በጀርመን ፍርድ ቤት ብይን ያገኙት ሩዋንዳዊ | አፍሪቃ | DW | 19.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በጀርመን ፍርድ ቤት ብይን ያገኙት ሩዋንዳዊ

ከ 20 ዓመት በፊት ሩዋንዳ ውስጥ ሙቩምባ በተባለች ሰሜን ምሥራቃዊ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ኦንስፎር ሩዋቡኮምብ የተባሉት የ 54 ዓመት ጎልማሳ ፣ ያኔ በአንድ ቤተ-ክርስቲያን የተጠለሉ ሩዋንዳውያን እንዲጨፈጨፉ በማድረጋቸው ፣ ፍራንክፈርት ጀርመን ውስጥ

፣ ትናንት፣ በአንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14 ዓመት እሥራት ተበየነባቸው። እኒህ ሰው ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸው በችሎቱ ሲነገራቸው ከፊታቸው አንዳች የሚነበብ ነገር አልነበረም።

የመሃል ዳኛ ቶማስ ዛገቢል በብይኑ ላይ እንደገለጡት ያኔ፤ በእኒህ ሰው አስተባባሪነት ነበረ ቢያንስ 400 የቱትሲ ብሔረሰብ አባላት በሁቱ ብሔረሰብ ሚሊሺያ ጦረኞች፤ እጅግ በሚያሰቅቅ ሁኔታ በቆንጨራ፣ በመጥረቢያ፤ በአንካሴና በመሳሰለው የተጨፈጨፉት ። የተገደሉት ቁጥር 1,200 እንደሚደርስም ይነገራል። የተገደሉትን ውሃ ጉድጓድ ውስጥ እንዲወረውሩ የተገደዱት ከጭፍጨፋው የተረፉት ዓይናቸው እያየ እየዘለሉ ጉድጓዱ ውስጥ በመግባት ከሟቾች ጋር እንዲቀላቀሉም ነበረ የተገደዱት። እ ጎ አ ሚያዝያ 11 ቀን 1994 ዓ ም፤ በዚያ የተፈጸመው ድርጊት ፍጹም የሚረሳ አይደለም።

ብይኑ እንደተሰጠ፤ ከከሳሾቹ መካከል አንጀሊክ ኬ የተባሉት እንዲህ ነበረ ያሉት --

«ወደ ፍርድ ቤቱ በተመላለስኩባቸው ጊዜያት ዘወትር የማስበው እጅግ የምወዳትንና የተገደለችውን ወላጅ እናቴን ነበር።»

የፍርንክፈርት ከፍተኛ ፍርድ ቤት 120 ገደማ የሚሆኑ የዓይን ምሥክሮችን ቃል ከማዳመጡም ሌላ ወንጀል መርማሪዎችን ሩዋንዳ ድርስ ልኮ አንዳንድ ሁኔታዎችን አስጠንቷል።

ከከሳሾቹ መካከል ሌላው አሎይስ አር የተባሉት፣ ስለ ብይኑ እንዲህ ብለዋል።

«14 ዓመት በጣም ቀላል ቅጣት ነው፤ይሁንና የሕጉ አካል ያሳለፈውን ውሳኔ መቀበል ይኖርብናል። »

ሩዋንዳ ውስጥ፣ ከሚያዝያ እስከ ሐምሌ 1986 ዓም፤ የሁቱ ጎሳ ሚሊሺያ ጦረኞች፤ 800,000 ያህል ቱትሲዎችንና ለዘብ ያለ አቋም እንደነበረቸው የተነገረላቸውን ሁቱዎች መጨፍጨፋቸው የሚታወስ ነው። በሥልጣናቸው ፤ ማስቆም ሲችሉ መንፈሳዊ አምልኮ በሚፈጸምበት ቅዱስ ቦታ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉ ሰዎች እንዲፈጁ የተባበሩት የያኔው የሙቩምባ ከተማ ከንቲባ ጀርመን ገብተው የፖለቲካ ተገን የጠየቁት እ ጎ አ በ 2002 ዓም ሲሆን፤ በኢንተር ፖል በኩል የተያዙት እ ጎ አ በ 2011 ነው። 3 ዓመታት የወሰደው የፍርድ ቤት የምርመራ ሂደት ትናንት እልባት አግኝቷል። በ ኦንስፎር ሩዋቡኮምብ ላይ ተጨማሪ ክስ ያቀረቡ ወገኖች ጠበቃ የሆኑት ጀርመናዊው ዲተር ማግሳም እንዲህ ነበረ ያሉት--

«በምርመራው ውጤት መሠረት ፤ ሰውየው ድርጊት ፈጻሚ መሆናቸው፤ ትእዛዝ ስለማስተላለፋቸው ብይን መግኘት ተገቢያቸው ነበር። በወንጀሉ መጠን መሠረት ዕድሜ ይፋታህ በተገባቸው ነበር። ነገር ግን፤ የቅጣቱ መጠን አይደለም ምናልባት ወሳኝነት ያለው። ዋናው ቁም ነገር፣ የተፈጸመው ድርጊት ፤ ሩዋቡኮምብም ያ ድርጊት እንዲፈጸም ያደራጁ መሆናቸው ዕውቅና ማግኘቱ ነው። »

ኦንስፎር ሩዋቡኮምብ፣ በጀርመን ፍርድ ቤት የተጠቀሰውን ብይን ማግኘታቸውን የሩዋንዳ ተወላጆች ፤ ቅጣቱ ከባድ ባይሆንም ፤ ወንጀለኛ የትም ሀገርና ቦታ ይሁን ተገቢውን ፍርድ ማግኘት እንዳለበት ዓለም አቀፉና ፍትኀዊው ደንብ በማረጋገጡ ከሞላ ጎደል ርካታ ሳይሰማቸው አልቀረም።

የሩዋንዳ የፍርድና ፍትኅ ጉዳይ ባለሥልጣን ቃል አቀባይ አላን ሙኩራሪንዳ፣ በበኩላቸው ይህን ነበረ ያሉት።

«የጀርመን ፍርድ ቤት ብይን በማስተላላፍ ተግባሩን ፈጽሟል። ተከሳሹ ብያኔውን ወንጀል በፈጸሙበት ሀገር ፍርዳቸውን ቢያገኙ የተሻለ ይሆን ነበር። ይሁን እንጂ፤ የፍርንክፈርቱ ፍርድ ቤት በውሳኔው ያስተላለፈው ጠንካራ መልእክት፣ ህዝብን የመጨፍጨፍ ወንጀል የጊዜ መርዘም የማይሽረው መሆኑን ነው። ወንጀል የፈጸመውም የትም አገር ይሁን በማንኛውም ጊዜ ፍርድ ማግኘት እንደሚገባውም አሳይቷል።»

ጀርመን ፣ እንዳስታወቀችው፤ ህዝብን በማስጨፍጨፍ የተከሰሱትን ሰው፤ የደን ኻኹ ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች መርማሪና ብይን ሰጪ ፍርድ ቤት እንዲሁም በአሩሻ ፣ ታንዛንያ የሚገኘው የሩዋንዳውን የጭፍጨፋ ድርጊት የሚከታተለው ፍርድ ቤት እንዲያስረክቧት ባለመጠየቃቸውና ወደ ሩዋንዳም ቢላኩ ፍትኃዊ ብይን የማግኘታቸው ሁኔታ ስላጠራጠራት በራሷ ግዛት ምርመራውንና የፍርዱን ሂደት ለመምራት ተገዳለች።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች