በጌዲዖ ″በረሐብ በየቀኑ ከ 3 እስከ 4 ሰው ይሞታል″ ቄስ ወልዴ አየለ | ኢትዮጵያ | DW | 16.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በጌዲዖ "በረሐብ በየቀኑ ከ 3 እስከ 4 ሰው ይሞታል" ቄስ ወልዴ አየለ

ከምዕራብ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው በጌዲዖ ዞን ከተጠለሉ ዜጎች መካከል በረሐብ በየቀኑ ከ3-4 ሰው እንደሚሞት የወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነየሱስ የደቡብ ሲኖዶስ ፕሬዝዳንት ተናገሩ። የዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ እንደሚሉት ተፈናቃዮች ተጠጋግቶ በመኖር ለሚከሰቱ ተላላፊና የውሐ ወለድ በሽታዎች ተጋልጠዋል።

ከአስር ወራት በፊት በጌዲዖ እና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች በተቀሰቀሰ ግጭት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ከ198 ሺሕ በላይ ዜጎች ለአስከፊ ችግር መጋለጣቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት እና የወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን ኃላፊ ተናገሩ።

ከመኖሪያ ቀያቸው በግጭት ሳቢያ ተፈናቅለው በቀበሌዎች፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና ጥራታቸውን ባልጠበቁ መጠለያዎች የሚገኙ ዜጎች ለአስከፊ ረሐብ እና ተጠጋግቶ በመኖር ለሚከሰቱ ተላላፊ እና የውሐ ወለድ በሽታዎች መጋለጣቸውን በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ ገልጸዋል።

"ከምዕራብ ጉጂ ተፈናቅለው በጌዲዖ ዞን ብቻ የተጠለሉ 198 ሺሕ 977 ሰዎች ይገኛሉ" ሲሉ የዞኑ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ትዕግስቱ ገዛኸኝ ለDW ተናግረዋል።

አቶ ትዕግስቱ "ተፈናቃዮቹ በስድስት ወረዳዎች እና በአንድ የከተማ አስተዳደር ይገኛሉ።  ከዚህ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ገደብ ወረዳ ሲሆን ወደ 96 ሺሕ ተፈናቃዮች ይገኛሉ" ሲሉ ተናግረዋል።

በገደብ ወረዳ በገደብ ከተማ እንዲሁም ጎቲቲ፣ ባንቆራ እና ጮርሶ ማዞሪያ በተባሉ ቀበሌዎች የተጠለሉ ተፈናቃዮችን ተዘዋውረው የተመለከቱት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነየሱስ የደቡብ ሲኖዶስ ፕሬዝዳንት ቄስ ወልዴ አየለ ተፈናቃዮቹ "እጅግ በሚያሳዝን ኹኔታ" ላይ እንደሚገኙ ለ«DW»አስረድተዋል።  

"በረሐብ ብቻ በየቀኑ በአማካኝ ከሶስት እስከ አራት ሰው ይሞታል" የሚሉት ቄስ ወልዴ አየለ "ከአንድ ወር ወዲህ ጭራሽ እርዳታ የሚባል ነገር የቆመበት ኹኔታ ነው ያለው። ሰው በረሐብ የተጎዳበት ኹኔታ ነው ያለው" ሲሉ አክለዋል።

ተፈናቃዮች ለከፋ የምግብ እጥረት በመጋለጣቸው የሚስማሙት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ትምህርት ቤት ኃላፊ አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ "የሰው ምግብ አጥተው ድሮ ለከብቶቻቸው ይሰጡት የነበረውን ቀለብ መመገብ ጀምረዋል" ሲሉ የችግሩን ጥልቀት ይገልጻሉ።

ኃላፊው እንደሚሉት ተፈናቃዮች ተጠጋግቶ በመኖር ለሚከሰቱ እንደ ኮሌራ፣ ኩፍኝ፣ ማጅራት ገትር የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ተጋልጠዋል።

አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ የኢትዮጵያ መንግሥት ተፈናቃዮቹን ቸል በማለቱ እና የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ እንዳይሰጡ መከልከሉ ችግሩን የከፋ እንዳደረገው ያምናሉ። አቶ ትዝአለኝ ተፈናቃዮች "ምግብ ሲከለከሉ ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ" የሚል ግምት በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ አለ ሲሉ ይወቅሳሉ።

የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ትዕግስቱ ግን የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ ለማቅረብ ክልከላ አልተደረገም ሲሉ አስተባብለዋል። አቶ ትዕግስቱ እንደሚሉት ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያ ቀያቸው ይመለሳሉ በሚል እሳቤ እርዳታ ከሚሻቸው ጎራ ሳይመደቡ ቀርተዋል።

ኃላፊው "ምዕራብ ጉጂ አካባቢ የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ከተደረሰው መግባባት የተነሳ መሔድ አለባቸው የሚል አቋም ነበረ። ነገር ግን እዚያ ምቹ ኹኔታ ባለመኖሩ መመለስ አልቻሉም። ስላልቻሉ እነዚህ ሰዎች በሚሰጠው ምግብ አልተካተቱም" ሲሉ ተናግረዋል።

ባለፈው አመት መገባደጃ በጌዲዖ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች በተቀሰቀሰ ግጭት ከ950 ሺሕ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ከተፈናቀሉ አስር ወራት ተቆጥረዋል።  ዓለም አቀፉ የስደተኞች መርጃ ድርጅት መረጃ እንደሚጠቁመው እስካለፈው የካቲት ድረስ ከ600 ሺህ በላይ ዜጎች በሁለቱ ዞኖች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ይገኛሉ።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከጌዲዖ የተፈናቀሉ ዜጎች ተርበል፤ ተጠምተዋል ታርዘዋል የሚሉ የማኅበራዊ ድረ-ገፅ መልዕክቶች በስፋት ይሰራጩ ጀምረዋል። እርዳታ ለማሰባሰብ የሚጥሩ፤ ችላ ያላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትኩረት ይሰጧቸው ዘንድ የሚወተውቱም አልጠፉም።

በመላው ዓለም ያሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጉዳይ የሚከታተለው IDMC የተባለው ተቋም ከዚህ ቀደም አንድ ዘገባ አውጥቶ ነበር። በዘገባው የምዕራብ ጉጂ እና የጌድዖ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የሕዝብ ቁጥር በድንገት በእጥፍ በመጨመሩ የውሐ እና የጤና አገልግሎቶች በበቂ መዳረስ አለመቻላቸውን እና የምግብ እጥረት እየጨመረ መምጣቱንም አስታውቋል።

ተፈናቃዮቹ በቂ የግል ንፅህና መጠበቂያ ግልጋሎት ባለማግኘታቸው ብዙዎች በብርድ ልብስ እና በፍራሽ እጦት በቀዝቃዛ ወለል ላይ ለመተኛት በመገደዳቸው የበሽታ ወረርሽኝ ሊቀሰቀስ እንደሚችል የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ሥጋት አላቸው።

እሸቴ በቀለ 

 

ተዛማጅ ዘገባዎች