በግዳጅ የተመለሱ ቱኒዝያውያን እጣ ፈንታ | አፍሪቃ | DW | 11.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በግዳጅ የተመለሱ ቱኒዝያውያን እጣ ፈንታ

የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘላቸውን ፣ በተለይ ፣ከማግሬብ ሀገራት የመጡትን ስደተኞች ወደሀገራቸው የመመለሱን አሰራር የተመለከተው ክርክር አሁን ጀርመን ውስጥ እንዳዲስ ተጧጡፎዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:03

የቱኒዝያ ስደተኞች

ከጥቂት ወራት በፊት ሞሮኮን፣ አልጀርያን እና ቱኒዝያን የጎበኙት የጀርመን ሀገር አስተዳደር ሚንስትር ቶማስ ደ ሜዝየር የነዚህ ሀገራት መንግሥታት ጀርመን ውስጥ ካለሕጋዊ ሰነድ የሚኖሩትን ዜጎቻቸውን በመቀበሉ ረገድ እንዲተባበሩ ለማግባባት ሞክረዋል። ይሁንና፣ ከዚሁ ጉብንትም በኋላ የመመለሱ ሂደት ከቱኒዝያ በስተቀር፣ በጣም አዝጋሚ ሆኖ ነው የተገኘው። ባለፈው ሳምንት ከጀርመን ተመላሽ ቱኒዝያውያን ስደተኞችን ያሳፈረ አንድ አይሮፕላን ቱኒዝያ ገብቶዋል።
ከቱኒዝያ መዲና ቱኒስ በስተደቡብ 100 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የኤንፊድሀ አየር ማረፊያ አንዳንድ የክራይ አይሮፕላኖችን ብቻ ነው የሚያስተናግደው። የሚያርፉትን አይሮፕላኖች ዝርዝር በሚያሳየው ሰሌዳ ላይ ከላይፕሲግ የተነሳው አይሮፕላን ስም አልተፃፈም። ስለዚሁ አይሮፕላን የሚያውቁት በአየር ማረፊያው የተገኙት የጀበሊ ቤተሰብ አባላትን የመሳሰሉ እና የሲቭል ልብስ ያደረጉ ፖሊሶችም ብቻ ናቸው። ልጃቸውን መሀመድ አሊን ለመቀበል ነው ወደዚያ የሄዱት።


ከአይሮፕላኑ የወረዱ ወጣት ወንዶች ወደእንግዳ መቀበያው እንደደረሱ ፣ እናት ጀቢላ ልጃቸውን መሀመድ ሰላምታ ከሰጡ በኋላ የቱኒዝያ ፖሊስ በወጣቶቹ አንፃር የተመሰረተ ክስ መኖሩን ለማጣራት ወደምርመራ ክፍል ወስደዋቸዋል። ምርመራው እስኪያበቃ ድረስ በመጠበቅ ላይ የነበሩት የመሀመድ አባት ጀበሊ ልጃቸው መሀመድ ከአብዮቱ በኋላ መጀመሪያ ወደ ኢጣልያ ከሄደ በኋላ በስዊትዘርላንድ አድርጎ ጀርመን እንደገባ እና እንደሚመለስ የሰሙት የዚያን ዕለት ጥዋት እንደነበር ገልጸዋል።
« ዛሬ ጥዋት ነበር ስልክ ደውሎ ወደ ቱኒዝያ በግዳጅ እንደሚመለስ የነገረን። እኛም ጉዳዩ ከሚመለከተው የሀገራችን መንግሥት ጋር ተነጋገርን፣ እዚህ በምንም ዓይነት ወንጀል፣ በስርቆት ሆነ በሌላ ወንጀል እንደማይፈለግ፣ ንፁሕ መሆኑን ሰማን። አሁን ይኽው እየጠበቅነው ነው። »
ከምርመራው በኋላ መሀመድ ነፃ ተብሏል፣ የቱኒዝያ መንግሥት መሀመድ ከአምስት ዓመት በፊት ከሀገሩ በሕገ ወጥ መንገድ የወጣበትን ድርጊት በሕግ ሊከታተለው አልፈለገም፣ ምንም እንኳን ይህ ጥፋት ከ15 ቀን እስከ ስድስት ወር ሊያሳስር ቢችልም።የተገን መጠያቂያ ማመልከቻው ተቀባይነት ያላገኘለት መሀመድ በላይፕሲኽ ከተማ //// ያገኘውን ስራ እየሰራ ነበር የኖረው። ከአንዲት የፖርቱጋል ዜጋ ጋር የተጋባው መሀመድ አሊ ቀደም ሲልም ከአንዲት ጀርመናዊት አንዲት ሴት ልጅ ወልዶዋል። መሀመድ በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ ላጭር ጊዜ እስር ቤት ከቆየ በኋላ በነፃ ተለቆ ይኸው አሁን ሳያስበው ወደ ቱኒዝያ እንዲመለስ መገደዱን ይናገራል።


« ወደ ቱኒዝያ በግዳጅ እንደምመለስ ማንም የነገረኝ የለም። ከእስር ቤት በነፃ ከተለቅቅሁ በኋላ፣ ልጅ ስላለኝ ወደ ሀገሬ በግዳጅ ላልመለስ እንደምችል ነግረውኝ ነበር፣ በኋላ ግን ፣ ልጅ እንዳለኝ ብነግራቸውም፣ ይኸው በግዳጅ መልሰውኛል።
በቱኒስ ማህበራዊ ችግር ጎልቶ በሚታይበት «ሲቴ ኤዙኡር» ሰፈር የኖረው እና ወደ ውጭ ሀገር ሲሰደድ 16 ዓመቱ የነበረው መሀመድ ያጠናቀቀው ትምህርትም ሆነ ሙያ ስልጠና የለውም። እና አሁን ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጥያቄ እሱን እና ቤተሰቦቹን እንደሚያሳስብ አባቱ ጀቢል ይናገራሉ።
« ሶስት ወንዶች እና ሴቶች ልጆች አሉን። ልክ ጓደኞቹ እንዳደረጉት ወደ ውጭ ሀገር የሄደው እሱ ብቻ ነው። እንዴት እንደሆነ፣ ታውቀዋለህ። ሁሌ በመኪና ይመጡ እና ጀርመን ወይም ኢጣልያ ብዙ ገንዘብ እንዳለ ነው የሚናገሩት። መሀመድም ይህን ኑሮ እና ዓለምን ማየት ፈለገ። »
ሶስቱ ልጆቻቸው ስራ አጥ ናቸው፣ አሁን ደግሞ የ21 ዓመቱ መሀመድ ተጨመረበት። ወደ «ሲቴ ኤዙኡር» ሰፈር በመመለስ ከወላጆቹ ጋር እየኖረ ስለወደፊት እጣ ፈንታው ማሰብ መጀመር አለበት። ከቱኒዝያ መንግሥት ርዳታ ይገኛል ብሎ ተስፋ አያደርግም፣ ምክንያቱም፣ ብዙ እንደሱ ስራ አጦች አሉ፣ ከዚህ በተረፈም፣ ከሀብታሟ አውሮጳ ካለ ገንዘብ እና መኪና ለሚመጡ ያልተሳካላቸው ተመላሽ ቱኒዝያውያን የሚጨነቅ የለም። ስለወደፊቱ እጣው በወቅቱ ምንም እቅድ የሌለው መሀመድ አንድ ሀሳብ ብቻ ነው ያለው። ይኸውም፣
« ልጄ በዚያ ስለምትኖር ወደዚያ መመለስ እፈልጋለሁ። »

የንስ ቦርኸርት/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic