በግብፅ የቀጠለዉ የኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ጥያቄ | ኢትዮጵያ | DW | 28.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በግብፅ የቀጠለዉ የኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ጥያቄ

ግብፅ ካይሮ ለሚገኘዉ ለተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን«UNHCR» የጥገኝነት ማመልከቻ አቅርበዉ በጅምላ እገዳ ተጥሎብናል ያሉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች አሁንም እንግልት ላይ መሆናቸዉን እየገለፁ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:58

ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በግብፅ

በተለይ በካይሮ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች በ«UNHCR» ጽ/ቤት ፊት ለፊት የተቃዉሞ ሰልፍ ካካሄዱና ሦስት ሰዎች ራሳቸዉን በእሳት ካቃጠሉ በኋላ፣ በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ በሰበቡ አንዷ የኦሮሞ ተወላጅ ከዚህ ዓለም መሞታቸው ተመልክቶአል።

ለተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን«UNHCR» የጥገኝነት ማመከቻ አቅርበን የጅምላ እገዳ ተጣለብን ያሉና ባለፈዉ ሳምንት በካይሮ ዋና ፅሕፈት ቤት ፊት ለፊት የተቃዉሞ ሰልፍ በማድረግ ራሳቸዉን በእሳት ከለኮሱ በኋላ አንዲት የሁለት ልጆች እናት ቃጠሎዉ ባስከተለባቸዉ ከፍተኛ አደጋ ሕይወታቸዉን አጥተዋል። በካይሮ የኦሮሞ ማኅበረሰብ አስተባባሪ አቶ ያዘዉ ከበበ እንደገለፁት ፣ ከ«UNHCR» ፈቃድ ባለማግነታቸው እስካሁን የሟችን አስክሬን ከሆስፒታል ማዉጣት አልቻሉም።
ስለተከሰተዉ ሁኔታ በጣም አዝነናል ያሉት በካይሮ የ«UNHCR» የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ታሪክ አርጋዝ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት ጉዳዩን በአስቸኳይ ለማስፈፀም እየሰሩ ነዉ።

« ከ UNHCR ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ ዉጭ የተካሄደውን ተቃውሞ እና አደጋን ተከትሎ በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ላይ ተገን ጠያቂዎች ላጋጠማቸው ችግር UNHCR ኃዘኑን ይገልጻል። UNHCR» ከመንግሥትና ከሆስፒታሉ እንዲሁም ከተገን ጠያቂ ማኅበረሰብ ጋር በመሆን ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል ላይ ነን። ስለዚህ ጉዳዩ እንዲህ ነዉ ብዩ አሁን መናገር ባልችልም ፣ በርግጠኝነት በጣም በቅርቡ መልስ ይኖረናል።»
በኦሮሞ ተገን ጠያቂዎች ላይ ካይሮ የሚገኘዉ ድርጅት የጅምላ እገዳ ተጣለ ስለመባሉ የ«UNHCR» የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ታሪክ አርጋዝ በሰጡት መልስ« ተገን ጠያቂዎቹ መሥራያ ቤቱ ሆነ ብሎ እገዳ ጣለባቸዉ የሚለዉ ቅሬታ እዉነት እንዳልሆነ መግለፅ እወዳለሁ። ምክንያቱም UNHCR ተገን የሚሰጠዉም ሆነ የሚነፍገዉ አንድ ቡድንን ወይም የአንድ አገር ዜጋን ለይቶ ወይም ትኩረት አድርጎ አይደለም። መስርያ ቤታችን የተገን ጠያቂዎችን ማመልከቻ የሚገመግመዉ የግለሰቡን ምክንያትና ሁኔታዎች አይቶና የ «UNHCR»ን ሕግና ደንብን መሰረት አድርጎ ነዉ። በጅምላ በቡድን እገዳ አይጥልም።» ቀብሩን በኢትዮጵያ ለማስፈፀምም ሆነ፣ ካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲም ሊረዳ አልቻለም ሲሉ በካይሮ የኦሮሞ ማኅበረሰብ አስተባባሪ አቶ ያዘዉ ከበበ ተናግረዋል።
አንድ ተገን ጠያቂ በ «UNHCR» እገዳን ከተቀበለ ዳግም ይግባኝ ማለት ይችላል ያሉት የ«UNHCR» የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ታሪክ አርጋዝ በመቀጠል « አንድ የተገን ጠያቂ ማመልከቻ በ«UNHCR» ተቀባይነት ካገኘ የተገን ጥያቄዉ ሙሉ በሙሉ ተሟልቶአል ማለት ነዉ። ግን የ UNHCRን መመለኪያ ማሟላት ያልቻለና እገዳ ያረፈበት ግለሰብ ፤ የይግባኝ ማመልከቻ በማስገባት ጥያቄዉን እንደገና ማቅረብ ይችላል። »
በግብፅ ካይሮ የኢትዮጵያ ኤምባሲን አስተያየት ጠይቀን፣ መልሳችሁ ደዉሉ በተባልነዉ መሠረት ብንደውል መልስ ባለማግኘታችን አስተያየቱን ማካተት አልቻልንም።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic