በጀርመን የተፈጥሮ ጋዝ ፍጆታ ዋጋ ጭማሪና ተፅእኖዎቹ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 16.08.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

በጀርመን የተፈጥሮ ጋዝ ፍጆታ ዋጋ ጭማሪና ተፅእኖዎቹ

የጀርመን ፓርላማ ባጸደቀው ሕግ መሠረት ከጎርጎሮሳዊው ጥቅምት አንድ ቀን 2022 ዓም አንስቶ በጀርመን የተፈጥሮ ጋዝ ፍጆታ ክፍያ በሰዓት 2.4 የዩሮ ሳንቲም እንዲሆን ተወስኗል። እስከ ሚያዚያ 2024 ዓም ይጸናል የተባለው ይህ ጭማሪ 4 አባላት ላሉት ቤተሰብ ታክሱን ሳይጨምር በዓመት ወደ 500 ዩሮ የሚጠጋ ተጨማሪ ገንዘብ ያስወጣል ተብሏል።

በጀርመን የተፈጥሮ ጋዝ ፍጆታ ዋጋ ጭማሪና ተፅእኖዎቹ

ከኃይል ፍላጎቷ ግማሹን ከሩስያ ታስገባ የነበረው ጀርመን በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ከሞስኮ የምታገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ በአንድ ሦስተኛ ከቀነሰ  ወዲህ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዷን ቀጥላለች ። የሚጎድልባትን ጋዝ ለመተካት አማራጭ የኃይል ምንጮች ገበያዎችን በማፈላለግ ላይ ያለችው ጀርመን ፣ጎን ለጎን የኃይል ቁጠባ እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግም ጀምራለች። በዚህ ረገድ የከተማ አስተዳደሮች መወሰድ የጀመሯቸውን እርምጃዎች መጥቀስ ይቻላል።ከመካከላቸው ከጀርመን በህዝብ ብዛት አራተኛውን ደረጃ በምትይዘው በምዕራብ ጀርመንዋ የኮሎኝ ከተማ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ቁጠባ ለአብነት የሚጠቀስ ነው። የከተማዋ ታሪካዊ ቦታዎች ትላልቅ ህንጻዎች ድልድዮች ሌሎችም ስፍራዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ለሊቱን በሙሉ በተለያዩ የመብራት ቀለማት አሸብርቀው ደምቀው መታየታቸው ቀርቷል። ከጀርመን ታሪካዊ ስፍራዎች ዋነኛው የሀገር ጎብኚዎች መስህብና ፣ የኮሎኝ ከተማ ፈርጥ ትልቁ ካቴድራል ዶም እንደቀድሞው ለሊት ሲበራ ማደሩ ቀርቷል። ይህ ከዩክሬኑ ጦርነት በኋላ ጀርመን ከሩስያ የምታስገባው የተፈጥሮ ጋዝ በመቀነሱ የተወሰደ በግልጽ የሚታይ የኃይል ቁጠባ እርምጃ ነው። ከዚህ ሌላ የከተማዋ ትልቁ የእግር ኳስ ስታድዮም፣ታሪካዊው ማዘጋጃ ቤቷ፣እና የከተማዋ መለያ በሆነው በአገር አቋራጩ በራይን ወንዝ ላይ የተገነቡት ድልድዮች መብራቶች ለሊት አይኖሩም ፣በአጠቃላይ በኮሎኝ ከተማ ብቻ 130 የመንግሥት ህንጻዎችና

የመንገድ  መብራቶች ከምሽቱ አምስት ሰዓት በኋላ ይጠፋሉ። የኮሎኝ ከተማ የወሰደው ይህ እርምጃም የአውሮጳ ኅብረት ባቀደው የ15 በመቶ የኃይል ቅነሳ መሠረት የተካሄደ ነው። የከተማዋን የኃይል ቀውስን ጉዳይ የሚከታተለው ቡድን ሃላፊ አንድሪያ ብሎመ «  ከዚህም ለባሰ አስቸኳይ ችግር እንዘጋጅ» ይላሉ። ሙቀት በማያስሳስብበት በአሁኑ የበጋ ወራት አሁን መቆጠብ የተጀመረው የኤሌክትሪክ ፍጆታ መሆኑን ነው ሃላፊዋ የገለጹት።ከዚህ ሌላ ጀርመናውያን ገላቸውን ሲታጠቡና ምግብ ሲያበስሉም ብዙ ጊዜ እንዳይወስዱና የሙቅ ውሀ አጠቃቀማቸውን እንዲቀንሱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። በትናንትናው እለት ደግሞ የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ መጨመሩ ተነግሯል። የጀርመን የጋዝ ገበያ ጉዳይ የሚመለከተው «ትሬዲንግ ሀብ ዩሮፕ» የተባለው ድርጅት ትናንት እንዳስታወቀውየጀርመን ፓርላማ ባጸደቀው ሕግ መሠረት ከጎርጎሮሳዊው ጥቅምት አንድ ቀን 2022 ዓም አንስቶ በጀርመን የተፈጥሮ ጋዝ ፍጆታ ክፍያ  በሰዓት ሁለት ነጥብ አራት የዩሮ ሳንቲም እንዲሆን ተወስኗል። እስከ ሚያዚያ 2024 ዓም ይጸናል የተባለው ይህ የዋጋ ጭማሪ አራት አባላት ላሉት ቤተሰብ ታክሱን ሳይጨምር በዓመት ከእስካሁኑ ክፍያ ወደ 500 ዩሮ የሚጠጋ ተጨማሪ ገንዘብ ያስወጣል ተብሏል። ከፍተኛ ትምሕርታቸውን ጀርመን የተከታተሉትና የሚሰሩት የምጣኔ ሀብት ምሁርና የአስተዳደር ባለሞያ ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ በሰዓት የተደረገው ጭማሪ አነስተኛ ቢመስልም በዓመት ሲሰላ ግን ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ ጭማሪም እያንዳንዱ ተጠቃሚ ሀገሪቱ ያጋጠማትን ችግር ለማቃለል የሚያደርገው አስተዋጽኦ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።
የዋጋ ጭማሪውን መራራ መድሐኒት መዋጥ ሲሉ የገለጹት የጀርመን የኤኮኖሚና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሮበርት ሀቤክ ውሳኔው የተላለፈው አደጋ ላይ ሊወድቁ የሚችሉትን የጀርመን ኩባንያዎችን ለመታደግ ነው ብለዋል።«አዲሱ የዋጋ ጭማሪ ህዝቡ ላይ ሊጫን ይችል የነበረውን ተጨማሪ ወጪ መጋራት የሚቻልበት አድሎአዊ ያልሆነ መንገድ ነው። አማራጩ የዋጋ ጭማሪን ማስቀረት አይደለም። ይህ ባይሆን የጀርመን የኃይል ገበያ መንኮታኮት እና ከዚሁ ጋርም የአብዛኛው የአውሮጳ የኃይል ገበያ እጣ ተመሳሳይ መሆኑ አይቀር »

ሚኒስትር ሮበርት ሀቤክ እንዳሉት የትናንቱ ውሳኔ አስፈላጊ የሆነበት ሌላም ምክንያት አለ።"በማያከራክር ሁኔታ ይህን ጨምሮ ሁሉም እርምጃዎች ዋጋ ያስከፍላሉ። የሚወሰዱ እርምጃዎች በሙሉ መዘዞች ይኖሩዋቸዋል፤ አንዳንዶቹም በግድ የሚጫኑ ናቸው። ሆኖም እኛን መፈናፈኛ  ለማሳጣት የሚያደርጉትን ሙከራ  ይቀንስልናል። እርምጃው ከሩስያ የተፈጥሮ ጋዝ ጥገኝነት ለመላቀቅ

Sonnenenergie

እንድንወስን ያደርገናል። በመጨረሻም የውጭና የደኅንነት የፖለቲካ መርሆቻችን በሚመለከት በሉዓላዊነት መንቀሳቀስ ያስችለናል።»ይሁንና የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች የዋጋ ጭማሪው ከአውሮጳ ግዙፍ ኤኮኖሚ በምታንቀሳቅሰው በጀርመን ተጨማሪ የዋጋ ንረት ያስከትላል የሚል ስጋት አላቸው። እንደ ባለሞያዎቹ የዋጋ ንረቱ በአሁኑ ጊዜ 8.5 በመቶ አሻቅቧል።ዶክተር ጸጋዬ ደግነህም የዋጋ ጭማሪው በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ላይ ይሁን በአጠቃላይ በጀርመን ምጣኔ ሀብት ላይ የተለያዩ ተጽእኖዎችን ማሳደሩ አይቀርም ባይ ናቸው። በሌላ በኩል ግን በርሳቸው እምነት  የጀርመን ኤኮኖሚ በቀላሉ የሚጎዳ አይደለም ። 

ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ 

Audios and videos on the topic