1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጉራጌ ዞን ቆሴ ከተማ ያለው ችግር ምንድን ነው?

ሰኞ፣ መጋቢት 19 2014

በጉራጌ ዞን ቆሴ በሚባል መለስኛ ከተማ አሁንም ድረስ በንብረት እና በህይወት ላይ ጉዳት እየደረሰ ነው ሲሉ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ሰሞኑን ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። ለዚህም ተጠያቂ የሚያደርጉት ቦታውን ይገባናል የሚሉ በሀዲያ ዞን የሚኖሩ ወጣቶችን ነው። እንደ የአካባቢው ባለስልጣናት ግን በቅርቡ በሰውም ይሁን በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም

https://p.dw.com/p/498nU
Karte Äthiopien Regionen EN

ቆሴ በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን ወደከተማ አስተዳደርነት ለማደግ እንቅስቃሴ ላይ ያለች መለስተኛ ከተማ ናት። አካባቢው ሁለት የጉራጌ እና የሃድያ ብሔረሰቦች የሚዋሰኑበት ነው። በዚህ አካባቢ  ከዚህ ቀደም ግጭት ተከስቶ ነበር። አካባቢው በህዝበ ውሳኔ ወደ ጉራጌ ዞን ተጠቃሎ ከቆየ ከረዥም ዓመታት በኋላ አሁን ደግሞ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለዶይቸ ቬለ እንደገለፁት ግጭት እንደ አዲስ ተነስቷል ። » ለውጡ ከመጣ በኋላ በሀዲያ ዞን የሚኖሩ ወጣቶች ከተማው ለኛ ይገባል በሚል መነሳሳት ውዝግብ ተነስቷል። እና አሁንም ድረስ ከፍተኛ የሆነ የአካል ጉድለት እና የንብረት ጉድለት እየተፈፀ ነው። ብዙ ቤቶች ተቃጥለዋል። »እንደ የአካባቢው ነዋሪ ከሆነ ችግሩ በውይይት ተፈታ በተባለ እለትም ቤቶች ተቃጥለዋል ንብረትም ወድሟል። « እስከዛሬ ድረስ ውጥረት ላይ ነው ያለው። ምንም መፍትሄ አላገኘም። ከተማዋ ላይ ትልቅ ገበያ ነበር። ግን እየተካሄደበት አይደለም»
እናም ከመንግሥት አካላት መፍትሄ እንፈልጋለን ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች። ጉዳዩን አስመልክቶ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሃመድ ጀማል በመሠረተ ልማቶች ላይ በተደራጀ መልኩ ጥቃት የሚፈፅሙ ሰዎች እንደነበሩ ገልፀው «ዘግይተንም ቢሆን» በቅርቡ ችግሩን ለመፍታት ችለናል ይላሉ።  ባለፉት ሁለት ወራት በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም ይታያል ያሉን የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሁንም ግን አንዳንድ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ተጠርጣሪ ሰዎች መኖራቸውን ገልፀዋል። 
ቆሴ ከ 16 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች አብረው የሚኖሩበት ከተማ እንደሆነች የገለፁልን የድቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዴ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምክንያት አለመግባባቶች የነበሩ ቢሆንም እነዚህ ጥያቄዎች አሁን በምክክር እና በውይይት ተፈተዋል ይላሉ። ይሁንና አሁንም የህዝቡን እንድነት ለመሸርሸር የሚሞክሩ ውስን ግለሰቦች አሉ ብለዋል። አቶ አለማየሁ አክለውም እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎችን ህዝቡ ጠይቀዋል። ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ሰዎችም በህግ እንደሚጠየቁ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። 

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ