በጎ አስተዳደር የታዳጊው ዓለም የልማት ዋስትና | ኤኮኖሚ | DW | 11.05.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

በጎ አስተዳደር የታዳጊው ዓለም የልማት ዋስትና

በጎ የአስተዳደር ዘይቤ ዛሬ በኤኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ ኋላ ቀር ሆኖ ለሚገኘው በተለይ ለታዳጊው ዓለም መሠረታዊ የልማት ዋስትና ነው። ይህ ሣይኖር ድህነትን ለመቀነስና የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል አይቻልም።

አፍሪቃና የልማት ዝግመቷ

አፍሪቃና የልማት ዝግመቷ

በዚህ በጀርመን የልማት ተራድኦ ተቋማት ይህን መሠረተ-ዓላማ ለተጠናከረ ትብብር ቅድመ-ግዴታ ያደርጋሉ። ከነዚሁ አንዱም ዓለምአቀፍ የፊናንስ አገልግሎት የሚሰጠው በአሕጽሮት KfW የተሰኘ የልማት ባንክ ይህንኑ መሠረት ያደረገ ዓመታዊ ዘገባውን ሰሞኑን አውጥቷል። የጀርመን ፌደራል መንግሥት የልማት ባንክና በግሉ ዘርፍ ላይ ያተኮረው የመዋዕለ-ነዋይና የልማት ድርጅት በአሕጽሮት DEG የታዳጊው ዓለም መንግሥታት ሃላፊነት የተመላበት የአሠራር ዘይቤ የኤኮኖሚና ማሕበራዊ ዕርዳታ ለመስጠት ወሣኝ ጉዳይ ነው ይላሉ። በሌላ አነጋገር የተግባር መርሃቸው በጎ አስተዳደር ባለበት ትብብሩ ይጠናከራል፤ በሌለበት ግን እንዲቆም ይደረጋል የሚል ነው።

የጀርመን ፌደራላዊ መንግሥት የልማት ባንክና የርሱው ተቀጥላ የፊናንስ ተቋም የታዳጊውን ዓለምና በሽግግር ላይ የሚገኙትን የማዕከላዊ-ምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ዕድገት ለማራመድ 2.6 ሚሊያርድ ኤውሮ ለመለገስ ባለፈው ዓመት ቃል ገብተዋል። የልማት ባንኩ በጀርመን ፌደራል መንግሥት ሥም ለምሳሌ በኤኮኖሚና ማሕባራዊ መዋቅራዊ ልማት ከታዳጊ አገሮች የፊናንስ ትብብር ያደርጋል። አባሪ ድርጅቱ DEG ደግሞ በኩባንያዎች መዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት ላይ የተሰማራ ነው።

የእስካሁኑ ልምድ እንደሚያሣየው በሁለቱም ዘርፎች የተሣካ ዕርምጃ ለማድረግ ተባባሪዎቹ አገሮች ውስጥ በጎ አስተዳደር መኖሩ ወሣኝ ቅድመ-ግዴታ ነው። ለዚህም ነው የልማት ባንኩ ባለፈው ዓመት ተግባሩ ላይ ባወጣው ዓመታዊ ዘገባ ለዚሁ ጉዳይ የተለየ ክብደት የሰጠው።

በጎ አስተዳደር ማለት ሃላፊነት የተመላበት የአስተዳደር ተግባር ማራመድ ማለት ነው። ሕዝብ በፖለቲካ ውሣኔ ላይ ተሳታፊ መሆኑና ግፍ እንዳይፈጸም ዋስትና መኖሩ፤ ሙስናን መታገሉና የግል ንብረት ዋስትናን ማረጋገጡም የዚያኑ ያህል ወሣኝኘት ይኖረዋል። እነዚህ ሁሉ ተጣምረው ለኤኮኖሚና ለማሕበራዊ ኑሮ ዕድገት፤ እንዲያም ሲል ዘላቂ ለሆነ የልማት ትብብር ስኬት ጠቃሚ አስተዋጽኦ አላቸው። ግን ለዚህ ለሚፈሰው ገንዘብ መንግሥት ተገቢውን ሁኔታ ካላመቻቸ የረባ ውጤት አይኖረውም የጀርመኑ ልማት ባንክ አመራር ዓባል ቮልፍጋንግ ክሮህ እንዳስረዱት።


በክሮህ አባባል ዕርዳታ የሚቀርብለት አንድ መንግሥት ያለውን መንከባከብና ማቆየት ካልቻለም ጥረቱ ሁሉ ከንቱ ነው። ለምሳሌ ያህል መንግሥት ለመምሕራን ደሞዝ በቂ በጀት ማቅረብ ወይም ደሞዝ መክፈል ካልቻለ ትም/ቤት ማነጽ ትርጉም አይኖረውም። በመሆኑም የልማት ትብብሩ እንዲሳካ ከተፈለገ አሁንም ቁልፍ የሆነው በጎ አስተዳደር መኖሩ ግድ ነው።

የጀርመን መንግሥት በልማት ፖሊሲው ለጉዳዩ ክብደት መስጠት ከጀመረ እርግጥ ዓመታት አልፈዋል። በመሆኑም በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ የሕዝብን ንብረት ሃላፊነት በተመላው መንፈስ የሚገለገለሉትን አገሮች ልማት ለማራመድ ጥረት ሲደረግ ነው የቆየው። ለልማት ትብብሩ ስኬት ተገቢው የፖለቲካና የኤኮኖሚ ሁኔታ መመቻቸቱ ትኩረት ይሰጠዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ፕሮዤዎችን በማቀዱና በማስፈጸሙ በኩል ልማቱ የሚመለከተውን ሕዝብ ማሳተፉ ነው። ይህ የጀርመን የመዋዕለ-ነዋይና የልማት ድርጅት DEG በተግባር ተሰማርቶ የሚገኝበትን የግል ኤኮኖሚ ዘርፍም ይጠቀልላል።
የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ ቪንፍሪድ ፖልተ እንደሚያስረዱት፤ “የግብር ሰብሳቢ ባለሥልጣን ተቋማት ግፍ፣ የሕጋዊ ዋስትና ጉድለትና የመንግሥታዊ ደምቦች የአፈጻጸም ድክመት፤ እነዚህ ሁሉ የሃቀኛ ኩባንያዎችን ተግባራት የሚያዳክሙ ናቸው።” ለምሳሌ መንግሥት ለሙያ ያልበቁ ሕጻናት የሚበዘብዙና ዝቅተኛውን የደሞዝ ክልል የማያከብሩ አሠሪዎችን ካልቀጣ ሃቀኞቹ ሕግ የሚያከብሩት ቀጣሪዎች ተጎጂዎቹ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ሙስናን፣ ብቃት አልባነትን፣ የዋጋ መናርንና በጠቅላላ ብልሹ አገልግሎትን ነው የሚያስከትለው። በእርግጥም ተገቢው አስተዳደር ባለበት አገር ነው ኩባንያዎች ደምቦችን ሊያከብሩ የሚችሉት። እንዲህ ካልሆነ ግብር በሥርዓት ይከፍላሉ ወይም ጉቦ ከመስጠት ይቆጠባሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።

ሕገ-ወጥ የገንዘብ ማጽዳት ድርጊትንና ሙስናን ማስወገጃ አንቀጽም የጀርመኑ የመዋዕለ-ነዋይና የልማት ድርጅት በታዳጊ አገሮች ኩባንያዎችን ለመመሥረትም ሆነ ለማስፋፋት የሚያደርጋቸው ውሎች ቋሚ አካል ነው። የሕጻናትን በሥራ መበዝበዝ፣ የዝቅተኛ የላብ ዋጋን አለመከበርና የተፈጥሮ ጥበቃ መስፈርችን መጠበቅ እንዲሁ ይጠቀልላል። መንግሥታዊው የጀርመን የልማት ባንክም የገንዘብ አቅርቦት ፍትሃዊ አስተዳደር መኖሩን መስፈርት ያደረገ ነው።
ከተባባሪዎቹ አገሮች ጋር የገንዘብ አቅርቦቱን በተመለከተ ቅድመ-ግዴታ የሆኑትን ሁኔታዎችና ግብ መሠረት አድርጎ ነው የሚዋዋለው። በጎ አስተዳደር ጨርሶ በሌለባቸው አገሮች ለምሳሌ በዚምላብዌ የጀርመን የልማት ባንክ ቮልፍጋንግ ክሮህ እንደሚሉት ትብብሩን ያቆማል። አሠራሩ በአንድ-ወጥ መስፈርት ቢራመድ ጠቃሚ እንደሚሆን ጨርሶ አያጠራጥርም። ይሁንና በታዳጊ አገሮች ዴሞክራሲን በማስፈኑ በኩል ሃብታም አገሮች በየጊዜው ሁለት መስፈርት ሲያራምዱ መታየታቸው በትክክል ገቢር መሆኑን አጠያያቂ የሚያደርግ ነው።

በልማት ትብብሩ አኳያ የጀርመንና የአፍሪቃ ግንኙነት በተለይ በሚቀጥለው ዓመት የተለየ ክብደት ይኖረዋል። ጊዜው ጀርመን በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትን ቀደምት መንግሥታት G-8 የተሰኘ ቡድን ሊቀ-መንበርነት የምትይዝበት፤ የአውሮፓ ሕብረትን ተፈራራቂ ርዕስነትም የምትረከብበት ነው። ሰሞኑን በዚህ በጀርመን ለሶሻል ዴሞክራቱ ፓርቲ የቀረበው በጎ አድራጎት ድርጅት ባደረገለት ግብዣ አገሪቱን የጎበኘ የደቡብ አፍሪቃ ልዑካን ቡድን በርሊን በአፍሪቃ ላይ ዓይኗን እንድታሳርፍ ደግሞ ደጋግሞ ነው ያሳሰበው።
የደቡብ አፍሪቃ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዚዝ ፓሃድ እንዳስረዱት ሁኔታው የጀርመንንና የአፍሪቃን ግንኙነት የበለጠ ክብደት ይሰጠዋል። “ጀርመን ትልቅ ሥልጣን የሚሰጥ ቦታ ነው የምትይዘው። በአውሮፓ ሕብረትና በ G-8 ቁንጮ ላይ መቀመጥ በዓለምአቀፉ የልማት ፖሊሲ መርሆዎች ላይ መወሰን መቻል ማለት ነው። እና ጀርመን በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ይበልጥ ፍቱን ሚና እንደሚኖራት ተሥፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

በልማት ጉዳይ የአፍሪቃ ልሣን እየሆነች የሄደችው የደቡብ አፍሪቃ ልዑካን በተለይ ያተኮሩት ድህነትን እስከ 2015 በከፊል ለመቀነስ በተያዘው የተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ዕቅድ ነው። አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ እርግጥ ግቡ በጊዜው የሚደረስበት መሆኑ ሲበዛ ያጠራጥራል። የአፍሪቃ ብሄራዊ ሸንጎ የ ANC ልዑካን የ G-8 መንግሥታት ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ስኮትላንድ-ግሌንኢግልስ ላይ የዕዳ ምህረት ለማድረግ የደረሱበትን ስምምነት ጥሩ ጅማሮ ነው ብለውታል።
በዕዳ ስረዛው ስምምነት የዓለም ባንክ የሚተወው ተመላሽ ብድር 37 ሚሊያርድ ዶላር የሚደርስ ነው። በስምምነቱ ከአርባ የሚበልጡ አገሮች ተጠቃሚዎች ሲሆኑ አብዛኞቹም የአፍሪቃ መንግሥታት ናቸው። ሆኖም የደቡብ አፍሪቃ የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር ማንዲሢ እምፓልዋ የዓለም ሕብረተሰብ በዚህ ስኬት ረክቶ መወሰን የለበትም ይላሉ። “አፍሪቃ በልማት ጥያቄ አሁንም ታላቋ የዓለም መፈተሻ ናት ብለን እናምናለን። በዚህች ክፍለ-ዓለም አንድ ፍቱን ዕርምጃ ካልወሰድን ከሚሌኒየም ግባችን ለመድረስ አንችልም። አፍሪቃ የዓለም ንግድ ድርሻዋ ያቆለቆለው ብቸኛዋ አካባቢም ናት። ለዚህም ነው የአፍሪቃ ጉዳይ በዓለም ሕብረተሰብ አጀንዳ ላይ ሰፍሮ እንዲቆይ ጀርመንን የምንጠይቀው” እምፖልዋ እንደተናገሩት።

በእርግጥም ከዕዳ ስረዛው ይልቅ ፍትሃዊ የንግድ ግንኙነት መስፈኑ ታላቅ ክብደት ሊሰጠው የሚገባ ነው። የአፍሪቃ አገሮች በዓለም ገበዮች ላይ ምርቶቻቸውን በተገቢው ዋጋ ለመሸጥ ዕድል ማግኘት አለባቸው። አለበለዚያ የልማት ዕርምጃ ይታያል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት አሁን ባለው መልክ ምርቶቻችውን መደጎም ከቀጠሉ ድሆቹ አገሮች ምንጊዜም የገበያ ተፎካካሪ ለመሆን አይበቁም። ሲጓተት የኖረው የዓለም ንግድ ድርጅት የድርድር ዙር እንግዲህ ፍትሃዊ ከሆነ ስምምነት መድረሱ ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ ነው የሚቀጥለው። ጀርመን በሚቀጥለው ዓመት የበለጸጉትን ቀደምት መንግሥታት ቡድንና የአውሮፓን ሕብረት አመራር ስትይዝ በዚህ በኩል ወሣኝ ተጽዕኖ ለማድረግ ትችል ይሆን? ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው።