በጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ቀጠናዊ ጉዳዮች ጎልተዋል | ኢትዮጵያ | DW | 20.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ቀጠናዊ ጉዳዮች ጎልተዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የመንግስታቸውን አቋም ለማስረዳት ደጋግመው ወደ መድረክ ብቅ ማለት ይዘዋል፡፡ ሁለት ሰአት የፈጀው የትናንቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ከዚህ ቀደም እንደነበሯቸው ማብራሪያዎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የተጫነው አልነበረም፡፡ ይልቅስ ሀገራዊና ቀጠናዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጎልተው ታይተዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:29

“በመርኅ ምክንያት የውጭ ኃይሎችን ማጣራት አንቀበልም”

ከሀገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮች ቀዳሚውን ቦታ የያዘው በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ተቀስቅሰው በነበሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባቀረበው የምርመራ ዘገባ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ለተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ማክሰኞ ባቀረበው ዘገባ በሀገሪቱ በነበሩ ተቃውሞዎች 699 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ በወቅቱ የጸጥታ አስከባሪዎች የወሰዱት እርምጃም “ተመጣጣኝ” እንደነበር ገልጿል፡፡ 

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በመንግስት የሚደገፈው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሳይሆን ገለልተኛ ወገን በሀገሪቱ የደረሱትን ጥሰቶች እንዲያጣሩ ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንቱ መግለጫቸው መንግስታቸው በ“መርህ ምክንያት” የውጭ ኃይሎችን ማጣራት እንደማይቀበል ገልጸዋል፡፡ የኮሚሽኑን ምርመራ “በገለልተኛነት” የተከናወነ እንደነበር ጠቅሰው ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡ የኮሚሽኑ ዘገባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል ጭምር ተቀባይነት እንዳገኘም ተናግረዋል፡፡ 

“ጄኔቫ ያለው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መንግስት ጽህፈት ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ከእኛው ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር ተከታታይ ውይይት ካደረጉ በኋላ እና የመጀመሪያ ሪፖርታቸውን ካዩ በኋላ ይሄ ሪፖርት ተገቢነት ያለው ስለሆነ ተቀባይነት አለው ብለው ወስደዋል፡፡ ሁለተኛውም ሪፖርት ይላክላቸዋል፡፡ የሚመለከታቸው አካላት በይፋ የሚላክላቸው እንደመሆኑ መጠን በእኛ ሀገር ሁኔታ በመርህ ደረጃ የሀገራችን የሰብዓዊ መብት ጥበቃ አቅም መጎልበት ስላለበት እና ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ስላለብን ምንም ጣልቃ ገብነት ሳይኖር እኛው ራሳችንን ይሄንን የማድረግ ችሎታችንን ማጠናከር ይገባናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ 

መቀመጫውን በጄኔቫ ያደረገው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ጥቅምት መጀመሪያ በኢትዮጵያ በተቃውሞ ወቅት ስለደረሱ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ገለልተኛ ማጣራት እንዲደረግ በይፋ ጠይቆ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ብሎ ለውጭ የመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የተባበሩት መንግስታትን ጥሪ ውድቅ አድርገዋል፡፡ በዚያው መግለጫቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአቅም እጥረት እንደሚታይበት ተናግረው የነበረ ቢሆንም በትናንቱ መግለጫቸው ግን ኮሚሽኑ “አሁን የተከሰተውን ችግር ለማጣራት አቅም አለው” ብለዋል፡፡ በኮሚሽኑ የምርመራ ዘገባ መሰረትም “የመንግስት አመራሮችና የጸጥታ አካላትን ጨምሮ ሁሉም በሂደቱ የተሳተፉ ሁሉ ያለአድልዎ ተጠያቂ“ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡  

በጋዜጣዊ መግለጫው ውስጥ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብበት የተስተዋለው ጉዳይ ግብጽ በቀጠናው እያደረገች ያለችው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወቅታዊ ግንኙነት የተመለከተ ነበር፡፡ “ግብጽ በጎረቤት ሀገራት ወታደራዊ ሰፈሮች ማቋቋሟ ለኢትዮጵያ ስጋት ይፈጥር እንደው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

“በእኛ እምነት የግብጽ መንግስት በርበራ ላይ ወታደራዊ ሰፈር አለው የሚለው ሀሰት ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ የለም፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ የሰሚ ሰሚ ገና ለገና ግብጽ እንደዚህ ልታደርግ ትችላለች በሚል ታሳቢ የሚፈበረኩ ወሬዎችን ተከትለን እኛም ራሳችን ፖሊሲ የምናወጣ ከሆነ አስቸጋሪ እና መጥፎ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እኛ ከማንም በላይ በሶማሌላንድ አካባቢ በቂ መረጃ አለን፡፡ ስለዚህ እኛ እስከምናውቀው ድረስ እንደዚህ ዓይነት መረጃ የለም ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ 

ግብጽ በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንደምትካሄድ ሲወራ እንደሚሰሙ ነገር ግን ከወሬ ያለፈ ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ ለጋዜጠኞቹ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ሁከት ይመሩ የነበሩ ኃይሎች ላይ ግብጽ እርምጃ ለመወውስድ መስማማቷን እና የተወሰኑ ሰዎችን እንዳሰሩ እንደነገሯቸውም ገልጸዋል፡፡ እንደ ግብጽ ሁሉ የባህረ ሰላጤው ሀገራት በአፍሪካ ቀንድና አካባቢው የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ለኢትዮጵያ አስጊ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡የባህረ ሰላጤው ሀገራት እንቅስቃሴ በየመን እና በሶሪያ ካሉ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ እንጂ በኢትዮጵያ ላይ ያተኮረ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡  

በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ “በገዢው ፓርቲ አባል ድርጅቶች መካከል እርስ በእርስ መጠራጠር ነበር” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ እውነትነቱን አረጋግጠዋል፡፡ ሆኖም ችግሩ አሁን መፈታቱን ጠቁመዋል፡፡ 

“በየብሔራዊ ድርጅቶች እና አመራሮች መካከል ያለው ጓዳዊ ግንኙነታችን ‘የሚፈለገው ጥንካሬ ላይ አልነበረም፤ የተለያዩ መጠራጠሮች ያሉበት ነው’ በሚል ገምግመን፤ ሂስ፣ ግለ ሂስ አድርገን እያንዳንዱ ሰው ራሱን ተችቷል፡፡ በአመራራቹ መካከል የነበረ ጥርጣሬ ነበር”  ሲሉ በአባል ፓርቲዎቹ መካከል የነበረውን ችግር አምነዋል፡፡  

ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ባሻገር ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎችም ሀገራት ለስራ ስለሚጓዙ ኢትዮጵያውያን፣ ስለ ውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በመንግስት እና በግል የጋራ ጥምረት በክልሎች ስለተጀመሩ ኢንቨስትመንቶች እና መሬት ወስደው ወደ ስራ ስለማይገቡ ባለሀብቶች ጉዳይ ጥያቄዎች ተነስተውላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ  

       

Audios and videos on the topic