በጀርመን የሽብር ጥቃት መክሸፍ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 03.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

በጀርመን የሽብር ጥቃት መክሸፍ

ዱስልዶርፍ ከተማ ጀርመን ዉስጥ ጥቃት ሊያደርሱ ነበር በሚል የተጠረጠሩ ሦስት የሶርያ ዜጎች ትናንት መያዛቸዉ ተሰምቷል። ባለፈዉ ዓመት በርካታ ስደተኞች ወደ ጀርመን ሲገቡ አብረዉ እንደመጡ የተገለጸዉ ሶርያዉያን ተገን ጠያቂዎች ራሱን የኢራቅ እና ሶርያ እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ፅንፈኛ ቡድን ISIS ሳይልካቸዉ እንዳልቀረ አቃቤ ሕግ አመልክቷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 02:58

የሽብር ስጋት በጀርመን

አቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎቹ ሁለቱ አጥፍቶ በመጥፋት ሌሎቼ ደግሞ በእሩምታ ተኩስ በርካቶችን ለመግደል ማቀዳቸዉን ቢገልጽም፤ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ተቃርበዉ እንደሆን የሚጠቁም መረጃ አለመኖሩም ተገልጿል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ጀርመን ዉስጥ ሊደርሱ የታቀዱ የሽብር ጥቃቶች አንድም መክሸፋቸዉን አንድም ሳይሳኩ መደናቀፋቸዉን ዘገባዎች ያመለክታሉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011ዓ,ም መጋቢት ወር ግን አንድ የኮሶቮ አልባንያ ዜጋ ፍራንክፈር አዉሮፕላን ማረፊያ ላይ ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮችን ገድሎ ሌሎች ሁለት አቁስሏል። በቁጥጥር ሥር የዋለዉ ጥቃት አድራሽ የዕድሜ ልክ እሥራት ተፈርዶበታል። ባለፈዉ የካቲት ወር የጀርመን ፖሊስ በመላ ሀገሪቱ በተለያዩ ግዛቶች የሽብርተኞች ሠንሰለት እና ቡድን መኖሩን እንደደረሰበት አሳዉቆ በርሊን፣ ኖርድ ራይን ቬስትፋለን፤ እንዲሁም ኒደር ዛክሰን በፈጣን ርምጃ መረቡን በጣጥሰዉ አራት ተጠርጣሪ አልጀርያዉያን ተይዘዉ የጥቃት ሴራዉ በእንጭጩ ተቀጨ። በተመሳሳይም በጀርመን የኖርድ ራይን ቬስት ፋለን ፌደራል ግዛት ዋና ከተማ በሆነችዉ ዱስልዶርፍ ሊጣል የታቀደዉ ጥቃት ከወዲሁ መክሸፉ ተገልጿል። ቀድሞ የከተማዉ ዋና ጎዳና የነበረዉ በርካቶች በእግር የሚንሸራሸሩበት ተወዳጅ ጎዳና ሃይንሪሽ ሃይን አለ ነበር የሽብር ጥቃቱ ዒላማ። ጥቃቱን በማቀነባበር የተጠረጠሩት ሐምዛ ሲ፤ ማሆድ ቢ፤ እንዲሁም አብድ አራህማን ኤኬ የተባሉት ሦስት የሶርያ ዜጎች ከጀርመን የተለያዩ ከተሞች ተይዘዋል። አራተኛዉ ተጠርጣሪ ሳላህ ኤ ፓሪስ ፈረንሳይ ዉስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ እና ወደ ጀርመን የሚላክበት ሂደት መጀመሩም ተሰምቷል።ይህ ተጠርጣሪ የተያዘዉ ባለፈዉ የካቲት ወር ቀ ደም ብሎ ሲሆን የጥቃት ዕቅዱን ለፖሊስ የዘረዘረዉ እሱ መሆኑም ተገልጿል። የኖርድራይን ቬስትፋለን ፌደራል ግዛት የሀገር ዉስጥ ሚኒስትር ራልፍ ያንገር በሃገራቱ መካከል ያለዉ የመረጃ ልዉዉጥ ለጥቃት ዕቅዱ መክሸፍ ትልቅ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል።

Deutschland, U-Bahn-Station Heinrich-Heine-Allee, Düsseldorf

የጥቃት ዒላማ የነበረዉ ጎዳና

«ይህን የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች በትብብር ለመሥራታቸዉ ጥሩ ምሳሌ ነዉ። ጀርመን ዉስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለዉ የጥቆማ እና መረጃ ልዉዉጥ ይደረጋል። ለዚህም ነዉ ሴራዉን ገና በእንጭጩ ፖሊስ ለማክሸፍ የቻለዉ።»

ተጠርጣሪዎቹ ወደ ጀርመን የገቡት መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሀገሪቱ ድንበሯን ለስደተኞች ክፍት እንድታደርግ ባሳለፉት አወዛጋቢ ዉሳኔ መሆኑን የጠቆመዉ የጀርመን የዜና ወኪል DPA ዘገባ፤ ሶርያዉያኑ የISIS አባላት ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ያመለክታል። በተለይም አብድ አራህማን ኤኬ በሽብርተኝነት የተፈረጀዉ የሶርያ ተቃዋሚ ቡድን አል ኑሥራ ግንባር ጋር አብሮ ሳይሰራ እንዳልቀረም ዘርዝሯል። ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል አንደኛዉ ካልርልስሩኸ ፍርድ ቤት ቀርቧል። ሃይድልበርግ ከተማ በሚገኝ የስደተኞች መኖሪያ የቆየዉ የ31 ዓመቱ ተጠርጣሪ የፈንጂ ቀበቶ ለማዘጋጀት ኃላፊነት ተሰጥቶት እንደነበርም ተገልጿል። ያም ሆኖ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ ፍራዉከ ከኽለር የጥቃት ዕቅዱን ተግባራዊነት የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳልተገኘ ተናግረዋል።

«ባለን መረጃ መሠረት ተጠርጣሪዎቹ የጥቃት ዕቅዳቸዉን በተጨባጭ ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀታቸዉን አያመለክትም። ፈረንሳይ ዉስጥ ከሚካሄደዉ የአዉሮጳ የእግርኳስ ሻምፒዮና ጋርም የተያያዘ አይደለም።»

ምንም እንኳን አቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎቹ ጥቃቱን ለማድረስ ተቃርበዉ እንደነበር የሚያሳይ መረጃ የለም ቢልም የጀርመን የሀገር ዉስጥ ሚኒስትር የሽብርተኞች ጥቃት ስጋት በሀገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን አመልክቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic