በፊዚክስ፣ የዘንድሮዎቹ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 07.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በፊዚክስ፣ የዘንድሮዎቹ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች፣

በሳይንሳዊው ምርምር ፣ « የብርሃን ጌቶች » የሚል ተቀጥላ ሥም ያገኙ 3 አዛውንት ፣ በፊዚክስ ፣ የዘንድሮውየኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች መሆናቸውን ትናንት የአስዊድን አካዳሚ የኖብል ኮሚቴ አስታውቋል።

default

በፊዚክስ፣ የዘንድሮ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች፣ ቻርለስ ኬ. ካዖ፣ ዊላርድ ኤስ. ቦይልና ጆርጅ ኢ. ስሚትዝ

ለሽልማት የበቁት፣ የ 76 ዓመቱ ቻርለስ ኩን ካዖ፣ የ 85 ዓመቱ ዊላርድ እስተርሊንግ ቦይል፣ እንዲሁም የ 79 ኙ ጆርጅ ኤልውድ እስሚትዝ፣ ናቸው። 3 ቱ አዛውንት ሳይንቲስቶች፣ የሽልማት አሸናፊዎች መሆናቸው መታወጁ ፣ ለጡረታ መደጎሚያ ታስቦላቸው ወይስ በምርምር ላስመዘገቡት አመርቂ ውጤት የሚገባቸው የክብር ዋጋ ሆኖ ተገኝቶ ነው ? የዛሬው ቅንብራችን ዐቢይ ትኩረት በሳይንቲስቶቹ የምርምር ክንውን ላይ ይሆናል።

በቅድሚያ ግን ከሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሁለት ጉዳዮች፣ በአጭሩ እንዳስሳለን።

የአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽናንና MP3፣

በተንቀሳቃሽ የሙዚቃ ማጫወቻ መሣሪያ፣ ሙዚቃን፣ ጆሮ ላይ በሚሰካ ማዳመጫ አማካኝነት፣ ከመጠን ባለፈ ሁኔታ ጮክ አድርጎ ማዳመጥ ጆሮን ለአደጋ ማጋለጥ መሆኑን የአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽን አስጠነቀቀ። ኮሚሽኑ፣ በአመዛኙ ወጣቶች ጆሮአቸው ላይ እየሰኩ የሚያዳምጡበት የሙዚቃ ማጫወቻ መሣሪያ(MP3) ፣ ከፍተኛ የድምፅ ደረጃው ዝቅ ብሎ አንድ ወጥ በሆነ መልኩ ፣ በሠሪዎቹ ፋብሪካዎች ይዘጋጅ ዘንድ አንድ ህግ እንደሚያረቅም ኮሚሽኑ አስታውቋል። በ MP3 ከፍ አድርጎ ሙዚቃ ማጫዎት ፣ ውሎ-አድሮ፣ ተጠቃሚዎቹን ጽሙማን (መስማት የተሳናቸው )እንዳያደርጋቸው ነው የሚያሠጋው።

በመሆኑም የአውሮፓው ኅብረት የኢንዱስትሪ ውጤት ተጠቃሚዎች ጉዳይ ኀላፊ ወ/ሮ ሜግሌና ኩኔቫ፣ እንዳስታወቁት፣ MP3 የሚያወጣው የሙዚቃ ድምፅ ደረጃ፣ ልዕለ-ድምፅ (Decibel) ከ 100 ወደ 80 ዝቅ እንዲል ነው የሚፈለገው። 2 ዓመታት ከሳይንቲስቶች፣ ከባለኢንዱስትሪዎችና ከተጠቃሚዎች ተወካዮች ጋር ሲመክር የቆየው የአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽን፣ MP3 አምራቾች ወደፊት አዲስ መመሪያ በመቀበል እንዲሠሩና ፣ ይህም በ 27 ቱ የአውሮፓው ኅብረት አባል ሀገራት በመላ ተግባራዊ እንዲሆን ይፈልጋል። ባለፈው ዓመት በጥር ወር ፣ አንድ የአውሮፓው ኅብረት የሳይንስ ቡድን፣ 10 ሚሊዮን ያህል አውሮፓውያን ወጣቶች በ MP3 መጠን ባለፈ ከፍታ፣ ሙዚቃ በማደማጥ ጆሮአቸውን ለአስከፊ አደጋ ያጋልጣሉ ሲል አስጠንቅቆ እንደነበረ ተመልክቷል። መጠን ባለፈ የደምፅ ደረጃ በ MP3 በየቀኑ ከአንድ ሰዓት በላይ ፤ ቢያንስ 5 ዓመታታ በተከታታይ የሚያዳምጡ ሰዎች፣ ከ 5-10 ከመቶ ፣ ከአነአካቴው ጆሮአቸው ደንቁሮ፣ ጽሙማን የመሆን አሳዛኝ ዕጣ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል፣ ኩኔቫ አስጠንቅቀዋል። አንድ ሰው የመስማት ችግር ያለበት መሆኑን እስኪገነዘብ ዓመታት ሊወስድ እንደሚችልም ፣ ኩኔቫ ጠቁመዋል።

የአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽን እንደሚገምተው በአውሮፓው ኅብረት አገሮች፣ ቁጥራቸው ከ 50-100 ሚሊዮን የሚጠጋ ወጣቶች፣ በየዕለቱ በ MP3 ይገለገላሉ። ዘመናዊ የሚባል የኢንዱስትሪ ውጤት ሁሉ እንከን-የለሽ ነው ብሎ ማሰብ እንደማይገባ ፣ ለኅሊና ደስታ ሲባል ጤንነትን እስከማወክ ላለመድረስ ፣ በኢንዱስትሪ በገፉት አገሮች የሚኖሩ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ በመልማት ላይ የሚገኙ አገሮች ተወላጆች የሆኑ ወጣቶች በጥሞና ሊያስቡበት ይገባል።

የ«ሱናሚ» ማስጠንቀቂያ አውታሮች መቶ-በመቶ አስተማማኝ አይደሉም ተባለ፤

ባለፈው ሳምንት በደቡብ ምሥራቅ እስያና በደቡብ ሰላማዊው ውቅያኖስ ፣ ፈንጠር ብለው በሚገኙ የተጫፈሩ ደሴቶች ላይ የደረሰው በባህር ወለል በተከሠተ የምድር ነውጥ ሳቢያ የተፈጠረው የውቅያኖስ ማዕበል መኖሪያ በሳሞዋና በቶንጋ ከባህር ልክ እምብዛም ከፍ ባላለ ቦታ የሚገኙ ከተሞችንን መንደሮችን አጥልቅልቆ 150 ያህል ሰዎች መግደሉ አይዘነጋም። ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ኢንዶኔሺያ ውስጥ ፣ በምዕራብ ሱማትራ፣ ፓዳንግ በተባለችው ከተማ በሪኽተር መለኪያ 7,6 የደረሰ የምድር ነውጥ፣ ቁጥራቸው ከ450 በላይ የሆነ ኑዋሪዎችን ህይወት ድንገት መቅጠፉ የሚታወሰ ነው። እ ጎ አ፣ ታኅሳስ 26 ቀን 2004 ዓ ም፣ ከህንድ የውቅያኖስ ወለል በብርቱ የምድር ነውጥ ሳቢያ የተቀሰቀሰው እጅግ አደገኛ የባህር ማዕበል (ሱናሚ) በ 20 ደቂቃ ውስጥ ኢንዶኔሺያ ጠረፍ ደርሶ በሰፊው በማጥለቅለቅ ከ 200,000 በላይ የሚሆን ህዝብ ደፍቆ መግደሉ አይዘነጋም። በስሪላንካ፣ ታይላንድና በአካባቢው በሚገኙ አገሮችና ደሴቶች ፣ ያኔ ባአጠቃላይ ከ 234,000 በላይ የሚሆን ህዝብ ነበረ ህይወቱን ያጣው። በመሆኑም የውቅያኖስን ማዕበል መከሠት አስቀድመው የሚጠቁሙ ይበልጥ አስተማማኝ ዘመናዊ አውታሮችን የመትከሉ አስፈላጊነት ከዚያን ጊዜ አንስቶ ትልቅ ግምት እንደተሰጠው የሚዘነጋ አይደለም። ባለፉት 4 ዓመታት ከመንፈቅ ገደማ ፣ በእስያና ሰላማዊው ውቅያኖስ የሚገኙ አገሮች፣ ራስን ከአደገኛ የውቅያኖስ ማዕበል ለመከላከል ፣ የተለያዩ፣ አስቀድመው ማስጠንቀቂያ የሚሰጡ አውታሮችን መትከላቸው ይታወሳል። ህዝብ፣ ዝቅ ካሉ የጠረፍ መኖሪያ ቦታዎች በአስቸኳይ ከፍ ወደአሉ ሥፍራዎች በመውጣት ህይወቱን እንዲያተርፍ፣ የሚያስጠነቅቅ የአደጋ ሁኔታ አስተጋቢ ድምፅ የሚያሰሙ መሣሪያዎች በየውቅያኖስ ዳር መትከል ብቻ ሳይሆን፣ በጥልቁ ውቅያኖስ በባህር ወለል የሚቀሰቀስ የምድር ነውጥን የሚመዘግቡ ማስጠንቀቂያ አውታሮችም ተተክለዋል። ኒውዚላንድና አውስትሬሊያ፣ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ በሚሰጡ የራሳቸው አውታሮች ይመካሉ። ጃፓንና ኢንዶኔሺያም የማስጠንቀቂያ አውታሮች አሏቸው፣ በተለይ ጃፓን በዚህ ረገድ ከብዙ ዓመታት በፊት አንስቶ የተራቀቀ ሥነ ቴክኒክ በመጠቀም፣ ራሷን ከጥፋት ለመከላከል ስትጥር ቆይታለች። ጃፓን ፣ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገሮችም መረጃ በመስጠት፣ ራሳቸውን ከድንገተኛ የውቅያኖስ ማዕበል እንዲከላከሉ ታግዛለች። ጥቂት የሰላማዊው ውቅያኖስ አካባቢ አገሮች፣ እ ጎ አ ከ 196 ዓ ም አንስቶ፣ የመረጃ ልውውጥ-ነክ ምርምራቸውን፣ ሃዋይ ከሚገኘው፣ 24 ሰዓት ሙሉ የምድር ነውጥ ይዞታን ከሚከታተለው የሱናሚ ማስጠንቀቂያ ማዕከል ጋር በማቀናጀት ይሠራሉ።

ያም ሆኖ፣ ኢንዶኔሺያንና ፓፑዋ ኒው ጊኒን በመሳሰሉ አገሮች፣ የሱናሚ ማስጠንቀቂያው መሣሪያ ፋታ ስለማይሰጥ በአደጋው በአመዛኙ በአደጋው መጎነጡ አይቀርላቸውም። «በውቅያኖስ ወለልም በወቅያኖስ የውሃ ልክ፣ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሰጪ አውታሮች ከመትከል ህዝብን ይበልጥ ማስተማር የተሻለ ነው፤ ከ 30 ሴኮንድ በላይ የምድር ነውጥ ካጋጠመ፣ ባስቸኳይ፣ ከፍ ወደአለ ቦታ ሮጦ ፣ ከሱናሚ ጥፋት ለመትረፍ መጣር ይበልጥ የሚበጅ ይሆናል» በማለት ምክር የሚሰጡ ጠበብት አልታጡም። በባህር ወለል በሚ ያጋጥም የምድር ነውጥ ሳቢያ የሚቀሰቀስ አደገኛ የውቅያኖስ ማዕበል(ሱናሚ) ለጥ ባለው ውቅያኖስ ፣ በሰዓት 800 ኪሎሜትር እንደሚከንፍ የታወቀ ሲሆን፣ በዚህ ፍጥነት ጠረፍ ላይ ሲደርስ፣ 30 ሜትር ከፍታ ያለውን ቦታ ሁሉ ነው የሚያጥለቀልቀው ።

(ሙዚቃ)-----------

በሻንጋይ፣ ቻይና የተወለዱትና የዩናይትድ እስቴትስ እንዲሁም የብሪታንያ ዜግነት ያላቸው Charles Kao,በኖቫ እስኮትያ፣ ካናዳ የተወለዱትና የዩናይትድ እስቴትስ እንዲሁም የካናዳ ዜግነት የያዙት Willard Boyle እንዲሁም አሜሪካዊው George Smith በፊዚክስ ፣ የዘንድሮው የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ለመሆን የበቁት ለዘመናዊው የመረጃ ሥነ-ቴክኒክ ሥር-ነቀል የሚሰኝ ውጤት በማስመዝገባቸው ነው። ቻርለስ ካዖ፣ የጽሑፍ፣ ድምጽም ሆነ ሙዚቃ፣ እንዲሁም የምስልና የቪዲዮ መልእክት ፣ ሴኮንድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ፣ በዓለማችን ዙሪያ ፣ ከአጽናፍ አጽናፍ በመስታውት መሰልም ሆነ ፕላስቲክ ሽቦዎች አማካኝነት እንዲተላለፍ ያበቃውን ሥነ-ቴክኒክ በማስተዋወቃቸው ነው። መልእክቱ የሚተላለፈው በብርሃን ፍጥነት ነው። የብርሃን ፍጥነት ማለት፤ ብርሃን ከመነሻው እስከመድረሻው የሚፈነጥቅበት ሲሆን ፣ ጉዞውም ሆነ ፍጥነቱ ፣ በሴኮንድ 300,000 ኪሎሜትር መሆኑ የታወቀ ነው። Boyle እና Smith ለዲጂታል ካሜራ «የኤሊክትሮኒክ ዐይን » የተሰኘውን ፣ የፎቶግራፍ ፊልምን መተካት የቻለውን የረቀቀ መሣሪያ በመፈልሰፍ ነው የኖቤሉ ሽልማት ተከፋዮች ለመሆን የበቁት።

ዘመናዊ ዲጂታል ካሜራዎች፣ የሚጠቀሙበት የፊልም ምትክ ፣ ራሱን፣ ከተፈለሰፈ ከሞላ ጎደል 150 ዓመት የሆነውን በቅመማ ሳይንስ የሚሰናዳውን የፎቶግራፍ ፊልም የሚተካ ወይም «ጊዜው ያለፈበት» የሚያሰኝ ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ እ ጎ አ በ1969 ተግባራዊ ለመሆን የበቃው የምርምራቸው ውጤት፣ በህክምናው ዘርፍ የወስጥ አካላትን በተሟላ ሁኔታ ለመመልከትና የበሽታ ዓይነቶችን ለመለየት፣ እንዲሁም የረቀቀ የቀዶ -ጥገና ህክምና ለማድረግም እንደበጀ የሚታወቅ ነው።

በፊዚክስ፣ ከዩናይትድ እስቴትስ፣ ሳይንቲስት ወይም ሳይንቲስቶች የኖቤል አሸናፊዎች ሲሆኑ የዘንድሮው 50ኛ ጊዜ መሆኑ ነው። እ ጎ አ በ 1907 ዓ ም፣ በፊዚክስ የመጀመሪያው አሜሪካዊ የኖቤል አሸናፊና ተሸላሚ አልበርት ሚቸልሰን ነበሩ።

ወደመገኛኛው ሥነ ቴክኒክ ስንመለስ፣ ቻርለስ ካዖ አያሌ ዓመታት አትኩረውበት የቆዩት እጅግ ዘመናዊ የመረጃ ማስተላለፊያ ዘዴ፣ በዓለም ዙሪያ እየተመናመነ የመጣው የመዳብ ማዕድን አስጨንቋጨው ለነበሩ ሁሉ ግልግል መሆኑ የሚታበል አይደለም። የአስዊድን አካዳሚ የኖቤል ሽልማት ሰጪ ቡድን አባል የፊዚክስ ፕሮፌሰር ላርስ በርግእሽትሮም የምርምሩ ውጤትና ሽልማቱ፣ የንግድ መስህብነት አይኖረውም ወይ በትንሹም ቢሆን ተጽእኖ አያሳድርም ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ--

«እኛ ፣ ምርምሩ ፣ ያስመዘገበውን ውጤት ነው የምናየው። ግኝቱ ነው ወሳኝ። ፣ ገዝፍ ያለውን ነገርና ከበስተጀርባው የሚኖረው ሌላ ጉዳይ ነው። እርግጥ ነው እንዲህ ዓይነቱ ግኝት ስኬታማ እንደመሆኑ መጠን ብዙ ኢንዱስትሪዎች መጠጋታቸውና በዚያም በኩል ብዙ ገቢ ማግኘት የሚችሉ መሆናቸው የሚታወቅ ነው። ነገር ግን በእኛ ውሳኔ ላይ አንዳች ተጽእኖ ያሳደረ አይደለም።»

ተክሌ የኋላ፣