በጀርመን የደረሰዉ ጥቃት ከሽብር ጋር የተያያዘ ይሆን? | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

በጀርመን የደረሰዉ ጥቃት ከሽብር ጋር የተያያዘ ይሆን?

በጀርመን ባቫርያ ግዛት አንስባህ በተባለች አነስተኛ ከተማ አንድ ከሶርያ የመጣ ስደተኛ የጣለዉ የፍንዳታ ጥቃት ከሽብርተኝነት ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ የባቫርያ ግዛት የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ዮአሂም ሄርማን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቁ።

ትናንት በጀርመን ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ በተጣለዉ በዚህ አጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ሶርያዊዉ ራሱን ገድሎ አስራ ሁለት ሰዎችን ለጉዳት ዳርጎአል። የጥቃት አድራሹ ሶርያዊ ዓላማ ምን እንደሆነ ግልፅ የሆነ ነገር ባይኖርም ፤ ጥቃቱ ከእስላማዊ ጽንፈኝነት ጋር ተያያዥ ሳይሆን እንደማይቀር ተገልጾአል። 27 ዓመቱ ሶርያዊ ወደ 2500 ሰዎች የሚሆኑ መሃል ከተማ ላይ በሚገኝ በገላጣ ሜዳ ላይ ተሰብስበዉ ይከታተሉ በነበረበት የሙዚቃ ድግስ መኃል ለመግባትና ፈንጂውን ለማፈንዳት ሞክሮ ሳይሳካለት በመቅረቱ ነበር የሙዚቃ ድግስ አቅራብያ በሚገኝ ቡና ቤት በራፍ ላይ ራሱን ያነጎደዉ። ጥቃት አድራሹ ሶርያዊ ተገን ጠያቂ የያዘዉን ከብረታ ብረት የተሰራ ተቀጣጣይ ፈንጂ ይዞ የነበረዉ በጀርባ በሚታዘል ቦርሳ ነበር። « ሰዎች አለመገደላቸዉ » አንድ እድል መሆኑን የባቫርያ ግዛት የሃገር ዉስጥ አስተዳደር ሚኒስትር ዮአሂም ሄርማን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልፀዋአል። የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ወደ ጀርመን እንደመጣ የተመለከተዉ ሶርያዊ በጀርመን የጥገኝነት መብት ተከልክሎ ጊዜያዊ መኖርያ ፈቃድ ያገኘ ሲሆን ፣ ግለሰቡ የእጽ ዝዉዉርን ጨምሮ፤ በስርቆት ወንጀል፤ እንዲሁም፣ ከሰዎች ጋር በመጣላት በፖሊስ ዘንድ መታወቁ ተዘግቦአል። የባቫርያ የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ባወጣዉ መግለጫ መሰረት ግለሰቡ ሁለት ጊዜ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ አድርጎ፣ የአዕምሮ ድጋፍና ህክምናም ተደርጎለታል። የሶርያዊዉን መኖርያ ቤት ፖሊስ ፈትሾአል፤ እስካሁን ግን ስለ ጥቃቱና ስለማንነቱ የተሰጠ ይፋ መግለጫ የለም። በአካባቢው ወደ 200 የሚጠጉ የፀጥታ አስከባሪዎች መሰማራታቸውን ተያይዞ የወጣው ዜና አመልክቶአል።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ