በጋምቤላ ጥቃት 108 ህጻናት ታፍነው ተወስደዋል | ይዘት | DW | 17.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ይዘት

በጋምቤላ ጥቃት 108 ህጻናት ታፍነው ተወስደዋል

በምዕራብ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ድንበር የተሻገሩ ታጣቂዎች በዕለተ አርብ ማለዳ በፈጸሙት ጥቃት ህጻናት መታገታቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ተናገሩ። ቃል-አቀባዩ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ በጥቃቱ ምን ያኽል ሰዎች ታግተው እንደተወሰዱ አለመናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በትንሹ 140 ኢትዮጵያውያን በተገደሉበት ጥቃት የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸውም ተሰምቷል። ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን የምትዋሰንበትን ድንበር ተሻግረው በኑዌር ጎሳ አባላት ላይ ጥቃት የፈጸሙት የሙርሌ ጎሳ አባላት አፍነው የወሰዷቸው ህጻናት ቁጥር 108 መሆኑን የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ዘግቧል። የተደራጀው ታጣቂ ኃይል፦ «ሚያዝያ 7 ከሌሊቱ 11 ሰአት እስከ ጠዋቱ 2 ሰዓት በፈፀመው ጥቃት» 182 ሰዎች መገደላቸውን ለመንግስት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። የኢትዮጵያ ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ በጥቃቱ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 140 መሆኑን እና የአገሪቱ ጦር ከታጣቂዎቹ መካከል 60 መግደሉን ለዎልስትሪት ጆርናል ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባዩ አቶ ተወልደ ሙሉጌታም ሆኑ የመንግስት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ኃላፊው አቶ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ ጦር በታጣቂዎቹ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ቢያረጋግጡም ጦር ሰራዊቱ የደቡብ ሱዳንን ድንበር ስለመሻገሩ ምንም ነገር አለማለታቸውን የውጭ ሀገር የዜና አውታሮች ጠቅሰዋል። ለመንግስት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ግን መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ሱዳን ድንበርን በመሻገር ጥቃት ማድረሱን ዘግበዋል። የደቡብ ሱዳን የማስታወቂያ ሚንሥትር ሚካኤል ማኩዊ መንግሥታቸው በግጭቱ እጁ እንደሌለበት እንደውም «ጥፋተኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ጋር እንተባበራለን» ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም «ሆኖም ግን ሉዓላዊ ሀገር እንደሆንን እንቀጥላለን» ብለዋል። ከ272,000 በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በተጠለሉበት የጋምቤላ ክልል በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ኢትዮጵያውያን በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ቁጣቸውን እና ቁጭታቸውን በመግለጥ ላይ ናቸው። የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት የአገሪቱን ዜጎች ከጥቃት መከላከል አለመቻሉን የኮነኑ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውን ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ ጥሪ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ