመናገር አልችልም። ባለፈው ሳምንት እንኳን በደቡቡ ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ በሰሜኑ የሃገሪቱ ከፊል ውጊያ ተካሂዶዋል። ሰዎች በተለያዩ ቦታዎች ራሳቸውን በጦር ቡድን እያደራጁ ነው። እስካሁን ብዙ ደም ፈሶዋል። ወደፊት የቡሩንዲ ዜጎች ደም እንዲፈስ አንፈልግም። በሃገራችን ላይ ይህ መድረሱ አሳዛኝ ነው። »

ፊሊፕ ዛንድነር/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ

 

Audios and videos on the topic