በግሪክ እና በፈረንሳይ የተካሄዱት ምርጫዎች | ዓለም | DW | 19.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ዓለም

በግሪክ እና በፈረንሳይ የተካሄዱት ምርጫዎች

ባለፈው እሁድ የተካሄደው የግሪክ የምክር ቤት ምርጫ ውጤት በግሪክ የወደፊት እጣ ላይ ያንዣበበውን ስጋት በእጅጉ ቀንሶታል ። በፈረንሳዩ የምክር ቤት ምርጫ ደግሞ ሶሻሊስቶች የበላይነትን ተቀዳጅተዋል ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ።

ባለፈው እሁድ የተካሄደው የግሪክ የምክር ቤት ምርጫ ውጤት በግሪክ የወደፊት እጣ ላይ ያንዣበበውን ስጋት በእጅጉ ቀንሶታል ። በፈረንሳዩ የምክር ቤት ምርጫ ደግሞ ሶሻሊስቶች የበላይነትን ተቀዳጅተዋል ። የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው ። የአሁኑ የግሪክ ምርጫ የተጠራው ከስድስት ሳምንት በፊት በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር የምክር ቤት ምርጫ በተገኘው ውጤት አሸናፊዎቹ ፓርቲዎች መንግሥት መመስረት የሚያስችል በቂ ድምፅ ባለማግኘታቸው ነበር ። በሚያራምዱት የቁጠባ መርኀ ግብር ሳቢያ ህዝብ ድምጹን የነፈገው አዲስ ዲሞክራሲ የተሰኘው ወግ አጥባቂ ፓርቲና የሶሻል ዲሞክራቱ ፓርቲ ፓሶክ ፣ በዚሁ ምርጫ ብዙ ድምፅ ካገኙት የግራ ክንፍ ተቃዋሚዎች ጋር ተጣምረው መንግሥት የመመሥረት ሙከራ  አድርገው ነበር ። ይሁንና ከተቃዋሚዎች ጋራ ያካሄዱት የመንግሥት ምሥረታ ድርድር ሳይሳካ ቀርቶ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ለመጠራት በቃ ። በዚሁ ሰኔ 10,2004 ዓ ም በተካሄደው ምርጫ ግን መፍቅሬ አውሮፓ ህብረት የሆነው አዲስ ዲሞክራሲ ድል ቀንቶታል ። ይኽው ፓርቲ በአሁኑ ምርጫ ያገኘው ድምፅ 29.6 ከመቶ ሲሆን የቁጠባ እርምጃ ተቃዋሚው የግራዎቹ ሲሬዛ ደግሞ 26.9 በመቶ ድምፅ ነው ያሸነፈው ። በግሪክ የምርጫ ስርዓት ትልቁን ድርሻ የያዘው ፓርቲ

ተጨማሪ 50 የምክር ቤት መቀመጫዎችን ያገኛል ። ይህ ሁሉ ተደማምሮ አዲስ ዲሞክራሲ ከግሪክ 300 የምክር ቤት መቀመጫዎች 129 ኙን ሲይዝ ከኒውዲሞክራሲ ጋር ሊጣመር የሚችለው ሶሻል ዲሞክራቱ ፓሶክ ደግሞ 13.3 በመቶ ድምፅ አሸንፎ በ 3ተ ኛነት 33 የምክር ቤት መቀመጫዎችን አግኝቷል ። የግራው ሲሪዛ 71 መቀመጫ ነው ያሸነፈው ። የእሁድ ምርጫ ውጤት የግሪክ ጉዳይ ናላቸውን ሲያዞር ለሰነበተው ጀርመንን ለመሳሰሉ የዩሮ ዞን ተጠቃሚ ሃገራት ብቻ ሳይሆን ለአውሮፓ ህብረት በአጠቃላይም ለባለፀጋዎቹ ሃገራት ትልቅ እፎይታ ነው የሰጠው ። የአሸናፊው የመሃል ቀኙ የአዲስ ዲሞክራሲ ፓርቲ መሪ አንቶንዮስ ሳማራስ ውጤቱ ይፋ እንደተደረገ በሰጡት መግለጫ የምርጫው ውጤት የግሪክ ህዝብ ከዩሮ አባልነት መውጣት እንደማይፈልግ ማረጋገጫ መሆኑን ነው ያሳወቁት

 « ዛሬ የግሪክ ህዝብ ፣ አገሩ ፣ ከዩውሮ ጋር እንደተተቆራኘች የተቀዋሚዎቹ ሃገራት ማኅበረተኛ እንደሆነች እንድትቀጥል፤ ወስኗል ። የገባችውን ቃል እንድታከብርና እድገቷን እንድታንቀሳቅስም እንዲሁ! ይህ የመላዋ አውሮፓ ድል ነው ። »

ከብዙ አቅጣጫ ጫናው የበረታበት የግሪክ ህዝብ ባለፈው ምርጫ  ቁጠባን ለሚቃወመው ለግራዎቹ  የሲሪዛ ፓርቲ ብዙ ድምፅ በመስጠቱ አሁንም ያ ሊደገም ይችላል የሚል ስጋት ነበር ። ግሪክን ከአውሮፓ ህብረት የቁጠባ እርምጃ አላቅቃለሁ በማለት በአጭር ጊዜ ዝናው የናኘው የግራው የሲሪዛ መሪ አሌክሲስ ትሲፕራስ ተሳክቶላቸው ቢሆን ኖሮ እንደርሳቸው አባባል ግሪክን ለመታደግ የአውሮፓ ህብረት የተስማማበት ውል ሰኞ ታሪክ ሆኖ ነበር ። ይህ ፓርቲ ከቀናው ፣ ለግሪክ የወጣው መርሃ ግብር አደጋ ላይ ይወድቃል የሚለውም የብዙዎች ስጋት ነበር ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አስተያየት ሰጭዎች ሃገሪቱ በግራዎቹ እጅ ብትወድቅ ኖሮ መጨረሻዋ አያምርም እያሉ ነበር የሚያስጠነቅቁት ። በነርሱ አስተያየት ግሪክ ለአውሮፓ ህብረት ቃል የገባቻቸውን ግዴታዎቿን ካልተወጣች እዳውን መክፍል ተስኗት ከዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገራት ማህበር ለመውጣት መገደዷ አይቀርም ። ይህም ሃገሪቱን ፈፆሞ እንድትንሰራራ የማያደርግ ነው ። የተፈራው ቀርቶ ግን የአውሮፓ ህብረትን ቃል ለማክበር የተስማማው ፓርቲ በማሸነፉ ይህ ሁሉ ስጋት ቀንሷል ። ምንም እንኳን አሸናፊው አዲስ ዲሞክራሲ ለግሪክ በቀረበው የአውሮፓ ህብረትና የዓለም ዓቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች  መፍትሄ ቢስማማም መሪው ሳማራስ ግን በአንዳንድ የብድር

ቅድመ ግዴታዎች ላይ እንደገና መደራደሬ አይቀርም ብለዋል ። ሳማራስ ፣ ግሪክ በአውሮፓ ህብረት ና በዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለተጠየቀችው የወጪ ቅነሳ ተጨማሪ 2 ዓመታት እንዲሰጣት ጥሬ አቅርበዋል ። ይህ አነጋጋሪ ቢመስልም ሊሆን የሚችልበት ፍንጭ ግን ተሰምቷል ። ግሪክ ብድሯን የምትመልስበት ጊዜ ይራዘም ስለማለቷም ሆነ እንደገና ለድርድር ሊቀርቡ ስለሚችሉ ጉዳዮች የተጠየቁት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬለ በጉዳዩ ላይ እንደገና መነጋገር ሳያስፈልግ እንዳልቀረ ጠቁመዋል ።

« ግሪኮች በርግጥ ከአውሮፓ ጋር ለመቆየት ወስነዋል ። ከገቡበት አርንቋ ሊወጡ የሚችሉት በጥንካሬና በፅናትና የተሃድሶ መርህን ተግባራዊ ሲያደርጉት ነው ። የተሃድሶ ተቃዋሚዎች ጥቂቶች ናቸው ። ለተሃድሶው የቆሙት ብዙሃኑ ናቸው ። ግሪክ እዳዋን መልሳ የምትከፍልበት የጊዜ ገደብ ላይ ለመነጋገር ዝግጁ ነን ። የባከኑ ሳምንታት አሉ ።  ይህ በቸልተኛነት ሊታይ አይገባም ። ሰዎችም ካለው ከባድ የኑሮ  ሁኔታ ጋራ ተያይዞ እየተጎዱ ነው ። ለምን ቢሉ ብዙ የተሃድሶ መርሃ ግብሮች ባለፉት ጊዜያት እንዲሁ በወረቀት ብቻ ሰፍረው የቀሩ ስለሆነ ነው ። የተሃድሶ ለውጡን በተመለከተ ዋናው ቁም ነገር ለውጥ ሳይደረግ ተግባራዊ ነው የሚሆነው ።መሆን ያለበትም እንደዛ ነው ። አለበለዚያ  በግሪክም ሆነ በሌላውም የአውሮፓ ክፍል ቀድሞ የነበረው ተዓማኒነት ሊመለስ አይችልም  ።  » ቬስተርቬለ ስለ ተጨማሪ ንግግር የሰጡት ይህ አስተያየት ግን በጋራ ያልተመከረበት ነው በሚል ከጀርመን መንግሥት በኩል ቅሬታ ተሰንዝሮበታል ። መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው ፤ ትኩረት የሰጡት ግሪክ ለአውሮፓ አገሮች የገባችውን ግዴታ ተግባራዊ ለማድረግ ፣ ቃሏን አክብራ መቀጠሏ ላይ ነው ። ይህን ታደርጋለች ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል ። በርሳቸው አስተያየት በህብረቱ ደረጃ አንዴ የተላለፈ ውሳኔ በምርጫ ምክንያት ሊለውጥ ና ሊስተካከል አይገባም ። ግሪክን በተመለከተም ከተሃድሶ እርምጃው ምንም የሚቀር ነገር አይኖርም ።

« አውሮፓ ውስጥ  ተባብረን ያዘጋጀነውን ውል ቀጣይነት ምን ጊዜም ምርጫዎች አጠያያቂ ሊያደርጉት እንደማይገባ ስንራምደው የቆየ  መመሪያ ነው ። ይህም ከግሪክ ጋር ስምምነት የተደረገበትን የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ጭምር የሚመለከት ነው ። የተሃድሶው እርምጃዎች ተግባራዊ ሲሆን ማለፊያ ምልክት ይሆናል ። ግን ከእነዚህ የተሃድሶ እርምጃዎች አንድም ሊሰረዝ የሚገባው ነገር የለም ። »

የእሁዱን ምርጫ ውጤት የአውሮፓ ህብረት በደስታ ነው የተቀበለው ።

የአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሆሴ ማኑኤል ህብረቱ ግሪክን ለመርዳት አሁን ወደ ኋላ የማይል መሆኑን አስገንዝበዋል ።

«ግሪክን  መርዳት እንችል ዘንድ ፤ባስቸኳይ መንግሥት እንዲመሠረት ነው የምንጠባበቀው። ግሪክም ዕድገት በምታስገኝበት ምጣኔ-ሃብታዊ እንቅሥቃሴ ላይ ታተኩራለች።  እርግጥ ነው፤ መሠረታዊው የግሪክና የዩውሮ ማኅበርተኛ ሃገራት ማስተካከያ አቅድ ተግባራዊ እንዲሆንም ነው የምንሠራው። አንድ ግልጽ የሆነ መልእክት ለግሪክ ዜጎች ሁሉ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። ከጎናችሁ ቆመናል። ግሪክ፤ የዩውሮ ተጠቃሚ ሃገራት ማኅበርተኛነቷን እንዲሁም የአውሮፓው ኅብረት ቤተሰብ አባልነቷን ማንም አይክድም። ከአናንተ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጂ ነን። በማንኛውም ረገድ ከመርዳት የምናፈግፍግበት ሁኔታ የለም። ይህም ሲሆን፤ በግሪክ ዕድገት ይመዘገባል፤ ሠራተኛውም ወደ ሥታ ገበታው የሚመለስበት ሁኔታ ይፈጠራል ።»

በአሁኑ ምርጫ ያሸነፈው አዲሱ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከሶሻል ዲሞክራቶቹ ከፓሶክ ና ከግራ ዲሞክራቶች ፓርቲ ጋር ተጣማሪ መንግሥት ለመመሥረት ከትናንት አንስቶ እየተደራደረ ነው ። ሶስቱ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ ለመድረስ መቃረባቸው ዛሬ ከቀትር በኋላ ተሰምቷል ። ውጤቱም ማምሻውን ይፋ ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው ።

ባለፈው እሁድ  በፈረንሳይም የምክር ቤት ምርጫ ተካሂዶ ሶሻሊስቶች አብላጫ ድምፅ አግኝተዋል ። ከ 3 ዓመት በፊት በተቺዎች አስተያየት የሞተ ያህል ይቆጠር የነበረው ሶሻሊስቱ ፓርቲ ባለፈው እህድ ታሪካዊ ውጤት ነው ያስመዘገበው ። ከፈረንሳይ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት 577 መቀመጫ የኦሎንድ ሶሻሊስት ፓርቲ 320ውን ወስዷል ።ፓርቲው በአሁኑ ምርጫ ከወግ አጥባቂዎቹ ተቃዋሚዎች ከ1 መቶ የሚበልጥ መቀመጫዎች አሉት ። በዚሁ 2 ተኛ ዙር ምክር ቤታዊ ምርጫ የተገኘው ውጤት በቅርቡ የተመረጡት ሶሻሊስቱ ፕሬዝዳንት ፍርንሷ ኦሎንድ በአዲሱ የኢኮኖሚ ተሃድሶ እንዲገፉ ኃይላቸውን እንደሚያጠናክር ተገምቷል ። ኦሎንድ አሁን በሁለት እግራቸው መቆም ችለዋል ። በአውሮፓ ከቁጠባ ይልቅ እድገትና የሥራ እድሎችን መፍጠር ላይ ትኩረት ይደረግ የሚል ሃሳብ ይዘው ብቅ ያሉት ኦሎንድ ከፊታቸው ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል ። ለመረጣቸው ህዝብ የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረግ መቻል አለመቻላቸው ማጠያየቁ አልቀረም ። ፈረንሳይ ብዙ እዳ አለባት ። እድገት እየቀነሰ

ሲሆን የሥራ አጡ ቁጥር ም 10 በመቶ ደርሷል ። ኦሎንድ የፈረንሳይን የበጀት ጉድለትን በማስተካከል እጎአ እስከ 2017 ወደ 3 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ቃል ገብተዋል ። የወጪ ቅነሳ ማድረግም ይጠብቅባቸዋል ። በዓመት ቢያንስ 20 ቢሊዮን ዩሮ መቆጠብ ይኖርባቸዋል ። ይህ ደግሞ ቃል የገቡለትን የህብረተሰብ ክፍል በሙሉ በመንካት መራጮቻቸውን ቅር ማሰኘቱ አይቀርም ። በሌላ በኩል ደግሞ በቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ዘመን የጎላው የጀርመንና የፈረንሳይ ቅርበት በሶሻሊስቱ ፕሬዝዳንት ሊቀጥል አልቻለም ።ኦሎንድ ባለፈው ሳምንት ከኢጣልያው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርዮ ሞንቲ ጋር የመሰረቱት የፓሪስና ሮም የእድገት ዛቢያ ያሉት ጉድኝት በዩሮ ላይ ከደረሰው ቀውስ አኳያ ለደቡባውያኑ የአውሮፓ ሃገሮች የእድገት እንቅስቃሴ መርህ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል ። አንጌላ ሜርክል ደግሞ በአውሮፓ የጀርመን ዋነኛዎቹ ተጓዳኞች የቁጠባ የፖለቲካ መርህ ላይ ኦሎንድ የላቀ ተቃውሞ

እንደሚያቀርቡ ማሰላሰል ሊኖርባቸው ነው ። የዚህ ተቃውሞ ማንፀባረቂያ ቃል በተደጋጋሚ እንደሚሰማው የእድገት ፅንሰ ሃሳብ የተሰኘው ነው ኦሎንድ በአውሮፓ ኤኮኖሚን ማንቀሳቀስ ይቻል ዘንድ 120 ቢሊዮን ዩሮ ማውጣት ይፈልጋሉ ። ይህ ገንዘብ ደግሞ በቴሌኮምኒኬሽን ፣ በ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ና በናኖ እንዲሁም በባዮ ቴክኖሎጂ መስክ እንዲውል ነው የሚፈልጉት ። ከዚህ በተጨማሪ በፋይናንስ ዝውውር ላይ ቀርጥ

እንዲጣልም ይሻሉ ። ይሄ እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን የሚፈልጉትም  ጥቅም ላይ ካልዋለው የአውሮፓ ህብረት የመጠባበቂያ የእርዳታ ገንዘብና ከአውሮፓ የኢንቬስትመንትን ባንክ ወረት ከፍ በማድረግ ነው ። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት አሁን ከአንጌላ ሜርክል ጋር የኃይል መፈተኛ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል ።አንዳንድ የመከራከሪያ ሃሳቦቻቸው ሲመረመሩ ኦላንድ እውነት እንዳላቸው ይመስክሩላቸዋል ። ጀርመናውያን አሁን የሚሉት ሁሉም የየራሱን በጀት መቆጣጠር ይኖርበታል ፤ የጋራ የመቆጣጠሪያ ህግም ይኖረናል ነው ። ኦሎንድ  በሚመጡት ሳምንታት ለነዚህ መልሱን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 19.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15I16
 • ቀን 19.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15I16