1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጉጂ ዞኖች ተፈጸሙ የተባሉ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች

እሑድ፣ ሰኔ 9 2016

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞኖች ከባባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) አስታወቀ፡፡ ተቋሙ በዞኑ “ከባባድ” ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸው ቢቀጥልም እስካሁን ተገቢውን ትኩረት አላገኙም ብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/4h6eS
ምዕራብ ጉጂ
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞኖች ከባባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) አስታወቀ፡፡ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) በጉጂ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ያወጣው መግለጫ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞኖች ከባባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) አስታወቀ፡፡

የሰብአዊ ተቋሙ አደረኩ ያለውን በአከባቢው ላይ ያተኮረ የሰብዓዊ ጉዳዮች ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ይፋ ሲያደርግ በጉጂ ዞኖች በታጣቂዎች እና በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች መካከል ለዓመታት በዘለቀው ነውጥ አዘል ግጭት “ከባባድ” ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸው ቢቀጥልም እስካሁን ተገቢውን ትኩረት አላገኙም ብሏል፡፡

ማዕከሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አስመልክቶ የሰላም፣ የፍትህ እና ተጠያቂነት ጥሪ አቅርቧል፡፡

የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ከተለያዩ የጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ነዋሪዎች ጋር የምክክር መድረክ በማመቻቸት በነውጥ አዘል ግጭቶች ሳቢያ ንጹሃን ላይ የሚደርሱ ተጽእኖዎችን ለመረዳት በሰብዓዊ መብቶች ክትትል፣ ዶክመንተሽንና አዘጋገብ ላይ ሰዎችን አሰልጥኖ በማሰማራት ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን አመልክቷል፡፡ ካርድ በዚህ ሂደት በተለያዩ የጥናት ዘዴዎች ያሰባሰባቸውን ማስረጃዎች በ36 የማሳያ ታሪኮች ሰንዶ ዛሬ መገናኛ ብዙሃን እና ባለድርሻ አካላትን ጠርቶ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ይፋ አድርጓልም፡፡

እነዚህ የተሰበሰቡ ማስረጃዎች በአከባቢው በምንቀሳቀሱ ሁለቱም ተፋላሚዎች ማለትም በመንግስት የጸጥታ ኃሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በስፋት ስፈጸሙ እንደነበር አስረጂ ናቸው ተብሏልም፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከምዕራብ ጉጂ ዞን ከሚገኝ ቀበሌ ወደ ኮሬ ዞን መሸሻቸውን የዐይን እማኞች ተናገሩ

የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶቹ ተጽእኖ

የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) ዋና ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ኃይሉ ሪፖርቱን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ የዚህ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሁኔታዎችን መሰነድ ያስፈለገው በአከባቢው ይፈጸማል ያሉት ከባባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና የነዋሪዎች ሰቆቃ ለብዙሃን እዲደርስ ታስቦ ነው፡፡ “የሪፖርቱ ዓላማ ነውጥ አዘል ግጭቶች በተሌም በሁለቱ የጉጂ ዞኖች በንጹሃን ህይወት ላይ እየተፈጸመ ያለውን ለመስማት አስቸጋሪ የሆነውን ተጽእኖ እንደማሳያ በማቅረብ በሌሎች የኢትዮጵያ አከባቢዎች ያሉ ነውጦች በሙሉ ተኩስ አቁም እንዲቋጩ፤ በፖለቲካ ድርድር እንዲፈቱና ዜጎች ሰላማዊ ህይወት ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ነው” ብለዋልም፡፡

ምዕራብ ጉጂ ዞን አውራ ጎዳና
የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ከተለያዩ የጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ነዋሪዎች ጋር የምክክር መድረክ በማመቻቸት በነውጥ አዘል ግጭቶች ሳቢያ ንጹሃን ላይ የሚደርሱ ተጽእኖዎችን ለመረዳት በሰብዓዊ መብቶች ክትትል፣ ዶክመንተሽንና አዘጋገብ ላይ ሰዎችን አሰልጥኖ በማሰማራት ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን አመልክቷል፡፡ምስል Private

የጉጂ ገዳ የስልጣን ርክክብ ከስምንት ዓመት በኋላ ሜኤ ቦኩ ላይ ይደረጋል

በሪፖርቱ የተካተቱ 36 ማሳያ ታሪኮች በአማጺ ታጣቂዎች እና በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ከህግ ውጪ ንጹሃን ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ የዘፈቀደና የጅምላ እስራቶች፣ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የንብረት ውድመት፣ አስገድዶ መሰወርና የገንዘብ ማግኛ የእገታ ድርጊቶች፣ የማሰቃያና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ እንዲሁም የማፈናቀል ድርጊቶች የተፈጸመባቸው የንጹሃን ዜጎችን ታሪኮች ያዘለም ነው ተብሏል፡፡

በነዚህ ነውጥ አዘል ግጭቶች በዓለም አቀፍ፣ በአገር አቀፍ እና ክልላዊ ህግጋት የተደነገጉ መብቶች እና ነጻነቶች በመጣሳቸው ብሎም “አሰቃቂ” የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በመፈጸማቸው በጉጂ ዞኖች አሁን አሁን መደበኛ ህይወት እየተስተጓጎለም ነው ይላል የሰብዓዊ መብቶች ማዕከሉ ሪፖርት፡፡

በአዲሱ የጉጂ አባገዳ የተላለፈው የሰላም ጥሪ

“በነውጥ አዘል ግጭቶቹ ተጠቂ የሆኑት የጉጂ ዞኖች ነዋሪዎች ሰላምና ፍትህ ይሻሉ” ያሉት የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) ዋና ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ኃይሉ ከደረሰባቸው አካላዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት ማገገም፣ የደረሰባቸው የንብረት ውድመት እንዲተካላቸው፣ የተስተጓጎለ ህይወታቸውም እንዲቀጥል ብሎም እንደዜግነታቸው መልሶ መቋቋም ገባቸዋልም ብለዋል፡፡ ስለሆነም “ካርድ በዛሬው እለት ለጉጂ ህዝብ ድምጽ መሆን ይፈልጋል!” ነው ያሉት፡፡

የነውጥ አዘል ግጭቶቹ ተጽእኖ

በመሰል ነውጥ አዘል ግጭቶች ሳቢያ ለአሰቃቂ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የተዳረጉ፣ ልማት የተስተጓጎለባቸው፣ ንብረታቸውም ወድሞ ከቀዬያቸው የተፈናቀሉ፣ የተገደሉና ንጹሃን ወዳጆቻቸው የተገደሉባቸው ኢትዮጵያውያን በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች መኖራቸውንም ካርድ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ እነዚህ ነውጥ አዘል ግጭቶች የማይደርስባቸው የኢትዮጵያ አከባቢዎችም የሚኖሩ ዜጎችም ብሆኑ ከተጽእኖው ሰለባ መሆን አልዳኑም ያለው ሪፖርቱ፤ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ስራቸውን በአግባቡ መስራት የማይችሉበት የፖለቲካ ምህዳር እየተፈጠረ የኢከኮኖሚ ጫናውም እየከፋ ነው ብሏል፡፡

ጉጂ ዞን 12 ሰዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

ስለሆነም ይላሉ የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD) ዋና ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ኃይሉ “ስለሆነም ካርድ ለሁሉም በነውጥ አዘል ግጭቶች ሳቢያ ሰላም፣ ፍትህ እና ተጠያቂኔት ለተነፈጉ ኢትዮጵያውያን ይፈላጋል!”፡፡ “ነውጥ አዘል ግጭቶች ባሉበት ምህዳር አሰቃቂ የሰብዓዊ መብቶች ይበረክታሉ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባትም አይቻልም፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚም አይኖርም፣ የመንግስት ቅቡልነትና ተጠያቂነት ያሽቆለቁላል” ያሉት አቶ በፍቃዱ ካርድ በነውጥ አዘል ግጭቶች የሚመጣ አዎንታዊ ለውጥ አለ ብሎ እንደማያምን አመልክተዋልም፡፡

ስለሆነም በነውጥ የሚሳተፉ አካላት በሙሉ በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ላይ በመድረስ ለችግሮቻቸው ዘላቂ እልባት ሐቀኛ እና አሳታፊ ድርድር እንዲያደርጉ ተጠይቋልም፡፡ ካርድ በጉጂ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች ነውጥ አዘል ግጭቶች ንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሱ ያሉትን ከፍተኛ ተጽእኖ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የፍትህ ፍላጎታቸውን በማስተጋባት ድምጽ እንደሚሆናቸውም አስረድቷል፡፡ ዛሬ ጥናቱ ይፋ ስደረግም በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይም የተጋበዙ ባለድርሻ አካላት በጥናቱ ውጤት ላይ ሃሳባቸውን ሰጥተው ውይይት ተደርጓል፡፡  

ሥዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ