በፈረንሳይ የስደተኞች ተቃዉሞ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 03.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

በፈረንሳይ የስደተኞች ተቃዉሞ

ወደ ብሪታንያ ለመሻገር ሲሉ በሰሜናዊ ፈረንሳይ ካሌ ዉስጥ በተለያዩ ቁሳቁሶች መጠለያ ሰርተዉ ይኖሩ የነበሩ ስደተኞች መንግሥት መኖርያቸዉን ካፈረሰባቸዉ በኋላ አንዳንድ ስደተኞች አፋቸዉን በክርና በመርፊ ሰፍተዉ የተቃዉሞ ሰልፍ አካሄዱ።

ስደተኞቹ መጠለያቸዉ በመፍረሱ ባካሄዱት የተቃዉሞ ሰልፍ « እኛም ሰዎች ነን» « የታለ የናንተ ዴሞክራሲ» « የታለ የኛ ነፃነት» የሚል መፈክርን አንግበዉ ታይተዋል። ኬር ፎር ካሊስ የተባለዉ የርዳታ ድርጅት ባልደረባ ክላራ ሞስሊ እንደሚሉት ስደተኞቹ ትኩረትን ይሻሉ።

«ከወራቶች ጀምረን እነዚህ ሰዎች ለመርዳት እየሰራን ነዉ ግን ምንም የተቀየረ ነገር የለም። ከዚህ በኋላ ማድረግ የሚችሉትን ነገር ስለማያዉቁ ትኩረት ለማግኘት ይህን እያደረጉ ነዉ።»

ፈረንሳይ ካሌ ላይ በፖሊስ ጥበቃ የተደረገላቸው የግንባታ ሰራተኞች ስደተኞች ሰርተዉት የነበረዉን መጠለያ ሰፈር ማፍረስ የጀመሩት ባለፈዉ ሰኞ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ይኖሩባቸዉ በነበሩት መጠለያዎች አካባቢ የንፅሕና አጠባበቅ ሁኔታዉ እጅግ የተበላሸ እንደነበር ተገልጾዋል። ስደተኞቹ በካሌ በኩል በሚያልፉ ባቡሮችና ተሽከርካሪዎች ላይ በመንጠላጠል ወደ ብሪታንያ ለማለፍ እንደሚሞክሩ ተመልክቶአል። የፈረንሳይ መንግሥት ካሌ ላይ መጠለያ ተክለው የሚኖሩትን በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ዉስጥ ለማስፈር ይፈልጋል።

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ