በጋምቤላ የደረሰዉ ጥቃት | ኢትዮጵያ | DW | 20.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

በጋምቤላ የደረሰዉ ጥቃት

በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ቀበሌዎች ከደቡብ ሱዳን ድንበር ተሻግረዉ በገቡ ታጣቂዎች የደረሰዉን ግድያ፣ እገታ እና ዘረፋ በተመለከተ ኢትዮጵያ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ብሔራዊ ሀዘን አዉጃለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:35
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:35 ደቂቃ

ጋምቤላ

ባለፈዉ ሳምንት ማለቂያ ገደማ ሳይታሰብ የደረሰዉ የሙርሌ ጎሳ አባላት ናቸዉ የተባሉት ታጣቂዎች ጥቃት በአንድ ወገን የተለመደ በድንበር አካባቢ የሚፈጸም የዘረፋ ጥቃትና አደጋ ነዉ የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ፤ ከዚህ በተቃራኒዉ የደቡብ ሱዳን መንግሥት እጅ አለያም ከድንበር አካባቢ አዲስ ክለላ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚሉም አልጠፉም። ከሀገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደተሰማዉ መንግሥት ሠራዊቱን ወደ ደቡብ ሱዳን ግዛት ልኮ በሰነዘረዉ የአፀፋ ጥቃት ስልሳ የሚሆኑ ተገድለዋል። የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት በበኩሉ ታግተዉ የተወሰዱትን ሕፃናትንም ሆነ የተዘረፉትን ከብቶች ለማስመለስ ጥረት መጀመሩን ይናገራል።

የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝደንት አቶ ገትሉዋክ ቱትኮት እንደሚሉት ድንበር ተሻግሮ የመጣዉ የሙርሌ ታጣቂ ኃይል ወታደራዊ ልብስ የለበሰ ነዉ። እሳቸዉ እንደሚሉት ገና ሳይነጋ ኗሪዉ እንቅልፍ ላይ እንዳለ ጥቃት በመሰንዘሩ ተገቢዉ መከላከል ባለመደረጉ እንጂ በስፍራዉ የታጠቀ የወገን ኃይል ባለመኖሩ አይደለም የከፋዉ ጉዳት የደረሰዉ። ሕዝቡ ራሱን እንዳይከላከል ትጥቅ እንደፈታ ተደርጓል የሚባለዉን የክልሉ ፕሬዝደንት አስተባብለዋል።

Flash-Galerie Äthiopien Land Grab

በደቡብ ሱዳን ያለዉ የእርስ በርስ ግጭት ጦርነት በርካታ የጦር መሣሪያ በአካባቢዉ እንዲበተን ምክንያት እንደሆነም በማመልከት በሕገወጥ መንገድ መሣሪያ የሚያዘዋዉሩት ላይ ርምጃ እየተወሰደ ነዉም ብለዋል። ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ሰዎችም ተገቢዉን ርዳታ በማድረግ ወደቀየያቸዉ የመመለስ ሥራ እየተሠራም እንደሆነ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ሃገራት ለፀጥታ ማስከበር ሥራ የሚያሠማራዉ በቂ ወታደራዊ ኃይል አለዉ። በተቃራኒዉ ግን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የፀጥታ ችግር ማጋጠሙ ይታያል። ይህ ተቃርኖ ሁሉንም እንደሚያስገርም ያመለከቱት በኢትዮጵያ ፍትሃዊ አስተዳደር እንዲሰፍን አጥብቀዉ በሰላማዊ መንገድ እንደሚታገሉ ያለመከቱት የፖለቲካ ጉዳይ አዋቂ አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኘዉ ሕዝብም ዋስታ አጥቷል ይላሉ። ጋምቤላ ዉስጥ በደረሰዉ ጥቃት የተሰማቸዉን ጥልቅ ሀዘን በግላቸዉ ለሕዝቡ አስተላልፉልኝ ያሉት አቶ አስገደ አክለዉም በርካታ ጦር ሠራዊት ባለበት ሀገር እንዲህ ያለዉ አደጋ መድረሱ አሳፋሪ እንደሆነ ነዉ ያመለከቱት። የሀገር ዉስጥ መገናኛ ጋምቤላ ዉስጥ ለተፈጸመዉ ግድያ አጸፋ ብዙሃን የመንግሥት ኃይሎች ደቡብ ሱዳን ገብተዉ 60 የሚሆኑ ሰዎችን መግደላቸዉን ያመለክታሉ። አቶ አስገደ ይህ ተደርጎ ከሆነ ዝንደዉ ዝም ከማለት በሚል ካልሆነ በቀር የሚያመጣዉ ዉጤት አልታየኝም ይላሉ። በሌሎች ሃገራት እንኳን ከሁለት መቶ የሚበጡ ዜጎች ሕይወት ጠፍቶ አይደለም ለአንድ ግለሰብም ሕይወት ቢሆን ብሔራዊ ሀዘን የሚታወጀዉ ወዲያዉ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ፤ የጋምቤላዉ ጥቃት በደረሰ ከአምስት ቀናት በኋላ ዘግይቶ የሀዘን ቀን መታወጁ ከትችት እንደማያድን ሳይገልጹ አላለፉም።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic