በጦርነቱ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ይዞታ | አፍሪቃ | DW | 14.11.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በጦርነቱ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ይዞታ

UNHCR ለስደተኞችና ለሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ደህንነት ሲባል እርዳታ መስጠት እንዲቀጥል እንዲፈቀድለትም ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጥሪ አቅርቧል።በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተጠሪ አን ኤንኮንትር UNHCR እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጋ መድረስ እንዲችል እየተነጋገረ መሆኑን ገልጸው ይህ ግን ቀላል እንዳይደለ አስረድተዋል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:05

በጦርነቱ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ይዞታ

ማክሰኞ ጥቅምት 24 ፣2013 ዓም ለሊት ትግራይ በሚገኘው የሰሜን እዝ ጦር ላይ ጥቃት መፈጸሙን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከተነገሩ በኋላ  የተጀመረው የፌደራል መንግሥትና የትግራይ ክልል መንግሥት ውጊያ እንደቀጠለ ነው።ከሁለቱም ወገን ቁጥራቸው በውል ያልተነገረ ሰዎችን ሕይወት ባጠፋው በዚህ ጦርነት ምክንያት፣በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችም ወደ ጎረቤት ሱዳን መሰደዳቸውንና በአካባቢያቸውም መፈናቀላቸውን፣የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR አስታውቋል።ከመካከላቸው አንዷ ከጦርነቱ ሸሽተው ሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ ባለ አንድ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ እኝህ እናት ናቸው።ተፈናቃይዋ ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት አቅመ ደካማ ዘመዶቻቸውን ጥለው ነው ወደ ሱዳን የተሰደዱት። 
« እናቴን ቤተ ክርስቲያን ነው የተውኩዋት።በእድሜ የገፋች ናት።ወንድሜ ዓይነ ስውር ነው።እሱንም እዚያው ጥለነው ነው የመጣነው፤ምግብም ውሀም የለም።ሁሉም መሸሽ ያዘ፤መንገድ ላይ የተገደሉ ሰዎችን አይተናል።  ምን ማድረግ ነበረብን? የሸሸነው ነፍሳችንን ለማዳን ነው »
UNHCR  ከሦስት ቀናት በፊት፣ሱዳን የገቡት ሴቶችና ህጻናት የሚገኙባቸው ስደተኞች ቁጥር 7ሺህ እንደሆነ ገልጾ ነበር።እንደ ትንንቱ  መግለጫው ደግሞ ይህ አሃዝ በእጥፍ ጨምሯል። የኮሚሽኑ የውጭ ጉዳዮች ከፍተኛ መኮንንና የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተልዕኮ አስተባባሪ ጁልየት ስቲቭንሰን ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣እንደተናገሩት እስከ ትናንት ድረስ ከ14 ሺህ በላይ ሰዎች  ከኢትዮጵያ ድንበር አቋርጠው ሱዳን ገብተዋል።  እዚያው ትግራይ ክልል ውስጥም በርካቶች ተፈናቅለዋል። 
«ሁኔታው እጅግ ፈታኝ ነው።በትግራይ ክልል አሳዛኝ ክስተቶች አይተናል። ከጎርጎሮሳዊው ህዳር 4 ወዲህ ግጭቱ እየተባባሰ ቀጥሏል።አሁን 14,500 ስደተኞች ወደ ጎረቤት ሱዳን

መሰደዳቸውን አይተናል።በትግራይ ክልል ውስጥ ደግሞ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተፈናቃዮች ይገኛሉ።»
ስቲቭንሰን በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉትን ቁጥር ለማወቅ እልቻልንም ይላሉ።ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ግንኙነት መቋረጡን ነው።መንገዶች ተዘግተዋል።በአካባቢው የስልክ ግንኙነትና ኢንተርኔት እንደሌለ መብራትም እንደሚቆራረጥ የነዳጅ እጥረትም እንዳለ የተናገሩት ስቲቭንሰን በነዚህ ምክንያቶች UNHCR  ምን ያህል የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዳሉ፣ ምን ያህሉ ደግሞ ከአካባቢያቸው ለመሸሽ መፈናፈኛ እንዳጡ ለመረዳት መቸገሩንም አስረድተዋል።ከዚህ ሌላ ከኤርትራ ተሰደው ትግራይ የተጠለሉ ስደተኞች ይዞታም አሳሳቢ ነው እንደ UNHCR ።ምንም እንኳን መጠለያዎቹ በግጭት ቀጣናዎች ውስጥ ባይገኙም UNHCR እንደሚለው እየተባባሰ በሄደው የፀጥታ ችግር ሰበብ የስደተኞቹና የሰብዓዊ የሠራተኞቹ ደህንነት ያሳስበዋል።UNHCR የሚረዳቸው  ከ96 ሺህ ይበልጣሉ የተባሉ ኤርትራውያን ስደተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ አራት የስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ።ከመካከላቸው የተወሰኑት በጦርነቱ ምክንያት ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ እንደስቲቭንበርግ ።ለዚህም ድርጅቱ መፍትሄ ያለውን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው።
«እንዳለመታደል ሆኖ ግጭቱ በትግራይ ከሚገኙት የስደተኞቹ መጠለያዎች ወደ አንዱ እየተጠጋ ነው።  6500 ስደተኞችን ካስጠጋው መጠለያ።እናም ትግራይ ከለላ ሽተው የሄዱ ሰዎች እንደገና እዛው ትግራይ ውስጥ ለመፈናቀል እየተገደዱ ነው።አሁን የነበሩበትን መጠለያ እየለቀቁ ነው።እነርሱን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ሁለተኛው መጠለያ ለማስፈር ዝግጅት እያደረግን ነው።»
ጁልየት ስቲቭንሰን በፀጥታ ችግር ምክንያት UNHCRን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች በመጠለያው መቆየት አለመቻላውን ገልጸዋል።በUNHCR መግለጫ መሰረት ሱዳን የገቡት ስደተኞች በሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኙት በገዳሪፍዋ ሉድጊ እና በከሳላው ሃምዳየት ኬላዎች አጠገብ ባሉ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ነው ያሉት።በየ24 ሰዓቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሱዳን መግባታቸው መቀጠሉና ፣ጦርነቱም አለመቆሙ የተሰዳጁ ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉ እንደማይቀር ነው UNHCR የሚገምተው። ስቲቭንሰን 

«በአሳዛኝ ሁኔታ በሚቀጥሉት ቀናት ተጨማሪ ስደተኞች ድንበር አቋርጠው ሱዳን  ይመጣሉ ብለን እየጠበቅን ነው።በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ 14 500 ሰዎች ድንበር ተሻግረው መሰደዳቸው እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው።እንደ UNHCR የዓለማችን ስደተኞች ቁጥር እንዲጨምር አንፈልግም።እንዳለመታደል ሆኖ ግን እውነታው ይሄ ነው።ግጭት ሲከሰት ሰዎች  ምግብ ውሃ ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ለደህንነታቸው ለቤተሰባቸው ሲሉ ለመሸሽ ይገደዳሉ።»
ወደ ሱዳን በሚጎርፈው ስደተኛ ምክንያት ተጨማሪ እርዳታዎች እንደሚያስፈልጉት UNHCR በተለያዩ ጊዜያት በሰጣቸው ማብራሪያዎች አስገንዝቧል።የድርጅቱ የውጭ ግንኘቶች ከፍተኛ መኮንን ስቲቨንሰን ከዚህ ሌላ ድርጅታቸው ጦርነት በሚካሄድባቸው ስፍራዎች እርዳታ ማቀበል በድንበር አካባቢም መግባት አለመቻሉ ችግሩን ማባባሱ እንደማይቀር አሳስበዋል። 
«ከሰብዓዊነት አንጻር በአካባቢው አስፈላጊ እርዳታዎችን ለማቅረብ ባለመቻላችን በዚያ ያለው የእርዳታ ክምችት እየቀነሰ ይሄዳል።በዚህ ግጭት አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎችን የእርዳታ ፍላጎትም ማሟላት አንችልም።አሁንም እርዳታዎችን በምድርም ሆነ በአየር ማቀበል አይቻልም።»
UNHCR ለስደተኞችና ለሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ደህንነት ሲባል እርዳታ መስጠት እንዲቀጥል እንዲፈቀድለትም ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጥሪ አቅርቧል።በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተጠሪ አን ኤንኮንትር UNHCR እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጋ መድረስ እንዲችል እየተነጋገረ መሆኑን ገልጸው ይህ ግን ቀላል እንዳይደለ አስረድተዋል። 
«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአጠቃላይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጋ መድረስ እንዲቻል እየተደራደረ ነው።ሰብዓዊ ኮሪዶር እንዲከፈትልን ጠይቀናል።ውስብስቡ ነገር  ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ከክልሉ ባለሥልጣናትም ጋር ነው መደራደር ያለብን። ይህ ደግሞ ሁሌም ቀላል አይደለም። »

ይህ እንዲስተካከል በአጠቃላይ የተመድ ድርጅት  ግፊቱን መቀጠሉን የተናገሩት ስቲቨንሰን የጸጥታው ችግር ግን በስደተኞች መጠለያ ጠባብ መግቢያ ያገኙትን የድርጅታቸውን ባልደረቦች እንደ ልብ ሊያንቀሳቅሳቸው አለመቻሉንም ነው የገለጹት።
«በተጨባጭ በአካባቢው የሚገኝ ህዝብ ጋ ለመድረስ እጅግ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው።በዚህ ምክንያትም ሁሉንም አማራጮች እየፈለግን ነው።በተለይ በመጠለያዎች ለሚኖሩ ኤርትራውያን ስደተኞች የትኞቹን አማራጮች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባን እና ከተቻለም ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የሚቻልበትን መንገድ እየተመለከትን ነው። 
ከዚህ ጎን ለጎን UNHCR ሌሎች ጎረቤት አገራት ድንበራቸውን ለስደተኞች ከፍት እንዲያደርጉም ተማጽኗል።ድርጅቱ ስደቱ እንዲቀንስ ቢመኝም ተጨባጩ ሁኔታ ግን ያን የሚያሳይ ሆኖ አልተገኘም።\
«ወደ ሌሎች ሃገራት የሚደረገው ስደት ይቀንሳል ብለን ተስፋ እናደርጋለ።ሆኖም አሁንም በርካታ ሰዎች ወደ ሱዳን እየተሰደዱ ነው።ከበጎው ጎን ጋር ለመቆየት እንሞክራለን። እንደሚመስለኝ ግን እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እየተመለከትን ነው።»  
የተመድ ዛሬ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎችና በትግራይ ክልል መካከል የሚካሄደው ግጭት ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችልና እስካሁንም የጦር ወንጀሎች ሳይፈጸሙ እንዳልቀሩ ስጋት አለው። ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ እስከ ትናንት ድረስ ሱዳን ከገቡት ከ14,500 በላይ ስደተኞች ግማሹ ህጻናት ናቸው።ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው አል ፋሽካ በተባለችው ከተማ የገቡ ህጻናትና ሴቶች የሚያመዝኑባቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ስደተኞች በቂ ምግብና ውሃ እያገኙ አይደለም።ሱዳን ድንበር ላይ የምትገኘው አልፋሽካ ከ7ሺህ በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች ነው።የዓይን ምስክሮች እንደሚሉት የፌደራል መንግሥት ኃይሎችና የትግራይ ክልል ሠራዊት ግጭት በመባባሱ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን ይሸሻሉ ብለው ይጠብቃሉ።
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች