በጀርመን ጥቃት አድራሹ የ«IS» ተከታይ ነዉ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

በጀርመን ጥቃት አድራሹ የ«IS» ተከታይ ነዉ

በጀርመን ባቫርያ ግዛት ዉስጥ ባለች አንስባህ በተባለች አነስተኛ ከተማ አንድ ከሶርያ የመጣ ስደተኛ የጣለዉ የፍንዳታ ጥቃት ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ መሆኑ ተገለፀ። ራሱን እስላማዊ መንግሥት ሲል የሚጠራዉ አሸባሪ ቡድን በበኩሉ አጥፍቶ ጠፊዉ የቡድኑ ተዋጊ እንደነበርም ገልፆአል።በጀርመን ባቫርያ ግዛት ዉስጥ ባለች አንስባህ በተባለች አነስተኛ ከተማ አንድ ከሶርያ የመጣ ስደተኛ የጣለዉ የፍንዳታ ጥቃት ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ መሆኑን የባቫርያ ግዛት የሃገር ዉስጥ አስተዳደር ሚኒስትር ዮአሂም ሄርማን አስታወቁ። ሚንስትሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጥቃት አድራሹ ለሽብርተኛ ቡድኑ ታማኝ መሆኑ የታወቀዉ በኪሱ በያዘዉ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ በተገኘዉ የሽብርተኛ ቡድኑ ቪዲዮ ላይ ነዉ። ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራዉና አቡበከር አልባግዳዲ «በአላህ ስም ጀርመን ላይ ጥቃት ይጣላል » ሲል የሚዝትበት ፊልም በጥቃት አድራሹ ስልክ ላይ ተገኝቶአል። ትናንት በጀርመን ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ በተጣለዉ በዚህ አጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ሶርያዊዉ ራሱን ገድሎ አስራ ሁለት ሰዎችን ለጉዳት ዳርጎአል። የ 27 ዓመቱ ሶርያዊ ወደ 2500 ሰዎች በአካባቢው ላይ በሚገኝ ገላጣ ሜዳ ላይ ተሰብስበዉ ይከታተሉ በነበረበት የሙዚቃ ድግሱ መኃል ለመግባትና ፈንጂውን ለማፈንዳት ሞክሮ ሳይሳካለት በመቅረቱ ነበር የሙዚቃ ድግስ አቅራብያ በሚገኝ ቡና ቤት በራፍ ላይ ራሱን ያነጎደዉ። ጥቃት አድራሹ ሶርያዊ ተገን ጠያቂ የያዘዉን ከብረታ ብረት የተሰራ ተቀጣጣይ ፈንጂ ይዞ የነበረዉ በጀርባ በሚታዘል ቦርሳ ነበር። « ሰዎች አለመገደላቸዉ » አንድ እድል መሆኑን የባቫርያ ግዛት የሃገር ዉስጥ አስተዳደር ሚኒስትር ዮአሂም ሄርማን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

Deutschland Ansbach Explosion Pressekonferenz Innenminister von Bayern Joachim Herrmann

የባቫርያ ግዛት የሃገር ዉስጥ አስተዳደር ሚኒስትር ዮአሂም ሄርማን


« ተገን ለመጠየቅ ወደ ሃገራችን መጥቶ እንዲህ አይነቱን ጭካኔ የተሞላዉ ወንጀል መፈፀሙ በራሱ በጣም መጥፎ ነዉ። በዚሁ ድርጊቱ በርካቶችን ጎድቶአል፤ አንዳንዶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የእድል ጉዳይ ነው ተጨማሪ ሌሎች ሰዎች አለመሞታቸዉ።»
የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ወደ ጀርመን እንደመጣ የተነገረው ሶርያዊ በጀርመን የጥገኝነት መብት ተከልክሎ ጊዜያዊ መኖርያ ፈቃድ ያገኘ ሲሆን ፣ ግለሰቡ የእጽ ዝዉዉርን ጨምሮ፤ በስርቆት ወንጀል፤ እንዲሁም፣ ከሰዎች ጋር በመጣላት በፖሊስ ዘንድ መታወቁ ተዘግቦአል። የባቫርያ የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ባወጣዉ መግለጫ መሰረት ግለሰቡ ሁለት ጊዜ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ አድርጎ፣ የአዕምሮ ድጋፍና ህክምናም ተደርጎለታል። በቅርቡ በወጣ ዜና በአንስባህ ጀርመን የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት የጣለዉ የሶርያ ተወላጅ ባለፈዉ ሐምሌ ከጀርመን እንዲወጣ ሁለት ጊዜ ወረቀት ደርሶት ነበር። ከአለፈዉ ሳምንት ጀምሮ ጀርመን ዉስጥ ተከታታይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ሕዝብ በሚበዛባቸዉ አካባቢዎች ተጨማሪ የፖሊስ ጥበቃ እንዲሰማራም ተጠይቆአል። ራሱን እስላማማዊ መንግሥት የሚለዉ አሸባሪ ቡድን በጀርመን አንስባህ ከተማ ለተጣለዉ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ከአንድ ሰዓት በፊት ሃላፊነትን ወስዶአል፣ የአንስባህ ጥቃት አድራሹ ግለሰብ የቡድኑ ተዋጊ እንደነበርም ገልፆአል።

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ