1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግጭት ሥጋት ውስጥ የሚገኙት የአርባ ምንጭ ዙሪያ ቀበሌያት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 2016

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተከሰተው ግጭት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ መንደራቸው የመመለስ ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የወረዳው የፀጥታ ባለስልጣናት ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ ከመንደራቸው የተፈናቀሉት ከአስተዳደራዊ አደረጃጀት ጋር በተያያዘ በተቀሰቀሰ ግጭት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/4b2Nf
አርባ ምንጭ
አርባ ምንጭ ምስል DW

ግጭቱ የተነሳው ባልተጠበቀ ሁኔታ የመንግሥት የፀጥታ አባላት ድንገት ትኩስ በመክፈታቸው ነው

 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተከሰተው ግጭት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ መንደራቸው የመመለስ ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የወረዳው የፀጥታ ባለስልጣናት ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ ከመንደራቸው የተፈናቀሉት ከአስተዳደራዊ አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓርብ በተቀሰቀሰ ግጭት ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡ የአሁኑ ግጭት የተቀሰቀሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) በአካባቢው ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ አዝማሚያዎች መስተዋላቸውን ከሳምንት በፊት ለክልሉ መንግሥት መጠቆሙን ተከትሎ ነው ፡፡

ግጭቱ እንዴት ተቀሰቀሰ ?           

የአይን እማኞች አንደተናገሩት ግጭቱ ባለፈው ዓርብ የተከሰተው በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ኤልጎ እና ወዘቃ በተባሉ ቀበሌያት ውስጥ ነው ፡፡ በቀበሌያቱ ለግማሽ ቀን የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን የጠቀሱት የአይን እማኞቹ በዚህም ሰዎች መሞታቸውንና በተኩሱ የተደናገጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ የመንደሮቹ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ቀበሌያት መሸሻቸውን ተናግረዋል ፡፡

በተኩሱ አንድ የቅርብ ዘመዳቸው እንደተገደለባቸው ለዶቼ ቬለ የገለጹት ሁለት አስተያየት ሰጪዎች “ ግጭቱ የተነሳው ባልተጠበቀ ሁኔታ የመንግሥት የፀጥታ አባላት ድንገት ትኩስ በመክፈታቸው ነው ፡፡ በጥቃቱ ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል ፡፡ ከሟቾቹ መካከል አጎታችን ይገኙበታል ፡፡ በርካታ ሰዎችም በመደናገጥ ወደ ጫካ እና አጎራባች ቀበሌያት በመሸሽ ተሸሽገው ይገኛሉ “ ብለዋል ፡፡

የተከበቡት የፀጥታ አባላት

ዶቼ ቬለ ተከስቷል በተባለው ግጭት ዙሪያ ያነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ዙሪያ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ክበበው አዳል ግን “ የግጭቱ መነሻ ሌላ ነው “ ይላሉ ፡፡ እንደአዛዡ ገለጻ ግጭቱ የተካሄደው የታጠቁ ቡድኖች በአካባቢውየነበረውን የፀጥታ ሀይል በመክበብ ተኩስ በመክፈታቸውና የተወሰኑ አባላትን በማቁሰላቸው ነው ብለዋል ፡፡ በፀጥታ አባላቱ ላይ ተኩስ የጀመሩት ቡድኖች የነፍስ ወከፍ እና የቡድን  መሣሪያዎችን  የታጠቁ ናቸው ፡፡ እኛ ራሳችንን ለመከላከል የአጸፋ ተኩስ ነው ያደረግነው ፡፡ በጥቃቱም ሦስት አባሎቻችን ቆስለውብናል “ ብለዋል ፡፡

ከግጭቱ ጀርባ ያለው የአደረጃጀት ጥያቄ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) አሁን ከተከስተው የአርባምንጭ ግጭት ከመታየቱ አንድ ሳምንት አስቀድሞ በጉዳዩ ላይ ሪፖርት አውጥቷል ፡፡ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ከዘይሴ ብሄር የልዩ ወረዳ አስተዳደር ጥያቄ ጋር በተያያዘ ውጥረቶች አንደሚስተዋሉና የአካባቢው አስተዳደር አስቸኳይ የመፍትሄ ምላሾችን እንዲሰጥ ሲልም አሳስቦ ነበር ፡፡

የግጭቱ መንስኤ የዘይሴ ብሄር በልዩ ወረዳ ለመደራጀት ካቀረበው ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው ይባላል  ? በተኩስ ልውውጡ ከቆሰሉት የፀጥታ አባላት በተጨማሪ በሲቪል ነዋሪዎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለ ወይ ?  በሚል ዶቼ ቬለ የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ክበበው አዳልን ጠይቋል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሲመሠረት የልዩ ወረዳ መዋቅር ጥያቄ አብሮ አልተመለሰልንም የሚል እንቅስቃሴ እንዳለ እናውቃለን ያሉት የፖሊስ አዛዡ “ የልዩ ወረዳ ጥያቄን እኛ ሳንሆን ሌላ አካል ነው መልስ ሊሰጥ የሚችለው ፡፡ ነገር ግን ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲጠይቁ የከለከላቸው አካል የለም ፡፡ ከዚህ ውጭ በጥቃቱ ይህን ያህል ሰዎች ሞተዋል ለማለት በአኛ በኩል በተጨባጭ ያረጋገጥነው ነገር የለም “ ብለዋል ፡፡

ተፈናቃዮችን የመመለሱ ሂደት

አርባምንጭ ዙሪያወረዳው ግጭት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ወደ መንደራቸው የመመለስ ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የወረዳው የፀጥታ ባለስልጣናት እየገለጹ ይገኛሉ ፡፡ የተኩስ ልውውጡን ተከትሎ በርካታ ነዋሪዎች በታጣቂ ቡድኑ በመወናበድና ባልተገባ ሥጋት ወደ አጎራባች ቀበሌያት መሸሻቸውን ያረጋገጡት የፖሊስ አዛዡ ኮማንደር ክበበው አዳል “ አሁን ላይ የአገር ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን በመጠቀም ነዋሪዎችን ወደ መንደራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ፡፡ ብዙዎችም ጥሪውን ተቀብለው በመመለስ ላይ ናቸው “ ብለዋል ፡፡ ዶቼ ቬለ አሁን ላይ በወረዳው ኤልጎ እና  ወዘቃ ቀበሌያት ባደረገው ማጣራት በአካባቢው የሰላሙ ሁኔታ መሻሻሉንና መንደራቸው ጥለው ሸሽተው የነበሩ ነዋሪዎችም እየተመለሱ እንደሚገኙ ከነዋሪዎች አረጋግጧል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ