በጥረት ቅሌት ጋር ፍርድ ቤት የቀረቡት የአቶ ምትኩ በየነ ጉዳይ | ኢትዮጵያ | DW | 04.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

በጥረት ቅሌት ጋር ፍርድ ቤት የቀረቡት የአቶ ምትኩ በየነ ጉዳይ

በጥረት ቅሌት ጋር ፍርድ ቤት የቀረቡት የአቶ ምትኩ በየነ ጉዳይ

በጥረት ኮርፖሬት አመራር ሆነው ሲሰሩ ባልተገባ መንገድ የኮርፖሬሽኑን ገንዘብ እንዲባክን አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩት አቶ ምትኩ በየነ ዛሬ ባህርዳርና አካባቢው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ጉዳያቸውን ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል። የ45 ዓመቱ አቶ ምትኩ በየነ ለፍርድ ቤቱ ስለራሳቸው ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:27

የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀዶላቸዋል

በዋግህምራ ዞን ከኤክስፐርትነት እስከ ዋና አስተዳዳሪነት መስራታቸውን፣ ባለትዳርና የ3 ልጆች አባት መሆናቸውን እንዲሁም ያለስራ ለ4 ወራት መቀመታቸውን ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል። የጥረት ኮርፖሬት ምክትል ስራ አስፈፃሚ ሆነው ሲሰሩ በ2005 ዓም በየዳ ለተባለ አክሲዮን ማህበር 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ያላግባብ የአክሲዮን ግዥ ከጥረት ኮርፖሬት እንዲከፈል አድርጓል ተብለው ለተጠረጠሩበት ጉዳይ ሲያብራሩም በወቅቱ የኔ ስራ አጠቃላይ ኩባንያዎችን ማስተባበር እንጂ በየዳ ሰስተነብል አክሲዮን ማህበርን በተመለከተ በዘርፍ ደረጃ እኔን አይመለተኝም ብለዋል። እንደዚሁም ጉዳዩ ተፈፀመ የተባለው በ2005 ዓም ሆኖ ሳላ የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የልማት ድርጅቶችን እንዲመለከት ህግ የወጣለት በ2007 ዓ ም በመሆኑ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለውም ብለዋል። ሌላው አቶ ምትኩ የተጠረጠሩበት ለባህርዳር ሞተርስና ለበየዳ ሰስተነብል አክሲዮን ማህበራት ከህግ ውጪ ከሌሎች አመራሮች ጋር በመሆን የ4 ነጥብ 65  ሚሊዮን ብር ብድር ፈቅደዋል የሚል ነው። አቶ ምትኩ ለዚህም ምላሽ ሰጥተዋል። ለፍርድ ቤቱ እንዳመለከቱት ድርጅቱ ለእህት ኩባንያዎች እንዲበድር የሚያስችል መመሪያ ቢኖረውም የተባለው ገንዘብ በብድር እንዲሰጥ አለማድረጋቸውንና በእርሳቸው ፊርማ የተሰጠ ብድር ከ200 ሺህ እንደማይበልጥ አመልክተዋል፡

በመሆኑም የተጠረጠርኩበት ጉዳይ እስር ቤት ሆኜ ጉዳዬን ለመከታተል የሚያስችል ባለመሆኑ ዋስትናዬ ተጠብቆ ውጪ ሆኜ ጉዳዬን ልከራከር የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። የአማራ ክልል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ በበኩሉ ተጠርጣሪው የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ኃላፊ ሆነው ሆነው በተጠረጠሩባቸው ጉዳዮች እጃቸው እንዳለበት ማስረጃዎች አሉኝ ብሏል። አንዱ ኩባንያ ለሌላ እህት ኩባንያ የሚያበድርበትን መመሪያ ማግኘት እንዳልቻለ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል። ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ወደ ኋላ ተመልሶ 2005ን ጉዳይ አይመለከትም የሚለውም ስህተት መሆኑን አቃቤ ህግ ጠቁሞ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ በየትኛውም ጊዜ የተፈጸመን የወንጀል ድርጊት ፋይል ከፍቶ መክሰስ ይችላል ብሏል አቃቤ ህግ።

ስለዚህ ግለሰቡ ከነበራቸው ኃላፊነት በቀሪ የምርመራ ሰራዎች ላይ ተፅእኖ ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጌዜ እንዲፈቀድለት አቃቤ ህግ ፍርድ ቤን ጠይቋል። አቶ ምትኩ አንዳመለከቱት የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራውን ማጠናቀቁን በብዙሐን መገናኛ ጭምር የገለፀ በመሆኑ፣እንዲሁም ከዚህ በፊት በተለያዩ የመንግስት ስራዎች ሲሰሩ በመልካም ስነ ምግባራቸው የሚታወቁ፣ የወንጀል ድርጊት ሰርተው የማያውቁና መልካም ስምና ዝና ያላቸው በመሆኑ አቃቤ ህግ የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ተገቢ ባለመሆኑ በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።የግየራ ቀኙን አስተያየት ከሰማ በኋላ የባህር ዳርና አካባበው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ተጠርጣሪው ለየካቲት 11/2011 ዓም እንዲቀርብ ወስኖ የእለት ውሎውን አጠናቅቋል።  ከጥረት ኮርፖሬት አክሲዮን ጋር ሥራን በማያመች አኳኋን በመምራት የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው  ባለፈው አርብ  ጉዳያቸው መታየት የጀመረው የባህር ዳር ሞተርስና የፓልማ አክሲዮን ማህበር ባለቤቶች ጉዳይ በሌላ ችሎት የታየ ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ በተመሳሳይ ለየካቲት 11/2011 ዓም እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ወሰኗል።

 

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic