በግሪክ የቁጠባ መርሐግብር ላይ የሬፈረንደም ዕቅድ | ዓለም | DW | 01.11.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

በግሪክ የቁጠባ መርሐግብር ላይ የሬፈረንደም ዕቅድ

የግሪክ ሕዝብ የሀገሩ መንግሥት ባወጣው አዲስ የቁጠባ መርሐግብር እና የአውሮጳ ህብረት ባለፈው ሳምንት በሰጠው ርዳታ ላይ በሬፈረንደም እንደሚወስን ተገለጸ።

default

የግሪክ ጠቅላይ ሚንስትር ጊዮርጊስ ፓፓንድሬዎ ትናንት ለሶሻል ዴሞክራቱ የፓስኮ ፓርቲያቸው ሳይታሰብ እንዳስታወቁት፡ በዚሁ ጥያቄ ላይ በሚቀጥለው አውሮጳዊ ዓመት ውጤቱ አሳሪ የሚሆን ህዝበ ውሳኔ ይካሄዳል። የዚሁ ርምጃ አስፈላጊነትን ሲያስረዱም እንዲህ ነበር ያሉት።

« ይህ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችን ዓቢይ መገለጫ ነው። ዜጎች በዚሁ ውሳኔአቸው ሀገር ወዳድነታቸውን ሊያስመሰክሩ ይችላሉ። የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ ሕዝቡ ነው። ውሳኔ የሚሰጠው በግለሰብ ወይም በፓርቲ ላይ ሳይሆን በሀገራችን ዕጣ ፈንታ እና በምትከተለው ፖሊሲ ላይ ነው። »

ፓፓንድሬዎ ከዚህ በተጨማሪም የፊታችን ዓርብ በምክር ቤት እአአ እስከ 2013 ዓም ድረስ ለሚቆየው የሥልጣን ዘመናቸው የምክር ቤት እንደራሴዎችን ድጋፍ የሚያረጋግጡበት የአመኔታ መስጫ ድምፅ እንደሚጠይቁም አመልክተዋል። ሀያ ሰባቱ የአውሮጳ ህብረት ርዕሳነ ብሔር እና መራሕያነ መንግሥት ግሪክን ከክስረት ለመጠበቅ ሲሉ ነበር ከብዙ ክርክር በኋላ የግሪክ ዕዳ በሀምሳ ከመቶ የሚሰረዝበትን ዕቅድ ጭምር ያጠቃለለ የርዳታ ፓኬት ያፀደቁት። ግሪክ ውስጥ ከጥቂት ጊዜ በፊት የወጣ የሕዝብ አስተያየት መመዘኛ መዘርዝር እንደሚያሳየው፡ ስድሣ ከመቶ የሚሆነው የግሪክ ሕዝብ ጠቅላይ ሚንስትር ፓፓንድሬዎ ያወጡትን የቁጠባ መርሐግብር እና የአውሮጷ ህብረት ጉባዔ ያሳለፈውን ውሳኔ አይቀበለውም። የግሪክ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጠቅላይ ሚንስትር ፓፓንድሬዎን የረሬፈረንደም ውሳኔ አጣጥለውታል። ውሳኔው አውሮጳውያኑን መሪዎችም አስገርሞዋል።

አርያም ተክሌ