1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግብርና ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶች አቤቱታ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 3 2016

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በግብርና ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶች የክልሉ የሰላም ሁኔታ በፈጠረው ጫና ምርት ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሮ ለመሸጥ አመቻላቸውን አመለከቱ። የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ ችግሮች ቢኖሩም ምርቱ ወደ ገበያ ማዕከል ደርሶ መሸጡን ይናገራል።

https://p.dw.com/p/4i756
Äthiopien  West Gondar und Metema
በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢ ከሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር ይዋሰናል። ፎቶ ከማኅደር፤ ምዕራብ ጎንደር መተማ ምስል DW/Alemenew Mekonnen

ምዕራብ ጎንደር

በአማራ ክልል የምዕራብ ጎንደርዞን ለግብርና ልማት የሚሆኑ ሰፊና ለም መሬት ካላቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በመሆን ይታወቃል። በዚህም ምክንያት በርካታ ባለሀብቶች በግብርና ልማት በዚህ አካባቢ ተሰማርተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ምርታቸውን አውጥተው መሸጥ ባለመቻላቸው ብዙም ውጤታማ እንዳልሆኑ አንዳንድ ባለሀብቶች ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።

አንዳንዶቹ እንደውም እንደልብ ተንቀሳቅሶ መሸጥ ባለመቻሉ የሠራተኛ ደመወዝና የመንግሥት ግብር ለመክፈል ሲሉ ምርታቸውን በዝቅተኛ ዋጋ እስከመሸጥ መድረሳቸውን አመልክተዋል። መንገድ በመዘጋቱ የተፈጠረን አንድ ክስተትን በተመለከተ ሲናገሩም፤

«ምርትህን ማቆየት አትችልም፣ በርካሽ ትሸጣለህ እንጂ፣ ለሠራተኛ፣ ለመሬት ግብር፣ በየመንገዱ እያስቆመ የተለያየ አካል ገንዘብ ይጠይቅሀል። አሁን ጥጥ በኪሎ 50 ብር ገብቷል እኛ ግን 22 እና 23 ብር ነው ከስረን የሸጥነ። መንገድ ችግር ነው፣ ሸኸዲ ላይ ሽንኩረት የጫኑ 30 መኪናዎች እንዲቆሙ ተደርጎ ነበር ። መንገዱ በመዘጋቱ ሽንኩርቱ ተበላሸ፣ አንድ መኪና 400 ኩንታል ይጭናል፣ አንዱ ኩንታል 60 ብር ቢያወጣ የደረሰውን ጉዳት ማወቅ ትችላለህ።» ነው ያሉት።

አጠቃላይ ያለው ሁኔታ በግብርና ሥራ የተሠማራውን አርሶ አደር ባለሀብት አላንቀሳቅስ ብሎታል ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ባለሀብት ምርታቸውን እንደልብ ማንቀሳቀስ ባለመቻላቸው አንዲ ሺህ ኩንታል የሚደርስ አኩሪ አተር ለብልሽት ተጋልጧል ይላሉ።

«የጥጥና የአኩሪ አተር ምርቱ የሞተ ነው፣ የመንገድ መዘጋጋቱ ሲከፈት ሲዘጋ፣ ወጪውም ከባድ ነው፣ በእጥፍ ነው መንገድ ላይ ገንዘብ የምንከፍለው። ግብር ያኛውም ይሔኛውም ይቀበለናል (ታጣቂውም መንግሥትም ለማለት ነው)። የጥጥ ምርት እንደምንም በቅናሽ ቢሆንም ተሸጧል። አኩሪ አተር ግን አንድ ሺህ ኩንታል የሚሆን ገበያ መድረስ ሳይችል ለብልሽት ተዳርጓል።»

የባንክ አገልግሎት ችግርን በተመለከተ በአካባቢው የሚገኘው የፀደይ ባንክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ዓለምነህ የግብርና ባለሀብቶቹ ብድር መክፈል ባለመቻላቸው ብድር መስጠት ማቆማቸውን ነው የተናገሩት። በግርብርና ልማት የተሰማሩት ባለሃብቶች አሁን ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት ብድር መመለስ እንዳልቻሉ በማመልከትም፤ በዘመኑ መመለስ የነበረበት ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር በዚህ ምክንያት ለባንኩ እንዳልተመለሰም ገልጠዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ቢሆነኝ ግን ምንም እንኳ ችግሮች ቢኖሩም ምርቱ ወደ ገበያ ማዕከል መድረሱን ነው የተናገሩት። በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢ ከሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር ይዋሰናል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ