በጥያቄ የተሞላዉ የዓለም የምጣኔ ሃብት መድረክ | ኤኮኖሚ | DW | 23.05.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

በጥያቄ የተሞላዉ የዓለም የምጣኔ ሃብት መድረክ

በመካከለኛዉ ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ ያለዉን የምጣኔ ሃብትና የተወሳሰበ የፓለቲካ ሁኔታ ለማቀናጀት አልሞ የተነሳዉ ሶስተኛዉ የዓለም የምጣኔ ሃብት መድረክ በትናንትናዉ ዕለት ተጠናቀቀ። ለሶስት ቀናት የዘለቀዉ ይህ ጉባኤ ከመልሶች በላይ በጥያቄ ተጥለቅልቆ ነዉ ያበቃዉ።

ለመሆኑ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት እንደሚሉት ለዲሞክራሲ ማበብ የሚያግዝ መሰረት በአረቡ አለም አለ ወይ?
ይህ ከሆነ ታዲያ ለምን በጣት የሚቆጠሩ የአዉሮፓ ባለስልጣናትና የንግዱ ዓለም መሪዎች ብቻ በዮርዳኖሱ የሶስት ቀን ስብሰባ ላይ ሊገኙ ቻሉ?
የአረብ አገሮችስ እንዴት ነዉ በፈጣን ሁኔታ እያደገ ከሚገኘዉ የእስያ ምጣኔ ሃብት ጋር ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉት?
ለምን ቢባል የዓለም ባንክ የሚፈልገዉ የእድገት ደረጃ ፈጣን እድገት ካስመዘገበዉ ከእስያ ምጣኔ ሃብት የሚነፃፀር የእድገት ሁኔታ ነዉና። ይህንና ይህን መሰል መልስ ፈላጊ መሰረታዊ ጥያቄዎች የተነሱበት መድረክ ነበር።
የዓለም ከፍተኛ የንግድና የፓለቲካ ሰዎችን እንዲያሳትፍ በታቀደዉ በዚህ ስብሰባ ወቅት የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት በጠንካራ ተሟጋችነት ተሳታፊ ነበሩ።
በዚያ ዉጥረት በነገሰበት የዮርዳኖሳዉያን የስብሰባ አዳራሽ አሜሪካዉያን የሚሉት የማሻሻያ ሃሳብ ተቀባይነት ቢያገኝ በአህጉሩ ተስፋ ሰጪ የሆነ እድገት በያቅጣጫዉ እንደሚኖር አበክረዉ ነዉ የገለፁት።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባለቤት ወ/ሮ ላዉራ ቡሽ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ባጠቃላይ በመካከለኛዉ ምስራቅ የበልግ ወቅት ተስፋ እያየን ነዉ በማለት እይታዉን ጠቅለል አድርገዉ አቅርበዋል።
የአሜሪካ ምክትል የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎቹም እሳቸዉ ያመላከቱትን እይታ የሚያጠናክሩ ድርጊቶችን ጠቅሰዋል።
ከነዚያ መካከልም በኢራቅ የተካሄደዉ ምርጫ፤ የሶሪያ የመረጃ ሃይል ከሊባኖስ መዉጣት፤ የፍልስጤም አዲስ መሪ ማግኘትና በኩዌት ሴቶች በምርጫ ድምፅ ለመስጠት መቻል ይገኙበታል።
በአንፃሩ የአዉሮፓያን በስብሰባዉ መገኘታቸዉ ዝምታ የታከለበት ነበር።
የህብረቱ የንግድ ኮሚሽነር ፔተር ማንዴልሶን በአገልግሎት ረገድ ስላለ ግልፅ ንግድ ሲናገሩ የአዉሮፓ ፓርላማ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ቦሬል ደግሞ በፓርላማ ዉስጥ ሊኖር ስለሚገባዉ ዲሞክራሲ ተናግረዋል።
በእለቱም የአህጉሩን የወደፊት የምጣኔ ሃብት ይዞታ በተመለከተ ሰፋ ያለ ዉይይት ተካሂዷል።
ሆኖም አህጉሪቱ ልትወጣዉ የሚገባት ከፊቷ የተደቀነዉ የምጣኔ ሃብት አቀበት እንዴት ባለ መልኩ ይሁን የሚለዉ ተፍታቶ አልቀረበም።
የዓለም ባንክ እንደሚለዉ ይህች ሰበበኛ አህጉር በሚቀጥሉት 20 አመታት በ25 በመቶ ስራ አጥነትን ማጥፋት ካለባት በአመት ከ6 እስከ 7 በመቶ እድገት ማሳየት ይኖርባታል። እዚህ ጋ መታየት ያለበት አጠቃላይ እድገቱ 3.7 በመቶ ሆኖ መቆየቱን ነዉ።
የአዉሮፓ ህብረቱ ማንዴልሰን በሰንጠረዥ ለማሳየት እንደሞከሩት የንግዱ ሁኔታ ለዉጥ ያልታየበት ነዉ።
ይህንንም ሲያብራሩ የመካከለኛዉ ምራቅና የሰሜን አፍሪካ በጋራ ከነዳጅ ዘይት ሌላ ለዉጪ ንግድ የሚያቀርቡት ከሃንጋሪ ጋር ሲተያይ በጣም ጥቂት ነዉ በማለት ለማሳየት ሞክረዋል።
በዚህ ስብሰባ የአረብ ባለስልጣናትና የአካባቢዉ የንግድ ተቋማት ሃላፊዎች በብዛት በስብሰባዉ ተካፍለዋል።
የዓለም የምጣኔ ሃብት መድረክ ባለስልጣን እንደሚሉት በዚህ ዓለም አቀፍ ሆኖ ሳለ ትኩረቱን አህጉራዊ ጉዳዮ ላይ ካደረገዉ የንግድ ስብሰባም አለማቀፋዊ ይዘት ያላቸዉ አዳዲስ ነጥቦች ተገኝተዋል።
በዮርዳኖስ ከተካሄደዉ ከዚህ ጉባኤያቸዉ በመቀጠልም የዛሬ ዓመት ስብሰባቸዉ በግብፅ ምድር እንደሚሆን ይጠበቃል።