በግብፅ- እሥራኤል ድንበር፣ የኤርትራውያን ፈላስያን መገደልና የ HRW ቅሬታ፤ | ኢትዮጵያ | DW | 17.08.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

በግብፅ- እሥራኤል ድንበር፣ የኤርትራውያን ፈላስያን መገደልና የ HRW ቅሬታ፤

የዜና አውታሮች ባለፈው ሳምንት ማለቂያ ላይ እንደዘገቡት፤ ዓርብ፣ ከቀትር በኋላ፤ በግብጽና እሥራኤል ድንበር ላይ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ፣ ሰዎችን ካገር -አገር በሚያሻግሩ ቡድኖችና በፈላስያን መካከል ፣ ተካሄደ በተባለ የተኩስ ልውውጥ 4 ኤርትራውያን ተገድለዋል።

በግብፅ- እሥራኤል ድንበር፣ የኤርትራውያን ፈላስያን መገደልና የ HRW ቅሬታ፤

በዚያው ዕለት ፣ የግብፅ ድንበር ጠባቂ ወታደሮችም በተጨማሪ 2 ኤርትራውያንን ከገደሉ ወዲህ፤ ከቆሰሉት መካከል አንዲት የኤርትራ ተወላጅ የሆነች ሴት ከትናንት በስቲያ ህይወታቸው አልፏል። ባለፈው ዓርብ በተወሰደው የኃይል እርምጃ ሳቢያ የሞቱት አኀዝ 7 ደርሷል።

በአፍሪቃውያን ፈላስያን ላይ፤ የሚወሰደውን የጭካኔ እርምጃ አጥብቆ ሲቃወም የቆየውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪውን ድርጅት(HRW) የሰብአዊ መብት ይዞታ ተመራማሪ «ሚስ» ሄባ ሞራየፍን በማነጋገር ተክሌ የኋላ የሚከተለውን ዘገባ

አጠናቅሯል።

ወደ ሌላ አገር ብናልፍ፣ እልፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ አያሌ አፍሪቃውያን ፤ ወደ አውሮፓ፤ መካከለኛው ምሥራቅና የፋርስ ባህረሰላጤ አካባቢ የዐረብ አገሮች ለመግባት ጉዞ እየጀመሩ በመሃሉ፤ ባህር ውስጥ የሰጠሙ፤ በባህር ኃይል ወታደሮች ተገደው ወደ አፍሪቃ የተመለሱ እንዲሁም በድንበር ጠባቂ ወታደሮች የተገደሉ ጥቂቶች አይደሉም። የሚገርመው፤ እጅግ አደገኛ ሁኔታ እንደሚያጋጥም በተጨባጭ ሁኔታ እየታዬና እየተነገረም፤ ወደ ሌሎች አገሮች ለመሄድ የሚነሳሱት ፈላስያን ቁጥር ሊገታ አለመቻሉ ነው ። 250 ኪሎሜትር ርዝማኔ ባለው የግብጽና እሥራኤል ወሰን ለህገ-ወጥ ድንበር አሻጋሪዎች፤ ብዙ ገንዘብ እየከፈሉ የሲናንና ነጌቭን በረሃ አቋርጠው ፣ በርሼቫ፤ ኢየሩሳሌምም ሆነ ቴልአቪብ ለመድረስ የሚያልሙ ሁሉ ህልማቸው እውን ሳይሆን፤ ቅዠት፤ ህልፈተ-ህይወት (ባጭር መቀጨት) እምደሚሆን እየታየ ነው። ካለፈው ጥር አንስቶ እስካሁን 29 አፍሪቃውያን ፈላስያን፤ በአመዛኙ ኤርትራውያንና ሱዳናውያን በግብፅ ድንበር ጠባቂዎች ከሰሞኑ ደግሞ በድንበር አሾላኪዎችጭምር ተገድለዋል ተብሏል። ሄባ ሞራዬፍ--

«ኤርትራውያን ፈላስያን ፤ ከድንበር አሻጋሪዎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የተገደሉ ሲሆን፤ ሌሎች 2 በግብፅ ወሰን ጠባቂዎች ጥይት ህይወታቸው አልፏል። ይህ ሁሉ ፤ በሲና ስለሚካሄደው ያለንን ግምትና ግንዛቤ አልለወጠውም። ፈላስያንን ከድንበር-ድንበር የሚያሸጋግሩ ቡድኖች፤ ፈላስያኑን በየጊዜው የሲናን ድንበር እንዲያልፉ ያደርጋሉ፤ እናም በግብፅ ድንበር ጠባቂዎች ግድያ ይፈጸማል። እዚህ ላይ ማውሳት የሚገባን ዋና ጉዳይ፤ አሁን በቅርቡ ስለሆነው ነገር ተጨማሪ ዝርዝር ማብራሪያ ያላጋኘን መሆባችን ነው። ለተገደሉት ሁሉ በትክክል ማነው ኀላፊው አጣርተን ማወቅ አልቻልንም።»

በግብፅና በሊቢያ የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት (HRW)የሰብአዊ መብት ይዞታ ተመራማሪ ሄባ ሞራየፍ፣ ድርጅታቸው በዚያ አካባቢ የፈላስያንን ሰቆቃ በተመለከተ እስካሁን እያሰማ ያለውን አቤቱታ አስመልክተው ሲናገሩ--

«እኛ ግብፅ ወሰኗን የመጠበቅ መብት ያላት መሆኑን እናውቃለን። በሲና ፀጥታ የማስከበር ኀላፊነት እንዳለባትም እንቀበላለን። ነገር ግን፤ ግለሰቦችን ተኮሶ መግደል ትክክለኛ እርምጃ አይደለም ምክንያቱም ተግባራዊ መሆን ያለበት መደበኛው የአሠራር ደንብ ፤ ነፍስ ሊያጠፋ በሚችል ኃይል መጠቀም ህጋዊነት የሚኖረው ፤ የራስን ህይወት መጠበቅ የማያስችል ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ ነው። ይህም ማለት፤ ወሰን ጠባቂዎች ጦር መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ ሲፋለማቸው፤ ሲያነጣጥርባቸው፤ ነው። ይህ ሲሆን ነው ፤ በኃይል መጠቀም፣ ለእነርሱ ተገቢነት ያለው ነው የሚባለው። ነገር ግን አብዛኞቹ ሰሞኑን ከተፈጸመው ድርጊት በስተቀር፤ ይህም ቢሆን ፍጹም የተረጋገጠ ማባራሪያ አልተገኘበትም---፣ ማለት--ማን ታጥቆ ነበር? ያልታጠቀውስ ማን ነበር? አይታወቅም። ነገር ግን ብዙኀኑ ፈላስያን የማይታጠቁና ለወሰን ጠባቂዎቹም የማያሠጉ እንደነበሩ የታወቀ ነው። »

ግብፅ፤ በህገ ወጥ ድንበር ተሻጋሪዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰደ የጀመረች፣ እ ጎ ኣ, በ 2007 ዓ ም፤ ፕሬዚዳንቷ ሆስኒ ሙባረክና የያኔው የአሥራኤል ጠ/ሚንስትር ኤሁድ ኦልመርት፤ አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህ መሆኑ ይነገራል። ይሁንና ግብፅ ያልታጠቁ ፈላስያንን ከመግደል እንድትቆጠብ ሲያሳስብ የቆየው HRW አሁን ምን ያደርጋል?

«የያዝነው አቋም(የቆምንለት ዋና ዓላማ፤--) ውሳኔው ፤ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎችን ከሚቆጣጠረውከግብፅ የሀገር አስተዳደር ሚንስቴር መምጣት እንዳለበት እናምናለን። እናም፤ የመርኅ ለውጥ እንዲደረግ እንጠይቃለን። መመሪያውም፤ ወደ አየር መተኮስና በፈላስያኑ ላይ አነጣጥሮ መግደል መሆን የለበትም። ህገ-ወጥ እርምጃ ነውና! የአኛ ተግባር፤ ግብፅ ፤ ዓለማ-አቀፍ ግዴታዎቿን እንድታከብር ማስታወስ ነው። በዚህ መንገድ ግፊት እንዲደረግባት መጣርም ይሆናል።»

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ