በገንዳ ውኃ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በከፈቱት ተኩስ ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ | ኢትዮጵያ | DW | 09.01.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

በገንዳ ውኃ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በከፈቱት ተኩስ ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በገንዳ ውኃ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በትላንትናው ዕለት  በከፈቱት ተኩስ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸው እና 15 መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች ለDW ገለጹ። ድርጊቱን በመቃወም ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡት የከተማይቱ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት ከስፍራው ለቅቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 02:45
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
02:45 ደቂቃ

ነዋሪዎች መከላከያ ሰራዊትአካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል

የመንግሥትት ሠራተኛ የሆኑ አንድ የዓይን እማኝ እንደተናገሩት የመከላከያ ሰራዊት አባላት በነዋሪው ላይ ተኩስ የከፈቱት በነዋሪዎች ታግተው የነበሩ የሱር ኮንስትራክሽን ድርጅት ተሽከርካሪዎችን ለማስለቀቅ በሚል ነበር። “የመከላከያ ሰራዊት የእሩምታ ተኩስ ተኩሶ ጉዳት አድርሷል። ባለኝ መረጃ መሰረት ህጻናትን ጨምሮ ወደ 15 ገደማ የሚሆኑ የቆሰሉ ሲሆን የሟቾቹ ቁጥር ዘጠኝ ደርሷል” ሲሉ እኚሁ የከተማይቱ ነዋሪ ተናግረዋል። 
የሞቱትም ሆነ የተጎዱ ሰዎች ወደ ገንዳ ውሃ መተማ ሪፈራል ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሚናገሩት የዓይን እማኙ ከማቾቹ ውስጥ የስድስት ሰዎችን አስክሬን መመልከታቸውን ገልጸዋል። “እኔ ስድስት ሰዎች ተመልክቻለሁ። እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት እስከነበርኩበት ድረስ ከገንደ ውሃ ከተማ አንዲት ህጻንን ጨምሮ ሶስት ሰዎች፣ ከኮኪት ከተማ ደግሞ ሶስት ሰዎች ነበሩ” ሲሉ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። ከቆሰሉት ውስጥ በእርሻ ስራ ላይ ቆይተው ሲመለሱ የነበሩ የቀን ሰራተኞች አሉበት ብለዋል። 
የገንደ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች የመከላከያ ሰራዊትን እርምጃ በመቃወም ዛሬ አደባባይ ወጥተዋል። ከጠዋት እስከ እኩለ ቀን ድረስ በዘለቀው ተቃውሞ ይሰሙ ከነበሩት መፈክሮች ውስጥ “የወህሓት መከላከያ እኛን አይወክልም፤ በፍጥነት ይውጣልን”፣ “በአማራነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ይቁም” የሚሉ እንደሚገኙበት ከሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች አንዱ ተናግረዋል።
ሰልፈኞቹ ትላንት ወደ ኮኪት ከተማ እንዲወሰዱ የተደረጉት የሱር ኮንስትራክሽን ተሽከርካሪዎች ወደ ገንደ ውሃ ከተማ እንዲመለሱ እንዲደረግ እና አስፈላጊውን ማጣራት እንዲደረግባቸው መጠየቃቸውን የከተማይቱ ነዋሪ ገልጸዋል። በተቃውሞ ምክንያት ከአዘዞ እስከ መተማ የሚዘልቀውን አውራ ጎዳና መዘጋቱንም ጨምረው አስረድተዋል። ለተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ምላሽ ለመስጠት የአካባቢው አስተዳደርም ሆነ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች በስፍራው አለመገኘታቸውንም አክለዋል። 

ተስፋለም ወልደየስ

አለምነው መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic