በጭቃ የተገነባው ዞማ ቤተ-መዘክር | ባህል | DW | 08.04.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

በጭቃ የተገነባው ዞማ ቤተ-መዘክር

"ዞማ ቤተ-መዘክር" የሚል ስያሜ የተሰጠው የዚህ ግዙፍ ማዕከል ሀሳብ የተጠነሰሰው በኢትዮጵያዊቷ አንትሮፖሎጂስት ወይዘሮ መስከረም አሰግድ ቢሆንም በ 2019 ዓ.ም በአሜሪካ በተካሄደው የስሚዝሶኒያን የአፍሪቃ አርት ብሔራዊ ሙዝየም ሽልማት አሸናፊው የሥነ -ጥበብ ባለሙያው አቶ ኤልያስ ስሜም አስተዋፆም ቀላል ግምት አይሰጠውም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:46

በጭቃ የተገነባው ዞማ ቤተ-መዘክር

ከጥንት ጀምሮ ቤተመዘክሮች የዓለምን ብሎም የሕዝቦችን ታሪክ፣ ባህል፣ ትውፊት፣ ወግና ልማድ፣ ቅርስና የአኗኗር ዘይቤ ሁሉ ያለፈውን የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን አጠቃላይ ሁነት ሰንደን እና አደራጅተን በትውልድ ቅብብሎሽ እንዲተላለፉ የምናቆይባቸው የማንነታችንና የአሻራዎቻችን መገለጫ ማዕከላት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ::ቀደም ባለው ዘመን በተለይም የንጉሳውያንን ገድሎችንና ተአምራቶች እንዲሁም የአብያተ-ክርስቲያናትን ታሪኮችና ትውፊቶች የሚገልፁ የብራና ሰነዶች በእምነት ተቋማትና በቤተመንግስቶች አካባቢ ብቻ ተቀምጠው ለትውልድ ሲተላለፉ ቢቆዩም ከሮማና ግሪክ ስልጣኔ በኋላ በተለይም በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ታላላቅ በሚባሉ ግለሰቦች መኖሪያ ቤት ጭምር የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስብስቦችን የማስቀመጥ ባህል በብዛት እየተለመደ መምጣቱን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ:: ዛሬ ትውልድን በመቅረፅ ረገድ የቤተ-መዘክሮች አገልግሎት ፋይዳው እጅግ የላቀ በመሆኑ ሀገራት በተለያዩ ዘርፎች ለጥናትና ምርምር የሚያግዙ ልዩ ልዩ ቤተ መዘክሮችን በስፋት ሲገነቡ ይታያል:: በኢትዮጵያም በዋና መዲናይቱ አዲስ አበባ መካኒሳ በተለምዶ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ወይም ኦልድ ኤርፖርት በሚባለው አካባቢ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች አነሳሽነት በአገልግሎቱ ዓለማቀፍ ይዘት ያለው ተፈጥሮና ጥበብን በአንድነት ያጣመረ አስገራሚና በዓይነቱ ልዩ የሆነ በጭቃ ኪነ ህንጻ የተገነባ ቤተ-መዘክር ተመስርቶ የስራ እንቅስቃሴውን በይፋ ጀምሯል:: "ዞማ ቤተ-መዘክር" የሚል ስያሜ የተሰጠው የዚህ ግዙፍ ማዕከል ሀሳብ የተጠነሰሰው በኢትዮጵያዊቷ አንትሮፖሎጂስት ወይዘሮ መስከረም አሰግድ ቢሆንም በ 2019 ዓ.ም በአሜሪካ በተካሄደው የስሚዝሶኒያን የአፍሪቃ አርት ብሔራዊ ሙዝየም ሽልማት አሸናፊው የሥነ -ጥበብ ባለሙያው አቶ ኤልያስ ስሜም አስተዋፆም ቀላል ግምት እንደማይሰጠው ለማወቅ ችለናል::

አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት ወይዘሮ መስከረም ከ 25 ዓመታት በፊት ጀምሮ ከሚኖሩበት አሜሪካ ቤተሰባቸውን ይዘው ለእረፍት ወደ ሀገርቤት በሚመጡበት ወቅት በተለይም ለጉብኝት ወደተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ ጉዞ ባደረጉባቸው አጋጣሚዎች ያስተዋሉት የማህበረሰቡ ቀደምት ባህልና ከተፈጥሮ ጋር ያለው ቁርኝት በእጅጉ ያስደምማቸው ስለነበር ባህልና ተፈጥሮን ያጣመረ ማዕከልን በትውልድ ሃገራቸው የመመስረት ውጥናቸው በአዕምሮዋቸው እንደሰረፀ ይናገራሉ:: ፀኃፊ፣ የአርት ኪውሬተር፣ የስነ ሰብዕ /አንትሮፖሎጂ/ እና የኪነ ጥበብ ዘርፈ ፈርጀ ብዙ ባለሙያዋ ወይዘሮ መስከረም ከኢትዮጵያ ሌላ በሴኔጋል ዳካር፣ በሚላን፣ በአውስትራሊያ ሲድኒ፣ በሎስ አንጀለስ፣ በዋሽንግተን፣ ኒውዮርክና የተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች፣ በጀርመን ድሬስደን፣ በርሊንና ሽቱትጋርት ከተሞች ጭምር ላለፉት 20 ዓመታት ከ 50 በሚልቁ ኤግዚቪሽኖች ሥራዎቻቸውን በዓለም አቀፍ መድረኮች አቅርበዋል::በፖላንድ ዋርሶም በሴንተር ፎር

ኮንቴምፖራሪ አርት ተጋብዘው ልምድ፣ ዕውቀትና ክህሎታቸውን አካፍለዋል:: ለንባብ ካበቋቸው የህትመት ስራዎቻቸው መካከልም ዳይቪንግ ፎር ኻኒ፣ ዘሪሁን የትምጌታ;- ዘ ማጂክ ዩኒቨርስ ኦፍ አርት በግላቸው የሚጠቀሱ ሲሆኑ ፤ከፕሮፌሰር አበበ ዘገየ ጋር ደግሞ "ሙላቱ አስታጥቄ;- ዘ ሜኪንግ ኦፍ ኢትዮ ጃዝ" የተሰኘ መጽሐፍን በጋራ አሳትመው ለአንባብያን አቅርበዋል:: የሥነ ጥበብ ሥራዎች ለሕዝብ ከመቅረባቸው አስቀድሞ ብቃትና ችሎታ ያላቸውን ባለሙያዎች በጥንቃቄ መምረጥን እንዲሁም ተስማሚ መድረክ ማመቻቸትን የሚጠይቀውን እምብዛም በኢትዮጵያ ያልተለመደ የኮንቴምፖራሪ አርት ማዕከልን እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባና በደቡባዊ ድሬዳዋ ክፍል አቅራቢያ በምትገኘው ሃርላ በምትሰኘው መንደር ለማስፋፋት ስኬታማ እንቅስቃሴዎችንም ባለሙያዋ አከናውነዋል:: በሁለቱ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ እየተከናወነ የሚገኘው የዞማ ቤተ-መዘክር ግንባታም ጥራትና ይዘት ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ በተጨማሪም በዓይነቱ ልዩ እንዲሆን ኢትዮጵያውያን አርክቴክቶች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ የስነ-ጥበብ ባለሙያዎችና የስነ-ሰብዕ /አንትሮፖሎጂ/ ጠበብቶች ጭምር በተለያዩ ጊዜያት አሻራቸውን አሳርፈውበታል::

ዞማ ሽፈራው ኑሮዋን በአሜሪካ ምድር ያደረገች ልዩ ተፈጥሮና ድንቅ የጥበብ ክህሎት የነበራት ወጣት የጥበብ ባለሙያ ነበረች:: ይህች ብዙ ተስፋ የተጣለባት ወጣት ገና በሃያዎቹ ዕድሜዋ ነበር ባጋጠማት የማህፀን ካንሰር ህመም በህክምና ስትረዳ ቆይታ አዲስ አበባ ውስጥ እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1979 ዓ.ም ሕይወቷ ያለፈው:: የዞማ ቤተመዘክር መስራችና የወጣቷ የቅርብ ጓደኛ አንትሮፖሎጂስቷ ወይዘሮ መስከረምም ማዕከሉ ወጣቷን እንዲዘክርና ሌሎች ታዳጊዎችም የሷን ድንቅ ፈለግ እንዲከተሉ በማሰብ መጠሪያ ስያሜው አድርገውታል:: በአሜሪካ ዩነቨርሲቲ በሶስዮሎጂና ካልቸራል አንትሮፖሎጂ የትምህርት ዘርፎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው ኢትዮጵያ ውስጥ የመመረቂያ ጥናትና ምርምራቸውን የሰሩት ባለሙያዋ በኦሮሞ ብሄር የኢሬቻ ክብረ በዓል፣ በሲዳማ የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ ዝግጅት፣ በጉራጌ ዞን፣ በትግራይ፣ በወሎና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚከናወኑ የተፈጥሮንና ጥበብን ቁርኝት ያዘመዱ ዘመን ተሻጋሪ ጥንታዊ ባህሎች አስገራሚ ገፅታ ተፈጥሮና ባህልን ያጣመረ ቤተ-መዘክር በሃገር ውስጥ ለመገንባት እንዳነሳሳቸው  ባደረግነው ውይይት ገልፀውናል።

እንዳልካቸው ፈቃደ 

ታምራት ዲንሳ 

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic