በጉጉት የሚጠበቀዉ የናይጀሪያ አዲሱ ካቢኔ | አፍሪቃ | DW | 07.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በጉጉት የሚጠበቀዉ የናይጀሪያ አዲሱ ካቢኔ

የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ማሃማዱ ቡሃሪ የአዲሱ መንግስታቸዉን ካቢኔ አባላት ዝርዝር ትናንት አሳወቁ። ታሪካዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ሽግግር በተካሄደባት በምዕራብ አፍሪቃዋ ሰፊ ሃገር ናይጀሪያ ላለፉት ስድስት ወራት ካቢኔ ሳይሰየም መቆየቱ ማነጋገሩ አልቀረም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:14
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:14 ደቂቃ

በጉጉት የሚጠበቀዉ የናይጀሪያ አዲሱ ካቢኔ

ለካቢኔ ያጩዋቸዉ 21 ባለስልጣናትም ሙሉ በሙሉ አዎንታ አልተቸራቸዉም። በነዳጅ ዘይት ሃብቷ የምትታወቁዉ ናይጀሪያን ከሙስና ለማፅዳት የሚዝትቱት ቡሃሪ ከእንግዲህ ወትሮ በተለመደዉ አካሄድ አንጓዝም እያሉ ነዉ። ምናልባትም ቡሃሪ ምርጫዉን በድል አጠናቀዉ ሲያበቁ ካቢኔ ለመመሥረት ጊዜ የወሰደባቸዉ ሃሳባቸዉን የሚጥሉበት ተሿሚ ሲፈልጉ ይሆን?

ከሳምንታት በፊት በስልጣን ዘመናቸዉ አብረዋቸዉ የሚሰሩትን ሚኒስትሮች ስም ያሳዉቃሉ ተብለዉ ተጠብቀዉ ነበር። አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዝደንት ሙሃመዱቡሃሪ ግን እስከትናንት ድረስ እነማንን በካቢኔያቸዉ ለማካተት እንዳቀዱ ሳይታወቅ ቆይቷል። ከታጩት ዉስጥ አብዛኞቹ የሚታወቁ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ተስፋ የተጣለባቸዉ ሚኒስትሮች መሆናቸዉ ነዉ የሚነገረዉ። ከ21 እጩ የካቢኔ አባላት አንዱ በአዲስ የመንግሥት አስተዳደር ለምትዋቀረዉ ናይጀሪያ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ተብሉ የታሰቡት ኢማኔዉል ኢቤ ካቺክዌ ናቸዉ፤ ባለፈዉ ነሐሴ ወር ነበር የናይጀሪያ ብሄራዊ የነዳጅ ኮርፖሬሽን ኃላፊ ሆነዉ ተሹመዋል። አሁን የናይጀሪያ የነዳጅ ሚኒስትር ሆነዋል። ቡሃሪ እኝህን ባለስልጣን የካቢኔያቸዉ አባል እንዲሆኑ ጠይቀዋል። ካቺክዌ ኃላፊነታቸዉን እንደተቀበሉ የመንግሥታዊዉን የነዳጅ ኮርፖሬሽን የተባለሸ አሠራር በማፅዳት እና ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል የየዘርፉን ባለስልጣናት በማሰናበት ሥራቸዉን ጀምረዋል። የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ ካቺክዌ የEXXON ሞባይል ሥራ አስኪያጅ ሆነዉም አገልግለዋል። ናይጀሪያ ዉስጥ የነዳጅ ዘርፉ በከፍተኛ ሙስና የተዘፈቀ መሆኑን የሚናገረዉ ሀገሪቱን በቅርብ የሚያውቃት ጋዜጠኛ ሃይንሪሽ በርግሽትረሰር፤ በዚህ አካሄድ ቡሃሪ የናይጀሪያን የሙስና አስኳል ማፍረስ እንደሚሳካላቸዉ ያምናል።

«መሠረታዊዉ ነገር የነዳጅ ዘይቱ ዘርፍ የሙስናዉ አስኳል መሆኑ ነዉ። በዚያ ላይ አዲስ የአሠራር ደረጃ ያስፈልጋል፤ ቡሃሪም በዚህ ላይ እንዲህ ያለ ለዉጥ የሚያመጣ ሚኒስትር ለማስቀመጥ ደህና አድርገዉ መምከራቸዉ በግልፅ ይታያል። እናም ከፍተኛ የሙስና ምንጭ የሆነዉን አሠራር መዝጋት ይችላሉ።»

ካቢኔያቸዉን ለመሠየም የፈጁት ጊዜም የተሻለች ናይጀሪያን ለመገንባት ይመጥናሉ የሚሏቸዉን ሚኒስትሮች ለመምረጥ ነዉ ባይነዉ። የአቡጃ ዩኒቨርሲቲዉ የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አቡበከር ማርካሪም ለካቢኔ አባልነት የቀረበዉ ስም ዝርዝር እዉቀትን ከልምድ ያዛመዱ ባለስልጣናትን ያካተተ መሆኑን ያረጋግጣሉ።

«አስገራሚ ሊሆን የሚችለዉ ሃሳብ ከሳምንታት በፊት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲብላላ ሰንብቷል። ስለዚህ አስደናቂ ነገር የለም። ነገር ግን በጥቅሉ በጣም ጥሩ የስም ዝርዝር ያካተተ ነዉ። እጅግ ሠፊ የሥራ ልምድና የፖለቲካ ሚና አላቸዉ። በዝርዝሩ ስማቸዉ ከተካተተዉ አብዛኞቹ ቀደም ሲል የተሞከሩና የተፈተኑ፤ ጠቃሚ ቦታዎችን ማለትም እንደአገረ ገዢ እና ሚኒስትር የነበሩ ናቸዉ። እናም ሚዛናዊ የሆነ ጥሩ ዝርዝር ነዉ።»

የካቢኔ አባላቱ ስም ዝርዝር ቀድሞ የሌጎስ ግዛት አገረ ገዢ ባባቱንዴ ፋሾናን፤ የቀድሞ ሪቨርስ ግዛት አገረ ገዢ ሮቲሚ አማቺን እንዲሁም የሰብዓዊ ጉዳዮች ተሟጋች ካዮዴ ፋያሚንም ያካትታሉ። ከዚህም ሌላ ቡሃሪ በምርጫ ፉክክር የስልጣን መንበራቸዉን የተረከቧቸዉ የቀድሞዉ ፕሬዝደንት ጉድላክ ጆነተንን ፓርቲ አባላትንም ይጨምራል።

ምንም እንኳን ፕሬዝደንት ቡሃሪ የናይጀሪያን የቀድሞ ገፅታ ሊለዉጡ ይችላሉ በሚል ያጩዋቸዉ ሚኒስትሮች በብዙዎች ዘንድ በአዎንታ ተቀባይነት ያገኙ ቢሆኑም ከፆታ ተዋፅኦ አኳያ ሲታይ ከ20 የካቢኔ ሚኒስትሮች መካከል ሴቶቹ ሶስት ብቻ ናቸዉ። ያም ቢሆን ግን ከቀድሞዉ ፕሬዝደንት ጀነተን ጋር ሲነፃፀር የካቢኔ አባሎቻቸዉ የተለያዩ የሃገሪቱን ግዛቶች የሚወክሉ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ እየተነገረ ነዉ። ይህም እንደተንታኞች ግምት ፕሬዝደንቱ ብቻቸዉን ሳይሆን እያንዳንዱ ሚኒስቴር የወከለዉን አካባቢ ፍላጎት ያካተተ ዉሳኔ ለማሳለፍ እንደሚረዳ ተገምቷል። እስካሁን የ21ዱን ማንነት ይፋ ቢያደርጉም ካቢኔዉ 35 ሚኒስትሮችን የሚይይዝ በመሆኑ የቀሩት ስም እየተጠበቀ ነዉ። ማን የየትኛዉ ተቋም ሚኒስትር እንደሚሆን ግን ገና አልታወቀም። ዋናዉ ጥያቄ ፕሬዝደንት ቡሃሪ ናይጀሪያ ዉስጥ አመጣዋለሁ ያሉትን ለዉጥ ማሳካት ይችላሉ ወይ የሚለዉ ነዉ። የፖለቲካ ምሁርና ተንታኝ የሆኑት ናይጀሪያዊ ዶክተር ዑመር አርዶ ዉጤቱ የፕሬዝደንቱ አመራር ላይ የተመረኮዘ ይሆናል ነዉ የሚሉት።

«በመሠረቱ የፕሬዝደንቱ ረዳቶች ናቸዉ። ከፕሬዝደንቱ ጎን ሆነዉ የሚፈለገዉን ለማሳካት የመቻል እና ያለመቻል ጉዳይ የአመራሩ አቅጣጫ የሚወስነዉ ነዉ የሚሆነዉ። አስተዳደሩ እነሱን የሚገመግምበት መንገድም ለዉጥ የማምጣት ችሎታቸዉን የሚቆጣጠር ይሆናል። ስለዚህ ምሳሌነት ያለዉ አመራር ካለን፤ ፕሬዝደንቱ በምሳሌነት የሚመራ ከሆነ ረዳቶቹ የእርሱን እግር መከተላቸዉ የማይቀር ነዉ። እናም ይህ ፕሬዝደንቱን ይመለከታል።»

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic