1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጦር ሜዳ የተገኘዉ ድል በሰላሙም ይደገማል-ጠ/ሚ ዓብይ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 23 2015

ደቡብ ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ዶክተር ዓብይ ሳዉላ-ጎፋ ዉስጥ አቀባበል ላደረጉላቸዉ ባለስልጣናትና ነዋሪዎች እንደነገሩት የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የሚፀናዉ የጦር ሜዳዉ ድል በሰላም፣የሰላሙ ደግሞ በብልፅግና ሲደገም ነዉ

https://p.dw.com/p/4IyMY
Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahemed im Süden
ምስል Southern Ethiopian regional office

ኢትዮጵያዉያን «እንኳን የሰዉ የዱር እንስሳትም መብት ያከብራሉ»ጠሚ ዓብይ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ «በጦር ሜዳ ያገኘነዉ» ያሉት ድል በሰላምም ይደገማል አሉ።ደቡብ ኢትዮጵያን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ዶክተር ዓብይ ሳዉላ-ጎፋ ዉስጥ አቀባበል ላደረጉላቸዉ ባለስልጣናትና ነዋሪዎች እንደነገሩት የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የሚፀናዉ የጦር ሜዳዉ ድል በሰላም፣የሰላሙ ደግሞ በብልፅግና ሲደገም ነዉ።በመንግስታቸዉ ላይ የሚሰነዘረዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት ወቀሳና ትችትም «እንኳን የሰዉ የዱር እንስሳት መብትም እንጠብቃለን» በማለት አጣጥለዉታል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በሳውላ ምን አሉ ?   

ትናንት አመሻሽ ላይ ወደ ደቡብ ክልል ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ በክልሉ የጋሞና የጎፋ ዞኖችን ጎብኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ አቀባበል ለማድረግ ለተሰባሰቡ የከተማይቱ ነዋሪዎች ንግግር አሰምተዋል፡፡ አብይ በዚሁ ንግግራቸው በስም ያልጠቀሷቸው አገራትና ተቋማት በሰው ልጆች መብት አጠባበቅ ላይ ያቀርባሉ ያሏቸውን ክሶች አጣጥለዋል ፡፡ 

‹‹ አንዳንድ አገራት የሰው ልጅ መብት መከበር አለበት ›› የሚሉ ወቀሳና ክሶች ይቀርባሉ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ‹‹ ለእነኝህ ወዳጆቼ ያለኝ መልዕክት መጥታችሁ በጎፋና አካባቢው የሚገኘውን የማዜ ፓርክን ተመልከቱ ፡፡ እኛ ኢትዮጲያን የሰው ልጆች መብት ቀርቶ የዝሆንና የአንበሳ መብቶችን  የምንጠብቅ ሰዎች ነን ›› በማለት በሳውላ ከተማ ስታዲየም ለተሰበሰቡ ተዳሚዎች ንግግራቸውን አሰምተዋል ፡፡  

Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahemed im Süden
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት የተሰበሰበ ጎፋ ህዝብ ምስል Southern Ethiopian regional office

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በደቡባዊ የአገሪቱ ክልል ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት መንግሥታቸው ከህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ ጋር እያካሄደ በሚገኘው ጦርነት ዋና ዋና የሚባሉ የትግራይ ከተሞችን መቆጣጠሩን እየገለፁ ባለበት ወቅት ነው፡፡ በጦርነት የተገኘውን ድል በሰላም መድገም አለብን የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሳውላ ንግግር መንግሥታቸው በጦርነቱ የበላይነቱን እየያዘ ስለመምጣቱ ይበልጥ ያረጋገጡበት ይመስላል፡፡  

ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚሁ ንግግራቸው ‹‹ ከእናንተ ጋር ሆነን በጦርነት ያገኘነውን ድል በሰላም መድገም ይኖርብናል ፡፡ በጦርነት የተገኘ ድል በሰላም ፣ በሰላም የተገኘ ድል ደግሞ በብልፅግና ካልተደገመ  የኢትዮጲያ ህልውና በአንድ ወይም በሌላ መልኩ መደፈሩ አይቀርም ፡፡ ሥለዚህ በአንዱ ድል ሳንኩራራ በጦርነት ያገኘነውን ድል በሰላም በመድገም የማትደፈር ፣ የተከበረችና ለልጆቿ ምቹ የሆነች  ኢትዮጲያን በጋራ እንድንፈጥር አደራ እላለሁ   ›› ብለዋል ፡፡ 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እየተጎበኘ የሚገኘው የደቡብ ክልል በመዋቅር አደረጃጀት ፣ በወሰን ይገባኛልና የማንነት ጥያቄዎችን መሠረት ያደረጉና ሄድ መለስ የሚሉ ግጭቶች የሚስተዋሉበት ነው፡፡ ያም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አካባቢው ያለውን የመልማት እድል ከመጥቀስ ባለፈ በክልል የአደረጃጀት ጥያቄም ሆነ በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ በንግግራቸው ያሉት ነገር የለም፡፡ 

የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር  እንድምታ  

ዶቼ ቬለ DW ያነጋገራቸው የፖለቲካ ሳይንስ አጥኚውና የደቡብ ክልል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን የሥራ ሃላፊ የነበሩት አቶ ደያሞ ዳሌ ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ያደረጉት ንግግር የራሱ እንድምታ አለው ይላሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንና በሰብአዊ መብት ተቋማት ሥም የሚወጡት መግለጫዎች የማሸማቀቅና የማስጨነቅ ዘመቻ አይነት ባህሪ አላቸው ፡፡ጠቅላይ ሚንስትሩ በንግግራቸው አነኝህ መግለጫዎች ተጨባጭ ሁኔታዎችን የሚገልጹ እንዳልሆኑ ለማሳየት ሞክረዋል ፡፡ አኛ ሰብአዊ መብት የመጣስ ባህሪያችንና ባህላችን አይፈቅድልንም ፡፡ ትክክለኛ ባህሪያችን እንደውም ለእንሰሳት ጭምር ማዘንና መብታቸውን ማክበር ነው የሚል መልዕክት ያስተላለፉበት ነው  ›› ብለዋል   

‹‹ በጦርነት የተገኘውን ድል በሰላምም መድገም ›› በሚል የጠቀሱት ሀሳብ የመንግስታቸውን ቀጣይ አቅጣጫ የሚያመላክት መሆኑን አቶ ደያሞ ተናግረዋል፡፡ 

‹‹ ጠቅላይ ሚንስትሩ በጦርነት ድል አድረገናል የሚሉት  የፌዴራሉ ምንግሥት ቀደምሲል በአፋርና በአማራ ክልሎች በትግራይ ተዋጊዎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ከማስለቀቁም በላይ ትግራ ክልል ውስጥ ተጨማሪ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል ፡፡ በንግግራቸው ማሳየት የፈለጉት ባሸነፉባቸው የትግራይ  አካባቢዎችም ሆነ በተቀሩት የኢትዮጲያ አካባቢዎች ሰላም መስፈን አንዳለበት የጠቆሙበት ነው  ›› ብለዋል አቶ ደያሞ ፡፡ 

ሸዋን ግዛዉ ወጋየሁ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ