1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

የዩኒቨርስቲው ተቋማት የሳይንስ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ናቸው

ረቡዕ፣ ሐምሌ 12 2009

የአፍሪካ ህብረት የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲን ለማቋቋም በጎርጎሮሳዊው 2008 ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ እቅዱ በአምስቱ የአፍሪካ ቀጠናዎች የተከፋፈሉ ተቋማትን ማቋቋም ነው፡፡ የሳይንስ ዘርፎች ላይ ያተኮሩት እኒህ ተቋማት ተማሪዎችን ተቀብለው ከማስተማር አልፈው ማስመረቅ ሁሉ ጀምረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2gpIf
Afrikanische Union Gebäude Außenansicht Äthiopien Addis Ababa
ምስል Imago

በፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ ሆነዋል

በርካታ ታዛቢዎች መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገውን የአፍረካ ህብረት ኮሚሽንን “ጥርስ እንደሌለው አንበሳ” ይመለከቱታል፡፡ በዓመት ሁለቴ በሚያካሄዳቸው መደበኛ ጉባኤዎቹም ሆነ በየጊዜው በሚጠራቸው አስቸኳይ ስብሰባዎች የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች እንኳ“ በቅጡ መተግበር አይችልም” ሲሉ ይወርፉታል፡፡ አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ቻዳዊው ሙሳ ፋኪ ማህማት ይህ ትችት ዘልቆ የተሰማቸው ይመስላሉ፡፡ ጉዳዩን በሰኔ ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ በተካሄደው የህብረቱ ጉባኤ ላይ አንስተውት ነበር፡፡ 

“በውሳኔዎቻችን እና በአፈጻጸማቸው ላይ ስላለው ከባድ ተቃርኖ አስመልክቶ ስናገር ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ አይደለም፡፡ ልዩነቱ ምንድነው አሁን የክስተቱን ልክ እና የተቃርኖውን መገለጫዎች በየዕለቱ ስጋፈጥ ራሴን ማግኘቴ ነው፡፡ አውቃለሁ ችግሩ ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን በድርጅታችን የሞራል ጤንነት እና ተዓማኒነት ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ችላ እያልን ልንቀጥል አይገባም፡፡ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ ወይ የወስናቸውን ውሳኔዎች ተቀብለን እንተግብራቸዋለን አሊያም ለመተግበር ዝግጁ እስክንሆን ድረስ ውሳኔዎችን ከመቀበል እንቆጠባለን” ብለዋል በስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ፡፡ 

Äthiopien Treffen Afrikanische Union - Tschad Außenminister Moussa Faki
ምስል picture-alliance/Anadolu Agency/M. Wondimu Hailu

ማህማት የሚመሩት ተቋም ላይ ቢያመሩም ህብረቱ ዓመታትን ወስዶም ቢሆን አንዳንዶቹን ውጥኖቹን ማሳካቱ አልቀረም፡፡ ከእነዚህ ስኬቶቹ መካከል የሚጠቀሰው የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ምስረታ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲው እንዲቋቋም የተወሰነው የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ በተካሄደው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነው፡፡ ያኔ የጉባኤው ዋና አርእስት ትምህርት ነበርና አፍሪካ በአህጉር ደረጃ የራሷ የሆነ ዩኒቨርስቲ እንደሚያስፈልጋት ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ አምስቱ የአፍሪካ ቀጠናዎችም የእዚህ ዩኒቨርስቲ አካል የሆኑ ተቋማት እንዲኖራቸው ውሳኔ ተላለፈ፡፡

የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ በቶሎ ወደ ስራ እንዲገባም አዲስ ተቋማትን ከመገንባት ይልቅ በየቀጠናው ካሉ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር መስራት እንደሚሻል ታመነበት፡፡ ይህን ተመርኩዞም ተቋማቱ በሀገራቸው አንዲመሰረት ፍቃደኝነታቸውን ካሳዩ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈጸመ፡፡ በዚህም መሰረት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ተቋም በምስራቅ አፍሪካዊቷ ኬንያ እንዲሆን ተደረገ፡፡ የተቋሙ አስተናጋጅ በመዲናይቱ ናይሮቢ አቅራቢያ የሚገኘው የጆሞ ኬንያታ የእርሻ እና ቴክኖሎጂ የመንግስት ዩኒቨርስቲ ሆነ፡፡ 

የምዕራብ አፍሪካ ቀጠናን ድርሻ ደግሞ ናይጄሪያ ወሰደች፡፡ በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ በምትገኘው ኢባዳን ከተማ ያለው የሀገሪቱ የመጀመሪያ ዩኒቨርስቲ የህይወት እና የመሬት ሳይንስ ተቋምን የማስተናገድ ኃላፊነት ተረከበ፡፡ ካሜሮን የማዕከላዊ አፍሪካ ቀጠናን ወክላ የአስተዳደር፣ ሂዩማኒቲ እና የማህበራዊ ሳይንስ ተቋምን ወደ ሀገሯ አመጣች፡፡ በመዲናዋ ያውንዴ የሚገኘውን እና በከተማይቱ ስም የተሰየመውን የሀገሪቱን ዩኒቨርስቲ የተቋሙ መናኸሪያ አደረገች፡፡ የሰሜን አፍሪካ ቀጠና ተወካይዋ አልጄሪያ ትሌምሰን በተሰኘው ከተማዋ ያለውን ዩኒቨርስቲ ለውኃ እና የኢነርጂ ሳይንስ ተቋም መደበች፡፡ በደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ይመሰረታል የተባለው የህዋ ሳይንስ ተቋም ግን ገና በሂደት ላይ ነው፡፡

እነዚህ ተቋማት በተለያየ የትምህርት ዘርፍ ላይ እንዲያተኩሩ ቢደረግም በሁሉም ግን ትምህርቱ የሚሰጠው በሁለተኛ ዲግሪ እና ከዚያ በላይ ነው፡፡ ይህም ቢሆን የፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ከተቋቋመበት ዓላማ ይመዘዛል፡፡ ወ/ሮ ዕልልታ አስመላሽ በፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ረዳት ናቸው፡፡ የትምህርት ዘርፎቹ የተመረጡበት መነሾ በማስረዳት በማድረግ ይጀምራሉ፡፡ 

African Union Hauptquartier in Addis Abeba
ምስል AFP/Getty Images/J. Vaughan

“አፍሪካ የሚያስፈልጋት ምንድነው? በሚለው እና የራሳችንን ተማሪዎች ራሳችን ልናስተምራቸው ይገባል በሚለው ነው፡፡ ጎበዝ ልጆች አሉ፡፡ ማስተርስ እና PHD ብዙውን ጊዜ ከአፍሪካ ውጭ ነው የሚሰራው ነገር ግን እዚሁ ሆኖ መሰራት ይችላል፡፡ የተማረ ወጣት ኃይል ማብዛት ነው ዋናው ዓላማው” ይላሉ ወ/ሮ ዕልልታ፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን የሆኑ አፍሪካውያን ላይ ከሚቀርበው ትችት አንዱ የማስተርስ እና ዶክትሬት ትምህርታቸውን ለመከታታል በሄዱበት ሀገር በዚያው የመቅረት ዝንባሌያቸው ነው፡፡ የሚፈለገውን ትምህርት በአህጉሪቱ ተቋማት መስጠት ከተቻለ የተማረ ሰው ኃይል ኩብለላን ማስቀረት ይቻላል የሚል እምነት በፓን አፍሪካ ዩኒቨርስቲ አቀንቃኞች ዘንድ አለ፡፡ ሃያ እና ሰለሳ ዓመታት በውጭ ሀገራት ቆይተው ከሚመለሱ የአህጉሪቱ የተማሩ ሰዎች ይልቅ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ተምረው ወደየሀገራቸው የሚመለሱ ትኩስ ኃይሎች በፖሊሲ መቅረጹም ሆነ ተቋማትን በመምራት ውጤት እንዲያመጡ ይሻሉ፡፡

ይህን ዓላማ አንግበው ተማሪዎችን መመልመል የጀመሩት በየቀጠናው ያሉ ተቋማት በራቸውን ክፍት ያደረጉት ከአራት ዓመት በፊት ነው፡፡ የመወዳደሪያ መስፈርቶችን አሟልተው ተቋማቱን ከተቀላቀሉት ተማሪዎች መካከል ኢትዮጵያውያንም አሉበት፡፡ ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥ በአልጄሪያው ትሌምሰን ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ሶስት ኢትዮጵያውያን ባለፈው ሳምንት የዶይቸ ቬሌ ራዲዮ ጣቢያ ወደሚገኘበት የጀርመኑ ቦን ከተማ መጥተው ነበር፡፡ 

ረሂማ ከድር አንዷ ነች፡፡ በትሌምሰን ዩኒቨርስቲ የውኃ እና የኢነርጂ ሳይንስ ተቋም ውስጥ በውኃ ፖሊሲ ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመያዝ እያጠናች ትገኛለች፡፡ አብረዋት ከ22 የአፍሪካ ሀገሮች የመጡ ተማሪዎች አሉ፡፡ በተቋሙ በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች የማይሰጡ የትምህርት ዓይነቶችን እየተማሩ እንደሚገኙ ታስረዳለች፡፡

“እንደሚታወቀው እኛ የውኃ ዩኒቨርስቲ አለን፡፡ እኔም የመጀመሪያን ዲግሪዬን ከሃሮማያ ዩኒቨርስቲ የጨረስኩት በውኃ ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ በዚህ ዩኒቨርስቲ በውኃ ዘርፍ በመማራችሁ ምን አዲስ ነገር ታገኛላችሁ? ለሚለው ኢትዮጵያ እያለህ ስታማር እይታህ የተገደበ ነው፡፡ [ትኩረቱ] ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ችግሮች ላይ ነው፡፡ እዚህ ስትመጣ ከተለያዩ ሀገሮች የመጡ ሃሳቦች ይጋራሉ፡፡ እኛ ያላየነውን አቅጣጫ ከሌሎች ተማሪዎች ልምድ [እንመለከታለን]፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የምንወስደው ነገር አለ፡፡ ያን ነገር በትክከል ስራ ላይ፣ ተግባር ላይ ማዋል ከቻልን እዚህ ያለውን ልምድ ሀገራችን ሄደን የማናጋራበት ምክንያት የለም፡፡”

“ሁለተኛ እኔ የውኃ ተማሪ ብሆንም የኢነርጂ ተማሪዎች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያም ኢነርጂ ኢንጂነሪንግ፣ ኢነርጂ ፖሊሲ የሚማሩ አሉ፡፡ ይሄ ዘርፍ እንደ ኢትዮጵያ ገና አዲስ ነው ወይም የለም ማለት ይቻላል፡፡ ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያ ስንል ኢነርጂ ላይ ብዙ መሰራት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ይሄኛውን ልምዳችንን ማጋራታችን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገራችን ማምጣት የሚያስችሉ ባለሙያዎችን ማፍራት እንችላለን፡፡ ይህን እንደትልቅ ጥቅም ማየት እንችላለን” ስትል በተቋሙ ያገኘችውን ጠቀሜታ ትዝረዝራለች፡፡  

Flaggen African Union AU
ምስል picture alliance/landov

ዳዊት ዘሩ ረሂማን ጨምሮ ከዘጠኝ ኢትዮጵያውያን ጋር በትሌምሰን ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን የሚከታተል ወጣት ነው፡፡ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በባዮ ኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተመርቆ በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ለሁለት ዓመት ያህል አስተምሯል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች የማይሰጠውን ኢንርጂ ኢንጂነሪንግ እየተማረ ይገኛል፡፡ በዩኒቨርስቲ ቆይታው በኃይል አቅርቦት በኩል በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ይበልጥ የመርመር ዕድል አግኝቷል፡፡

“በኢነርጂ በኩል አሁን በኢትዮጵያ ባለው የዕድገት ሁኔታ ዕድገቱ በጣም በፍጥነት ሲሄድ የኃይል ፍላጎት በ30 በመቶ እየጨመረ ነው፡፡ የኃይል ፍላጎት ከምናመርተው መጠን [ጋር ሲነጻጸር] በጣም ክፍተት አለው፡፡ እዚህ መጥቼም ሆነ እዚያም ሆኜ ከማየው ኃይልን ማስተዳደር እና በአግባቡ መጠቀም ላይ ችግር አለብን፡፡ ኢነርጂን በአግባቡ ነው የምንጠቀመው ወይ? ለምሳሌ ራቅ ላሉ ቦታዎች ከዋና መስመር ጋር የተያያዘ የኃይል አቅርቦት ከምንሰጣቸው ይልቅ ከመስመር ውጪ ያለ የኃይል ምንጭ እዚያው ብንጠቀም ይሻላል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ በጣም ጥሩ የሆነ የነፋስ፣ የጸሀይ ኃይል አቅም አለ፡፡ ስለዚህ እነርሱ ላይ ገንዘብ ብናፈስ ይሄ የምንጠቀመውን ከዋናው መስመር ጋር የተያያዘ ኃይል ውጤታማ በሆነ መልኩ ለኢንዱስትሪዎች እና ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማዋል ይቻላል፡፡ ለሌሎቹ ቦታዎች ደግሞ ከመስመር ውጭ የሆነ ኃይል ብንሰጣቸው የሚሉ ሀሳቦች አሉ፡፡ በእነዚህ ላይ እንግዲህ የተለያዩ ልምዶች ካገኘን በኋላ እዚያ ሄደን የምንሰራው ነገር ይታየኛል” ሲል ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በኢትዮጵያ ሊያደርግ የሚያስበውን ይናገራል፡፡

በሚቀጥለው ዓመት የሚመረቁት ረሂማ እና ዳዊት የቀሰሟቸውን ልምዶች እና ዕውቀቶች ወደ ተግባር ይለውጡ እንደው የሚታይ ነው፡፡ ተቋማቸው የመጀመሪያ ተማሪዎቹን ባለፈው ዓመት ሲያስመርቅ አንድ ኢትዮጵያዊ በውኃ ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪውን ጭኗል፡፡ ስድስት ኢትዮጵያውያን በዚህ ዓመት ይከተላሉ፡፡ ትልቁ ጥያቄ እኒህ ምሩቃን በሀገራቸው ተገቢውን ቦታ ያገኙ ይሆን ወይ የሚለው ይሆናል?

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ