በጀርመን የስደተኛው ቁጥር መጨመር | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 20.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

በጀርመን የስደተኛው ቁጥር መጨመር

በጀርመን መንግሥት ትንበያ መሠረት፣ በዚህ ዓመት ጥገኝነት ፈልገው ወደ ሃገሩ የሚመጡት ስደተኞች ቁጥር 800,000 ይደርሳል።በጀርመን ታሪክ ይህን ያህል ተገን ጠያቂ ሲገባ ይህ የመጀመሪያ መሆኑ ነው። የስደተኛዉ ቁጥር በተለይ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ መጨመሩ በጀርመን ፖለቲከኞች እና ሕዝብ ዘንድ አነጋጋሪ ርዕስ ሆኖዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:00
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:00 ደቂቃ

የተገን ጠያቂው ቁጥር በጀርመን ካሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እጅግ በጣም ከፍ እንደሚል ነው የሚጠበቀው። የጀርመን መንግሥትን ትንበያ ሰሞኑን በጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ያደረጉት የሃገር አስተዳደር ሚንስትር ቶማስ ደ ሜዝየር እንደገለጹት፣ ጥገኝነት እንዲሰጠዉ የሚጠይቀዉ ስደተኛ ቁጥር በጎርጎሮስያዊው የዘመን ቀመር 2015 ዓም መጨረሻ ወደ 800,000 ይደርሳል።

« ይህም ባለፉት የፀደይ ወራት ከቀረበው ግምት በእጥፍ፣ ባለፈው ዓመት በዚሁ ጊዜ ከነበረው ደግሞ በአራት እጥፍ በልጦ ነው የተገኘው። በወቅቱ የሚታየው ይህ የናረው የስደተኞች ቁጥር ለሁላችንም ትልቅ ፈታኝ ሁኔታ ቢፈጥርም፣ ለጀርመን ከአቅሟ በላይ አለመሆኑን ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ። »

ባለፈው ሀምሌ ወር ብቻ ወደ 83,000 የሚጠጉ ተገን ጠያቂዎች ናቸው ጀርመን የገቡት፣ ከነዚህም ብዙዎቹ የርስ በርስ ጦርነት የሚካሄድባቸው የሶርያ፣ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ዜጎች ናቸው። በአንድ ወር ውስጥ ይህን ያህል ስደተኛ ጀርመን ሲገባ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ያስረዱት ደ ሜዝየር ምክንያቱን ሲያስረዱ፣

« ከቱርክ የኤጌይስ ባህር ወደ ቦልካን በሚወስደው መስመር የሚደረገው የፍልሰት መጠን ግዙፍ ጭማሪ ታይቶበታል። ስደተኞቹ በሚመጡባቸው ውዝግብ በቀጠለባቸው በመካከለኛ ምሥራቅ፣ በአፍሪቃ ቀንድ ወይም በሰሜን አፍሪቃ ሁኔታዎች የሚሻሻሉበት አንዳችም አዎንታዊ ምልክት አልታየም። »

ጀርመን ወደ አውሮጳ ከሚመጣው ስደተኛ መካከል እስካሁን 40 ከመቶውን ተቀብላ እንደምታስተናግድ ያስታወቁት የሃገር አስተዳደር ሚንስትር ቶማስ ደ ሜዝየር ሃገራቸው ወደፊት በዚሁ አሰራሯ ልትቀጥል እንደማትችል ሳያስገነዝቡ አላለፉም። የስደተኞቹን እና ተገን ጠያቂዎቹን አቀባበል ፖሊሲ የአውሮጳ አባል ሃገራትን አቅም ባገናዘበ መልኩ የሚካሄድበት መንገድ ሊዘጋጅ እንደሚገባ ጀርመናዊው ሚንስትር አስታውቀዋል።

ብዙዎቹ የጀርመን ከተሞች ማዘጋጃ ቤቶች ቁጥራቸው የናረውን ስደተኞች በመቀበሉ እና በማስተናገዱ ሂደት ላይ የገንዘብ አቅም እና የሰው ኃይል እንደተጓደላቸው ይናገራሉ፣

ለምሳሌ፣ ባለፈው ሀምሌ ወር መዲናይቱ በርሊን የገቡት 4,100 ስደተኞች እስኪመዘገቡ ድረስ ብዙ ቀናት መጠበቅ ነበረባቸው፣ በዚሁ ጊዜ በጎ ፈቃደኞች ከከተማይቱ ማዘጋጃ ቤቶች ጋር በመተባበር ለስደተኞቹ ምግብ፣ ውኃ በማከፋፈሉ እና መጠለያ ቦታ በማዘጋጀቱ ተግባር ርዳታ አቅርበዋል። ይህን ዓይነቱን ችግር ለማስወገድ የጀርመን መንግሥት ተጨማሪ ገንዘብ እንዲመድብ የግራ ፓርቲ ሊቀ መንበር ካትያ ኪፒንግን የመሳሰሉ የተቃዋሚውቡድኖች ጠይቀዋል።

« የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ስደተኞቹን የመቀበሉን ሂደት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ቀዳሚ አጀንዳቸው ሊያደርጉት የሚገባ ይመስለኛል። ይኸው ሂደትም ሁነኛ የፊናንስ በጀት ሊመደብለት ያስፈልጋል ባይ ነኝ። »

ጀርመን በሃገርዋ ተገን ለጠየቁ ስደተኞች ማመልከቻዎች ፈጣን መልስ የምትሰጥበትን አሰራር ለማመቻቸት ትችል የስደተኞች እና የፍልሰት ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ተጨማሪ ሰራተኞች እንደተመደቡለት እና በዚህም የተነሳ የአንድ ተገን ጠያቂ ማመልከቻ መልስ የሚያገኝበት ጊዜ በአማካይ ወደ አምስት ወር ተኩል ዝቅ ማድረግ መቻሉን የሃገር አስተዳደር ሚንስትር ቶማስ ደ ሜዝየር አስታውቀዋል። በጀርመን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም፣ ከኤኮኖሚ እና ከሲቭሉ ማህበረሰብ የተውጣጡ ተወካዮች ከአንድ ወር በኋላ ተገናኝተው የተገን አሰጣጡ አሰራር ለገጠመው ተግዳሮት ዘላቂ መፍትሔ የሚገኝበትን ውሳኔ እንዲደርሱ ጠይቀዋል።

ኒና ቬርክሆይዘር/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

 

 

 

Audios and videos on the topic