በፈጠራዎቹ የጨቅላ ህፃናትን ህይወት የሚታደገው ባለሙያ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 01.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በፈጠራዎቹ የጨቅላ ህፃናትን ህይወት የሚታደገው ባለሙያ

ወጣት ሀብታሙ አባ ፎጊ ይባላል።የባዬ ሜዲካል ምህንድስና ባለሙያ እና በጅማ ዩንቨርሲቲ የባዬ ሜዲካል ህክምና የቴክኖሎጅ አና የፈጠራ ማዕከል አስተባባሪ ነው።ወጣቱ በከፍተኛ ገንዘብ ከውጭ የሚገቡ የህክምና መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ ይሰራል።በ2020 በቴክኖሎጂው ዘርፍ የአፍሪካ ወጣቶች ሽልማትን አግኝቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:53

ሳይንስና ቴክኖሎጂ


በኢትዮጵያ የህክምና መሳሪያዎች በአብዛኛው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ  ተገዝተው ከውጭ የሚገቡ ናቸው።ተገዝተው ወደ ሀገር ከገቡ በኋላም ቢሆን ብልሽት ካጋጠማቸው በሀገር ውስጥ የተሟላ የጥገና አገልግሎት ባለመኖሩ ለጥገና የሚወጣው ወጭ ቀላል አይደለም።ይህንን ችግር ለመፍታት ይመስላል ከወደ ጅማ አንድ ወጣት ባለሙያ የህክምና መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት ጀምሯል።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ከዚህ ወጣት ጋር ቆይታ አድርጓል።
ወጣት ሀብታሙ አባ ፎጊ የባዬ ሜዲካል ምህንድስና ባለሙያ እና ከፍተኛ ተመራማሪ ነው። ወጣቱ የመጀመርያና የሁለተኛ ዲግሪውን በባዮ ሜዲካል ምህንድስና እና በንግድ አመራር  ከጅማ ዩኒቨርሲቲ  አግኝቷል።በተማረበት የጅማ ዩንቨርሲቲ የባዬ ሜዲካል ህክምና የቴክኖሎጅና የፈጠራ ማዕከል አስተባባሪ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል። ወጣቱ በጎርጎሮሳዉያኑ 2015 ዓ/ም  የአፍሪካ ኢንተርፕረነር ሺፕ ሽልማት አሸናፊ በመሆን ባገኘው ገንዘብ  «ሲንቦና አፍሪካ ሄልዝ ኬር»  በሚል ስያሜ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስርቷል። በዚህ ተቋም ላለፉት ሰባት ዓመታት  ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን በከፍተኛ ገንዘብ ከውጭ ሀገር የሚገቡ የህክምና መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ምርምር  ሲያካሂድ ቆይቷል።ደክሞም አልቀረ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ  ያለ ጊዚያቸው ቀድመው ለተወለዱና ከክብደት በታች  ለተወለዱ ጨቅላ ህፃናት ሙቀት የሚሰጥ መሳሪያ በተሳካ ሁኔታ ሰርቷል።

ሁለተኛ ስራውም ህፃናት ከተወለዱ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ሚያጋጥማቸው በእንግሊዝኛው አጠራር «ጁዋንዲስ»ወይም የቆዳ ቀለም ቢጫ መሆን በሽታን የሚያክም መሳሪያ ነው።ይህ የህክምና መሳሪያ በፀሀይ ብርሃን እንዲሰራ ተደርጎ የተዘጋጄ በመሆኑ ኤለክትሪክ በሌላቸው  አካባቢዎች ጭምር ተደራሽ ማድረግ ይቻላል።
እንደ ባለሙያው ገለፃ እነዚህ ፈጠራዎች ከውጭ ከሚገቡ የህክምና መሳሪያዎች ጋር እኩል ጥራት ያላቸው እና የደረጃ መዳቢ ተቋም ያስቀመጠውን ዓለም አቀፍ መስፈርት ያሟሉ ቢሆንም፤የህክምና ፈጠራ ጥንቃቄን የሚጠይቅ በመሆኑ  ወደ ምርትና አገልግሎት የሚገብቡት ገና በቅርቡ ነው።
ጨቅላ ህፃናትን ከሞት ከሚታደጉት ሁለቱ የህክምና መሳሪያዎች  በተጨማሪ  የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ፤ ሀብታሙ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን የህክምና ኦክስጅን ማምረቻ መሳሪያና የኮሮና ተዋህሲን  ጨምሮ ሌሎች በአይን የማይታዩ ተህዋሲያንን ያለ ኬሚካል በአልትራ ቫዮሌት ጨረር በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የሚያፀዳ ማሽን ሰርቷል።ይህ ማሽን በከፍተኛ ጥራት በሀገር ውስጥ ተመርቶ በተለያዩ ቦታዎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ገልጿል።
 የህክምና መሳሪያዎች ግዢ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ  የሚጠይቅ  በመሆኑ የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ለሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ቀላል አይደለም።ተገዝተው ከውጭ ወደ ሀገር ከገቡ በኋላም ቢሆን ብልሽት ካጋጠማቸው በሀገር ውስጥ የተሟላ የጥገና አገልግሎት ባለመኖሩ ለጥገና የሚወጣው ወጭም የዚያኑ ያህል ነው።በዚህ የተነሳ በጤናው ዘርፍ የሚያስፈልጉ የህክምና መሳሪያዎችን ማሟላት  በአንዳንድ ሆስፒታሎች ካልሆነ በስተቀር በዝቅተኛ የጤና ተቋማት የማይታሰብ ነው። ያ በመሆኑ  የህክምና መሳሪያዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት እንደ ባለሙያው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል ።


ከተጠቀሱት በተጨማሪ በሂደት ላይ ያሉና ማረጋገጫ የሚጠብቁ በርካታ ስራዎች እንዳሉት የሚናገረው ሀብታሙ፤ በእነዚህ ስራዎቹ በጎርጎሪኑ 2015 የአፍሪቃ የኢንተርፕርነርሽፕ ሽልማትን፣በ2020 ደግሞ በቴክኖሎጂው ዘርፍ  የአፍሪካ ወጣቶች ሽልማትን አሸናፊ ሲሆን በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በተለያዩ የአፍሪቃ ሀገሮች በርካታ  ሽልማትቶችንና ዕውቅናዎችን አግኝቷል። 
ያም ሆኖ በመንገዱ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳጋጠሙት ይገልፃል።ከነዚህም ውስጥ ዘርፉ አዲስ በመሆኑ አንወጣዉም የሚል የራስ ስጋት፣ የመንግስት ተቋማት ድጋፍ ደካማ መሆን፣የመስሪያ ዕቃዎች ግዢ በሀገር ውስጥ እንደልብ ያለማግኘት፣የገንዘብ ችግር፣ የቤተ ሙከራ እና የባለሙያ እጥረት፣  ለፈጠራ ስራዎቹ ዕውቅናና ማረጋገጫ መስጠት የሚችል ልምድ ያለው ተቋም ባለመኖሩ  ማረጋገጫ አግኝቶ ቶሎ ወደ ስራ ለመግባት መቸገር ፣ እንዲሁም የህክምና መሳሪያዎች አስመጭና አከፋፋይ እንጅ አምራች ባለመኖሩ በሀገር ውስጥ አጋር ተቋማት አለማግኘት ይጠቀሳሉ። በዚህ የተነሳ ኬንያ ከሚገኝ እና በዘርፉ ከሚሰራ ተቋም ጋር ክፍተቱን ለመሙላት በአጋርነት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።ከሀገር ውስጥም ከጅማ ዩንቨርሲቲና ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር የሚያገኘውን  የተወሰነ ድጋፍ በመጠቀም  በአሁኑ ወቅት በሁለት ዕቅዶች ላይ ጠንክሮ መስራት ይፈልጋል።
"በሁለት ዕቅዶች ላይ እንሰራለን"። ካለ በኋላ ፤ለፈጠራዎቹ ማረጋገጫ ማግኘት እና ወደ ምርትና አገልግሎት ለመግባት የገንዘብ ድጋፍ ማፈላለግ መሆኑን አብራረቷል።


እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ የህፃናት ያለጊዚያቸው መወለድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጨቅላ ህፃናትን ለሞት የሚያበቃ ግንባር ቀደም ምክንያት ሲሆን፤ይህም በእስያ እና ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት የበረታ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት ከ15 ሚሊዮን በላይ ህፃናት ያለ ጊዜያቸው ይወለዳሉ።አንድ አራተኛ  ያህሉ ደግሞ ለሞት ይጋለጣሉ።ከነዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት  በደቡብ እስያና በአፍሪቃ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከሰሃራ በታች ባሉ  የአፍሪቃ ሀገሮች የሚወለዱ ናቸው።የባዮ ሜዲካል ምህንድስና ባለሙያው  ሀብታሙ ይህንን እና  ኢትዮጵያ በዘርፉ የሚገጥማትን ሌሎች  ችግሮች ለመፍታት ከሙያ አጋሮቹ ጋር በህክምናው ዘርፍ የጀመረውን  የምርምር  ስራ  አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic